Saturday, 11 December 2021 13:08

ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ አደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የመጀመሪያ ዙር የማስተርስ ተማሪዎቹን አስመርቋል
                                        
              ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ለህልውና ዘመቻው የሚውል 100 ሺህ ብር ለገሰ፡፡ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ባለፈው እሁድ ህዳር 19 ቀን 2014 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል አስመርቋል። ኮሌጁ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ በሃገራችን የመጀመሪያ የትምህርት ዘርፍ በሆነው ፋይናንስና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በፕሮጀክት ማጅመንት ዘርፎች ትምህርታቸውን በብቃት ተከታትለው የጨረሱ 388 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
የሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ታሪኩ አቶምሳ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር ኮሌጁ ለህልውና ዘመቻው 100 ሺህ ብር መለገሱን አስታውሰው በቀጣይ የኮሌጁን ሰራተኞች፣መምህራንና ተማሪዎችን በማስተማር ድጋፉን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
ኮሌጁ በተለይም ለተመራቂ ተማሪዎች የስራ እድል ለመፍጠር ከብዙ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቆ በተጨማሪም የቢዝነስ ኢኖቬሽንና ኢንኩቤሽን ማዕከል አቋቁሞ ፍላጎት ያላቸው ተመራቂዎች የራሳቸውን ቢዝነስ እንዲጀምሩ የፋይናንስና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ በማደረግ ላይ እንደሚገኝም በዕለቱ ተገልጿል፡፡  ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ከ15 ዓመት በላይ የማስተማርና ስኬታማ ቢዝነሶችን በማቋቋም ልምድ ባላቸው ሰዎች የተቋቋመ ሲሆን በትምህርቱም ዘርፍ ያሉትን በርካታ ክፍተቶች በመሙላት በተለይም በትምህርት ጥራት ላይ አተኩሮ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት የተቋቋመ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
ኮሌጁ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ከመወጣ አኳያም ከሜሪጆይ ኢትዮጵያ 25 ህጻናትን በቋሚነት በማሳደግ ላይ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በየቀኑም 100 ለሚሆኑና በሜሪጆይ ለሚደገፉ አረጋዊያን ምግብ በማቅረብ የበኩሉን እያደረገ እንደሆነም የኮሌጁ ፕሬዝዳንት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተማሪዎች ወላጆች የክብር እንግዶችና የኮሌጁን አመራሮች ታደሙ ሲሆን በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ኤባ ሚናጀር(ዶ/ር) እና የሜሪ ጆይ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁና የስራ መመሪያ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ብልጫ ላመጡ ተመራቂዎችም ሽልማት ሰጥተዋል፡፡ ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ በሁለት የዲግሪና በሶስት የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ትምህርትን በጥራት እየሠጠ ስለመሆኑም ለማወቅ  ተችሏል፡፡

Read 11306 times