Saturday, 04 December 2021 13:30

አዲሱ የኮሮና ዝርያ በ1 ሳምንት ወደ 24 አገራት መስፋፋቱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ባለፈው ሳምንታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ የተገኘውና ከቀደምቶቹ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ጋር ሲነጻጸር በፍጥነት የመሰራጨት ባህሪ እንዳለው የተነገረለት ኦሚክሮን የተባለው አዲሱ ቫይረስ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝና እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ወደ 24 የአለማችን አገራት መሰራጨቱ ተዘግቧል፡፡
ቫይረሱ በፍጥነት መስፋፋቱን ተከትሎ በደቡባዊ አፍሪካ እና በሌሎች አስጊ አገራት ላይ የጉዞ ክልከላዎችን የሚጥሉ አገራት ቁጥር ከእለት ወደ እለት በመጨመር እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ከ56 በላይ አገራት ጠንካራ የጉዞ ክልከላዎችን ማውጣታቸውን የዘገበው ቪኦኤ፣ ቫይረሱ በመላው አለም ከፍተኛ ስጋትን መፍጠሩን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የደቡባዊ አፍሪካ አገራት መሰል የጉዞ ክልከላዎችን የባሰ ጥፋት የሚያስከትሉ ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎች በማለት መንቀፋቸውን አመልክቷል፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ በደቡባዊ አፍሪካ አገራት ላይ የተጣሉ የጉዞ ክልከላዎች፣ ቫይረሱን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ ካላቸው ሚና ይልቅ የሚያደርሱት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ የሚያመዝን አፓርታይዳዊ እርምጃዎች ሲሉ መኮነናቸውንም ዘገባው አስነብቧል፡፡
 አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው የአለማችን አገራት መካከል አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቦትስዋና፣ ናይጀሪያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ጀርመን፣ እስራኤል፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ሆላንድ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮርያ እንደሚገኙበት የተነገረ ሲሆን የጉዞ ክልከላዎችን ካወጡ አገራት መካከልም አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ህንድ፣ ብራዚል፣ እንግሊዝ፣ እስራኤል፣ ጃፓን፣ ኢራንና ፓኪስታን እንደሚገኙበትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ እንዳለው፤ ለሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች የሚሰሩት ነባር ክትባቶች ለአዲሱ ዝርያም እንደሚያገለግሉ ማስታወቁን የዘገበው ሮይተርስ በበኩሉ፣ እስካሁን ድረስ በርካታ ሰዎችን ለሞት በመዳረግ ቀዳሚነቱን የያዘው ዴልታ የተባለው የቫይረሱ ዝርያ መሆኑን መግለጹንም አስነብቧል፡፡

Read 5208 times