Saturday, 11 December 2021 13:09

አሜሪካ በ10 ቀናት ውስጥ ለ12 ጊዜያት ዜጎቿ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ አሳስባለች

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

  አሜሪካ ከህዳር 18  እስከ ህዳር 28 ቀን 2014  ባሉት  10 ቀናት ውስጥ ለ12 ጊዜያት ያህል ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥታለች።
የኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታ እየተባባሰ ነው በሚል ሰበብና የሽብር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በሚል ምክንያት ዜጎቿ ኢትዮጵያን በተገኘው አማራጭ ለቀው እንዲወጡ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ላይ የምትገኘው አሜሪካ፤ ዜጎቿ ወደ ገበያ ማዕከላትና ህዝብ ወደሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንዳይሄዱም አስጠንቅቃለች።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም፤ አገሪቱ የገንዘብ ችግር ላለባቸው ዜጎቿ የጉዞ ትኬት በብድር የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቷንም አስታውቃለች። በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቿ ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም እስካሁን ለማስጠንቀቂያው በተፈለገው መጠን ምላሽ እየተሰጠ እንዳልሆነም ምንጮች ጠቁመዋል። ከኤምባሲው ምንጮች በደረሰን መረጃ መሰረትም፤ እስካሁን ድረስ አገሪቱ የምታወጣቸውን ማስጠንቀቂያዎች ተቀብለው ከኢትዮጵያ ለመውጣት የቻሉ አሜሪካውያን ቁጥር በእጅጉ አነስተኛ በመሆኑ ሳቢያ አገሪቱ ተደጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን በማውጣት የዜጎቿን ስሜት ለማሸበር ጥረት እያደረገች መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

Read 11771 times