Tuesday, 30 November 2021 00:00

በዘመነ ኮሮና 245 ሚ. የአለማችን ሴቶች ጥቃት እንደደረሰባቸው ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪካ በ5 ዓመታት፣ 21 ሺ ህጻናት ወደ ውትድርና ገብተዋል


             ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአለማቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች እንዲባባሱ ማድረጉንና ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በመላው አለም ከ15 አመት እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ልጃገረዶችና ሴቶች የተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ ሆነዋል ተብሎ እንደሚገመት ዩኤን ውሜን የተባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋም ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ከአለማችን አገራት መካከል በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ለተለያዩ ጥቃቶች የተጋለጡት በኬንያ መሆኑን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ በአገሪቱ 80 በመቶ ያህል ሴቶች ለጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
ተቋሙ በሪፖርቱ እንዳለው በ13 የአለማችን አገራት ባደረገው ጥናት፣ ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው ሴቶች መካከል ግማሽ የሚሆኑት በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በራሳቸው ወይም በሌላ በሚያውቋቸው ሴቶች ላይ የጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ሩብ ያህሉ ሴቶች ደግሞ ከኮሮና በኋላ ከቤታቸው መውጣት በእጅጉ እንደሚያስፈራቸውና ለደህንነታቸው እንደሚሰጉ መናገራቸውን የጠቆመው ጥናቱ፤ በቤት ውስጥም ቢሆን የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚያጋጥሟቸው መግለጻቸውን አመልክቷል፡፡
በጥናቱ ከተካተቱት ሴቶች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጾታዊ ትንኮሳዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመሩ መናገራቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ወረርሽኙ ስራ አጥነት፣ የምግብ ዋስትናና የገንዘብ ችግርን የመሳሰሉ ፈተናዎችን እንዳባባሰባቸው መናገራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በምዕራባዊና ማዕከላዊ አፍሪካ በሚገኙ ግጭት የተቀሰቀሰባቸው አገራት ባለፉት 5 አመታት ከ21 ሺህ በላይ ህጻናት በመንግስት ሃይሎችና በታጣቂ ቡድኖች ተመልምለው ወደ ውትድርና እንዲገቡ መደረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ባለፈው ማክሰኞ ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው፣ እ.ኤ.አ ከ2016 አንስቶ በአለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህጻናት ወደ ውትድርና እንዲገቡ የተደረጉት በእነዚህ አገራት ውስጥ ሲሆን፣ በአገራቱ ከ2ሺህ 200 በላይ ህጻናት የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች መሆናቸውንም ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡


Read 8207 times