Saturday, 04 December 2021 13:20

ኢትዮጵያዊንና የሐገር ፍቅር ምንና ምን ናቸው?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  አድማስ ትውስታ

         "--ጋዜጠኞችና ጦማሪዎችንም በተመሳሳይ መነፅር ማየት ይቻላል፡፡ በአጐብዳጅነት ሕዝብን በተዛባ መረጃ መደለል፣ ሌላኛውን ወገን ጥላሸት መቀባትና ስም ማጥፋት፣ በማህበራዊ ድረ-ገፅ ላይ የጥላቻና የጠብ-አጫሪነት ንግግር መለጠፍና አመፅ ማነሳሳት ሀገርን ማፍቀር ሊሆን አይችልም።--"

              አሁን  አሁን ለዓመታት  ችላ ብለን የተውናቸው ኢትዮጵያዊነት፣ የአንድነትና የአብሮነት ስሜቶች እያገገሙ ይመስላሉ፡፡ ዛሬ በጥቂቱ ስለ ሐገር ፍቅር ልናወጋ ነው፡፡ በርግጥ ስለ ሐገር ፍቅር ብዙ ተፅፏል፡፡ ብዙ ፊልም  ተሠርቷል፡፡ ብዙ ትያትር፣ ብዙ ትንግርት ተነግሯል፡፡ በዓለም ዙሪያ በርካታ ተፅእኖ ፈጣሪዎች፣ ለምሳሌ የአሜሪካው ጆን  ኤፍ ኬኒዲ፣ የእንግሊዙ ዊንስተን ቸርችል፣ የቬትናሙ ሆቺ- ሚን ተናገሩ ወይም አደረጉ የሚባሉት ነገሮች ከዘመን - ዘመን  እየተነገሩ አሁን ድረስ ዘልቀዋል፡፡ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት  ቀዩ ጦር ‹‹የአባት  ሐገርን  ማዳን››  ገድል  ተነግሮ  የሚያልቅ  አይደለም፡፡  ወደ ሐገራችን  ስንመለስ  የአፄ ቴዎድሮስ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ የኮሎኔል መንግሥቱ  ኃይለማርያም፣ አሁን  ደግሞ  የጠ/ሚኒስትር  ዐቢይ  አሕመድ  የሐገር  ፍቅር  ሞልቶ  እየፈሰሰ  ሁላችንንም  ሲያጥለቀልቀን  አይተናል፤ አሁንም  እያየን  ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ እኛ  ኢትዮጵያዊያን  የራሳችን  ስኬቶች  ሰለባ የሆንን  ሕዝብ  ነን፡፡  እንዲህ የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ቀደምት  ሥልጣኔያችንንና ታሪካችንን እያወሳንና  በግብዝነት እየተመጻደቅን፣ የጀመርነውን ማስቀጠል  አቅቶን፣ ዓለምን ረስተን፣ ዓለምም  እኛን ረስቶ መቀመጥ ከሚገባን ቦታ ተንሸራተን  በመውረድ፣  ከዝቅተኛው  እርከን  ላይ በመገኘታችን  ነው።  እርግጥ  ነው - እኛ  ኢትዮጵያዊያን  እልኸኛና   ለነፃነታችን  ቀናዒ ህዝብ  ነን፡፡
የኢትዮጵያ   የቁርጥ  ቀን  ልጆች  በከፈሉት   መስዋእትነት፣ መላው  አፍሪካና  እስያ   በቅኝ  አገዛዝ  ለዘመናት  ሲማቅቁ፣  እኛ  ነፃነታችንን  አስከብረን  መዝለቃችን ብቻ ሳይሆን፤ ለነጻነት በሚደረገው ትግል አርአያና ተምሳሌት ሆነን ቆይተናል፡፡
በዚህች አጭር መጣጥፍ ስለ ሐገር ፍቅር  የማይጨበጥ ንድፈ-ሃሳባዊ ትንተና ለመስጠት  አይቃጣኝም፡፡
የመጣጥፏ  ዋና  ዓላማ  የአሁኑ  ዘመን  ኢትዮጵያዊያን የሐገር  ፍቅርን እንዴት  ይረዱታል?  እንዴትስ  ይተገብሩታል? የሚለውን  ጉዳይ በማንሳት ትንሽ  ሃሳቦችን   በማንሸራሸር  ውይይት ለመቀስቀስ  ነው፡፡  የሐገር  ፍቅር የማይጨበጥ ረቂቅ ነገር ሳይሆን፤ የሚታይ፣ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ፤ በአመለካከታችን፣ በአኗኗራችን፣ በዕለት-ተዕለት ምግባራችን ሁሉ  ሊገለፅ የሚችል ምሥጢራዊ  ኃይል ነው፡፡
በአንድ ወቅት “የኢትዮጵያዊያን የሐገር ፍቅር  በድመት ፍቅር ይመሰላል” የሚል ነገር ማንበቤን  አስታውሳለሁ፡፡ ድመት  ስለ ልጆቿ ያላት ፍቅር ቅጥ ከማጣቱ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ትበላቸዋለች። ድመት ልጅዋን የምትበላው ለሌላ ተቀናቃኝ ጥላ ላለመሄድ ወይም ከአደጋ ለመጠበቅ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አዎ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያንም  እንደ ድመቷ ሐገራችንን እየበላናት የሚያስመስሉ በርካታ ሁኔታዎችን መታዘብ ይቻላል፡፡ መጥኔ! ኢትዮጵያ ግን እያገላበጥን እየጋጥናትም አሁንም ድረስ አለች፡፡ ሐገራችንን እንደ ፍልፈል መቦርቦራችንን ከቀጠልን ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፋት ሐገር አፅሟ የቀረ፣ በድህነት የተቆራመደችና ልጆቿ እርስ በእርስ የሚናከሱባት የመሆን ዕድሏ ከፍተኛ ነው። ይሄን የምለው ጨለምተኛ ሆኜ ሳይሆን እውነቱን መነጋገር ይጠቅመናል ብዬ ስለማምን ብቻ ነው፡፡
የሐገር ፍቅር ሲባል ወንዙን፣ ተራራውን ወይም ባሕላዊ ምግቡን መናፈቅ ብቻ አይደለም። በየጊዜው የተነሱና አሁንም ያሉ የኪነ-ጥበብ፣ የሥነ-ጽሁፍ፣ የሣይንስና ምርምር ሰዎቻችን፤ እንዲሁም አትሌቶቻችን፣ ዲፕሎማቶቻችንና ሌሎችም ያልጠቀስናችው የሐገር ፍቅር በተግባር ሲገለፅ ምን እንደሚመስል አሳይተውናል፡፡
እውነተኛ  የሐገር  ፍቅር ማለት፡-
የራስ  የሆነን ሁሉ  ከማጥላላትና  ማንቋሸሽ  መቆጠብ፤
በሐገር  ምርት  መኩራትና  መጠቀም፤
ከባሕል  ወረራ ራስን  መከላከልና ሐገራዊ እሴቶችን መንከባከብ፤
የመንግሥትና  የሕዝብ  ንብረት ላይ ጉዳት ከማድረስ መቆጠብ፤
ተፈጥሮን ለመንከባከብ፣ የማህበረሰቡን የጋራ ጥቅምና  ደህንነትን  ለማስጠበቅ፣
 እንዲሁም ለከተማውና  ለሐገር  ውበትና  ገፅታ  ታስበው  የተዘረጉ/የተቋቋሙ መሠረተ  ልማቶችን፣ ተቋሞችን፣ ወ. ዘ. ተ በግዴለሽነት  ከማበላሸት  መታቀብ፤
“ለእኔ  ብቻ”  የሚለውን  የግለኝነት  ስሜት ገታ አድርጐ  የጋራ ጥቅምን  ማስቀደም፤ እንዲሁም ወገኔ  የምንለውን  ሌላውን ኢትዮጵያዊ  ዜጋ  ማክበርና  መብትና  ጥቅሙን  አለመጋፋት፣ በስሜት  ስንታወር ታላቋንና በሩቅ  የምትታየውን  ኢትዮጵያን  ማሰብና  ማስቀደም፤
በተሰማራንበት የሥራ መስክ ሳንለግም፣ ሳንሸቅብ፣ ሳናስመስል፣ አቅምና ችሎታችን በፈቀደ  መጠን ሃላፊነታችንን  መወጣት፤
በበጐ ፈቃድ በተለያዩ አካባቢያዊ፣ ማህበረሰባዊና ሐገራዊ  ጉዳዮች  ላይ በሃላፊነትና   በያገባኛል ስሜት መሳተፍ (የመሳተፊያ  ሜዳው ቢጠብም) ወ.ዘ.ተ ከብዙ  ጥቂቶቹ  ናቸው፡፡
እነዚህን ነገሮች በግለሰብ ደረጃም በቡድንም  የመተግበሩ ነገር ምን ያህል ተሳክቶልናል? ሁላችንም ይህን ጥያቄ ለራሳችን አቅርበን መመለስ  ይኖርብናል። ከዚህ አንፃር ጥቂት ማሳያዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል። (እዚህ ላይ ለማሳያ የምንጠቃቅሳቸው ጉዳዮች  ሁሉንም ሰው የሚመለከቱ እንዳልሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡) አሁንም  ድረስ በተሠማሩበት መስክ - ለዚያውም  ብዙ ባልተመቻቸ  ሁኔታ ሐገራቸውን  በቅንነትና በሃላፊነት  መንፈስ ለማገልገል ደፋ ቀና  የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በርካቶች ናቸው፡፡ ፈጣሪ የዚህ አይነቶቹን  ያብዛልን፡፡
ለማሳያነት ከተመረጡት መካከል የጐላ የሥነ-ምግባር ጉድለት ከሚስተዋልባቸውና የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ከሚመዘበርባቸው መስኮች  አንዱና ምናልባትም ዋንኛው የምህንድስናውና የኮንስትራክሽን  ዘርፍ ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄዱ የመንገድና የሕንፃ ግንባታ ሥራዎችን ማስተዋል በቂ ነው፡፡ መጀመር እንጂ መጨረስ የማይሳካልን እስኪመስል ድረስ መንገዶቻችን በተዘጋጀላቸው ዲዛይን መሠረት በአግባቡ ሳይጠናቀቁ ተዝረክርከው ማየት በጣም የተለመደ ነገር ነው፡፡ ተጠናቀቁ የሚባሉትም ቢሆኑ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ባለመሆኑ ተሠርተው ከመጠናቀቃቸው መፈራረስ ይጀምራሉ፡፡ የመንግሥት ሕንፃዎችን አጨራረስ ካስተዋልን ተመሳሳይ ሁኔታዎችን መታዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ሥራ ተቋራጮች ይህን ሲያደርጉ፣ አማካሪ መሐንዲሶችም ለእንደዚህ ዓይነት ሃላፊነት ለጐደለው አፈፃፀም የሐሰት ምሥክርነት በመስጠት ክፍያ እንዲፈፀም ሲያደርጉ ከተማቸው አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ትዝ ትላቸው ይሆን? ሠርተው መበልፀግ የቻሉት በድሃዋ ኢትዮጵያ መሆኑን ይገነዘቡ ይሆን? መሐንዲስና ምሕንድስና ከተማን፣ ሐገርን ይገነባል፤ እንዲሁም አሁን  እንደምናየው ሃገርንም  ይበላል፡፡
ፊታችንን ወደ ንግዱ ዘርፍ እናዙር፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያልተገባ ትርፍ ለማጋበስ በድሀው ዜጋ ላይ የሚረማመድ፣ ግብር  የሚደብቅ፣ እንዲያም ሲል በወገኖቹ ሕይወት ላይ ዘላቂ ጉዳት  ሊያስከትሉ የሚችሉ ባዕድ ነገሮችን እያቀላቀለ ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርብ ነጋዴስ ምን ሊባል ነው? ባለ ሐብት ልትሉት ትችላላችሁ፤ ግን  በእርግጠኝነት  ሐገር ወዳድ  ሊባል  አይችልም፡፡
ትውልድን የመቅረፅ  የተከበረ ሃላፊነት የተሸከመ መምህር፤ ሥራውን በብቃትና በሃላፊነት ስሜት ካላከናወነ፣ ሐኪሙ ጐስቋላ ታካሚዎቹን  ካንጓጠጠ ወይም ከሙያው ሥነ-ምግባር ውጪ የሆነ ነገር ከፈፀመ  የሁለቱም የሐገር ፍቅር  ጉዳይ ጥያቄ  ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው፡፡ የሀገር ፍቅር ስንል በዋናነት ህዝብንና ወገንን ማለታችን ስለሆነ ነዋ፡፡
የመንግሥት ሠራተኛውስ  ቢሆን? የመንግሥትን  የሥራ ሰዓት በየምክንያቱ ከሸራረፈ፣ ደሞዝ ለሚቆርጥለት ሕዝብ ቅንና ቀልጣፋ አገልግሎት  ካልሰጠ፣ እንዴት ሆኖ ሐገሬን እወዳለሁ ሊል  ይችላል?
 ባለሥልጣኑማ እንደውም የአንበሳውን  ድርሻ  ነው  መውሰድ  ያለበት፡፡ ያ ሳይሆን  ቀርቶ  ባለሥልጣኖቻችን የሕዝብን መብት የማያከብሩ፣ የሐገርን ብሔራዊ ጥቅም  ለድርድር የሚያቀርቡ ሆነው ሲገኙ ቋንቋው  ተቀይሮ  የሐገር ፍቅር  ሳይሆን የሐገር  ክህደት ይሆናል፡፡
አሽከርካሪውስ ቢሆን? ለሁላችንም  ደህንነት ሲባል የተቀመጡ  የመንገድ  ምልክቶችን ወይም  የከተማውን  ውበት  ለመጠበቅ የተዘጋጁ  ቁሳቁሶችን  በግዴለሽነት  የሚያወድሙ የመኪና አሽከርካሪዎች ቁጥር ጥቂት  አይደለም፡፡ መንገድ  የጋራ መገልገያ  መሆኑን ዘንግተው ብቻቸውን ሊቆጣጠሩት  የሚዳዳቸውም የዚያኑ ያህል በርካቶች ናቸው፡፡ አሁን አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ሕግ አክብሮ በመተሳሰብ መኪና ለማሽከርከር መሞከር እንደ ሞኝነት የሚቆጠርበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል፡፡ ይህ አዝማሚያ የአስተዳደግ ችግር ነው፣ ወይም ተራ የሥነ-ምግባር ጉድለት ነው ብለን የምናልፈው ሳይሆን ከፍተኛ የሞራል ዝቅተትን የሚያመለክት፣ በውጤቱም ሐገራዊ አንደምታ ያለው ነው፡፡ መነሻውም ዕብሪት፣ ደንታ-ቢስነትና ለሌላው ሰው፣ አንዳንድ ጊዜ ለራስ ሕይወትም  ጭምር ዋጋ አለመስጠት ነው። ጥሩ ዜጋ የሐገርን ሐብት ይጠብቃል፣ ሌላውን ወገኑን ያከብራል፣ ለራሱና ለወገኖቹ ሕይወት ዋጋ ይሰጣል፡፡
ጉዳይ ለማስፈፀም ወይም አገልግሎት ፈልገው ወደ አንድ መሥሪያ ቤት ሄደው፣ ወይም ነዳጅ ለመሙላት፣ ወይም ዳቦ ለመግዛት ወረፋ መጠበቅ ግድ ሆኖብዎት ያውቃል? ከፊታቸው የተሰለፈውን ሰው ረምርመው በማለፍ ለመገልገል የሚሽቀዳደሙ ሰዎችን  አላስተዋላችሁም? እነዚህ በአጠገባቸው ላለው ሰው ደንታ የሌላቸው፣ በራሳቸውና በራሳቸው ጥቅም ብቻ  የታወሩ  ናቸው፡፡ እናም ሐገር ወዳድ ፈጽሞ ሊባሉ አይችሉም፡፡
ጋዜጠኞችና ጦማሪዎችንም በተመሳሳይ መነፅር ማየት ይቻላል፡፡ በአጐብዳጅነት ሕዝብን በተዛባ መረጃ መደለል፣ ሌላኛውን ወገን ጥላሸት መቀባትና ስም ማጥፋት፣ በማህበራዊ ድረ-ገፅ ላይ የጥላቻና የጠብ-አጫሪነት ንግግር መለጠፍና አመፅ ማነሳሳት ሀገርን ማፍቀር ሊሆን አይችልም።
የፖለቲካ አመራሩ ለውጡንና ተሃድሶውን የገፋበት ይመስላል፡፡ ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ገና ብዙ መሠራት  ያለበት  ነገር  ቢኖርም ጅምሩ የሚያበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን ለውጡና ሽግግሩ አድማሱ ሰፍቶ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሐገር  ደረጃ እውን ሆኖ መታየት አለበት፡፡
በእርግጥ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ማስፈለግ ብቻ ሣይሆን በፍጥነት መለወጥ ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን የምንለውጠው የትኛውን ነው? እንዴትና መቼ ነው የምንለውጠው? የለውጡ ዋና ተዋናዮች እነማን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ፤ብርቅዬዎቹ ማህበራዊ እሴቶቻችን በደረሰባቸው ያላቋረጠ ጥቃት ተሸርሽረዋል፡፡ ችግሩ ወይ እነርሱን አላስቀጠልንም ወይም በሌሎች በተሻሉ እሴቶች አልተካናቸውም፡፡
እውነት ለመናገር፤ እርስ በርስ መከባበር እየራቀን ሄዷል፣ ጥራዝ - ነጠቅነት፣ ሁሉን ነገር በአቋራጭ የማግኘት ብልጣ-ብልጥነትና ግለኝነት ነግሰው፣ ወደ አጠቃላይ የሞራል ዝቅጠት እየወሰዱን ነው፡፡ ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣቱ ላይ ሀገራዊ መግባባት ከተፈጠረ ለውጡን እንዴትና በምን አግባብ እናስኪደው የሚለው ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ ነው። በአንድ ነገር ላይ መግባባት ይኖርብናል፤ ሁሉም ለውጦች በመንግሥት ብቻ ሊመጡ አይችሉም፤ ሁሉም የድርሻውን መወጣት  ይኖርበታል፡፡ የሐገር ፍቅር ማለትም ሌላ ሳይሆን ይሄ ይመስለኛል፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል  አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 5416 times