Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 13:46

የመለስን የአፍሪካ ቃል አቀባይነት ማን ይተካዋል?

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮችና ውይይቶች ሲነሱ በቅርቡ  ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይታወሳሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም (UNEP) በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ዜና የተሰማውን ሀዘን ገልፃ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በተነሱ አጀንዳዎችና የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማስተዋወቅ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ታላቅ እንደነበር መስክሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተባበሩት መንግስታት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በሚያደርገው ምክክር፤ አፍሪካ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆን  በተጫወቱት የመሪነት ሚና፣ የአፍሪካ መንግስታት አህጉሪቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚኖራትን የጋራ አቋም ለማራመድ የተቋቋመውን ኮሚቴ በመምራት ባበረከቱት የጎላ አስተዋፅኦና በአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካ ድምጽ  በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት እንዲኖረው ባበረከቱት የቅስቀሳና የማስተባበር ተግባር በአርአያነት የሚወሳ ስራ ማከናወናቸውንም ድርጅቱ ገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን “የአካባቢ ጥበቃ ሻምፒዮን ነበሩ” ያለው ዩኔፕ አፍሪካ፤ በዝቅተኛ የካርቦን ልቀት፣ የተፈጥሮ ሀብትን አብቃቅቶ በመጠቀምና ዘላቂ ዕድገትን ለማምጣት በሚያስችለው የአረንጔዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊነት ላይ ጽኑ አቋም በማራመድ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የሚፈጠር ተጽእኖን ለመቋቋም በሚያስችለው የአረንጔዴ ልማት ስትራቴጂ እንድትንቀሳቀስ በመጣር፣ አገሪቱን በ2025 እ.ኤ.አ  ከካርቦን ነፃ የሆነችና መካከለኛ ገቢ ያላት አገር የምትሆንበትን መሠረት እንደጣሉም ዩኔፕ አፈሪካ አመልክቷል፡፡

በመለስ ዜናዊ ብልህ አመራር  ቢሊዮን ዛፎች በመትከል ዘመቻ ላይ ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና መጫወቷን በመጥቀስም ከ2007 እ.ኤ.አ ወዲህ በአገሪቱ 1.7 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞች መተከላቸውን ጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይ ዘመቻ በመላው ዓለም 12.6 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞች መተከላቸውንና የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ከህንድና ከቻይና ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፈ ባንኪ ሙንን የሚያማክረውና ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን በመደራደር ላይ ያለውን ቡድን ተጣምረው በሊቀመንበርነት እየመሩ የነበሩት የኖርዌዩ ጠቅላይ ሚኒስትር የንስ ስቶልትንበርግ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ የአማካሪ ቡድኑ ሁለቱን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጨምሮ የሪፐብሊክ ኦፍ ጊኒ ፕሬዚዳንት ባሃራት ጃግዴዮንን፣ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮችን፤ የታላላቅ ባንኮች ተወካዮችና ዲፕሎማቶችን ያካተተ ነበር፡፡ አሁን ይህን ዓለምአቀፍ ህብረት በሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ማጣቱ ክፍተት ፈጥሮበታል እየተባለ ነው፡፡አቶ መለስ kxmT ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ደርባን ተደርጎ በነበረው ዓለምአቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፍረንስ (ኮፕ17) ላይ ሲናገሩ፤ ድሃና በማደግ ላይ ያሉ የዓለም አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚጠይቁት የገንዘብ ድጋፍ ዋናው የማይቀለበስ የትግል ትኩረት ሆኖ እንዲቀጥል አሳስበው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት ዓመት በፊት በዴንማርክ ኮፐንሃገን የዓለም መንግስታት ስለሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ የገቡትን ቃል አለማክበራቸው እንደሚያሳስባቸው ሲገልፁም፤ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ለሚገጥማት ቸግር የምትጠይቀው ድጋፍ ተገቢነት የሚመለከታቸው ሁሉ በቅጡ እንዲገነዘቡና የምታደርገውን ጥረት በህብረት መቀጠል እንዳለባትም መናገራቸው ይታወሳል፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚሁ መልእክታቸው፤ አፍሪካ የኪዬቶ ስምምነት እንዲሻሻል እና እንዲለወጥ ድጋፍ እንደምትሰጥም ተናግረው ነበር፡፡

ከሰሞኑ በታይላንድ ባንኮክ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያተኮረ የምክክር የተካሄደ ተከናወነ ሲሆን መድረኩ ከ2 ወራት በኋላ በኳታር ዶሃ ለሚደረግ ዓለምአቀፍ ስብሰባ መግባባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ተግባራት እንደተከናወኑበት የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት በ1997 እ.ኤ.አ በዓለም መንግስታት የተፈረመው የኪዮቶ ፕሮቶኮል እንዲሻሻልና እንዲጠናከር ባለው ፍላጐት መሠረት በስፋት መንቀሳቀሱንም ቀጥሏል፡፡ የኪዮቶ ስምምነትን በህግ አስገዳጅ በሆነ ድንጋጌ የመቀየር ሃሳብ ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ በአየር ለውጥ ላይ አዲስ ዓለም አቀፍ ስምምነት በ2015 እ.ኤ.አ ፀድቆ በ2020 እ.ኤ.አ ተግባራዊ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡

በሁለት ወር ውስጥ በኳታር ዶሃ በሚደረገው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፍረንስ (ኮፕ 18) ላይ ምክክርና ድርድር ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት ዋናዎቹ አጀንዳዎች  በ1997 እ.ኤ.አ ላይ በ192 የዓለም አገራት የፀደቀውና በ2012 መገባደኛ ላይ ቀነ ገደቡ የሚያበቃው የኪዮቶ ስምምነት በህግ አስገዳጅ ድንጋጌ እንዲቀየር ማነሳሳትን ያካትታል፡፡ አምና በደቡብ አፍሪካ ደርባን በተደረገ የኮፕ 17 የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ ደሃና በማደግ ላይ ያሉ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስና ለመቋቋም ከሃብታም የዓለም መንግስታት ሊያገኙ የሚገባቸው የገንዘብ ድጋፍ ዋንኛው አጀንዳ ነበር በዓለም አቀፍ ንቅናቄው የገንዘብ ድጋፉ እስከ 2020 እ.ኤ.አ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር እንደደርስ ይፈለጋል፡ ይሄው አጀንዳም ከኮፕ 18 ትኩረቶች ዋንኛው ነው፡፡

የዓለም አየር ንብረት ለውጥን  ጉዳት ለመቀነስ እንደዋንኛ መፍትሄ የተወሰደው የመንግስታት የገንዘብ ድጋፍ  የሚገኝ ከሆነ እንዴት ሊተዳደር ይችላል በሚለው ጉዳይም በርካታ ጥያቄዎች በዶሃ የኮፕ18 ኮንፍረንስ ላይ እንደሚያከራክሩም ይጠበቃል፡፡ ገንዘቡ የት ይቀመጥ፤ ማን ያንቀሳቅሰው፤ እንዴት ይንቀሳቀስ እና  ከየት ይገኛል የሚሉት ጥያቄዎች በኮንፍረንሱ ላይ ተነስተው  መግባባት ላይ እንዲደረስባቸው ማድረግም ከባድ ፈተና እንደሚሆን እየተገለፀ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአየር ንብረት ለውጥ ዙርያ በመላው ዓለም በተለያዩ ስፍራዎች፤ የምክክር ቡድኖችና ቦርዶች ለዓመታት የሚደረጉ ኮንፍረንሶች በጉዳዩ ላይ ለሚደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት ብዙም ውጤት አለማሳየታቸው በኮፕ 18 ኮንፍረንስ ላይ ትኩረት የሚስብ ይሆናል፡፡

አንዳንድ መረጃዎች፤ በአየር ንብረት ለውጥ ዙርያ ከ50 በላይ አጀንዳዎች ድርድር እየተደረገባቸው እንደሚገኙ ያመለክታሉ፡፡ ላለፉት 10 አመታት አፍሪካ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ዙርያ የሚኖራትን አቋምና የሚገባትን ድጋፍ በመደራደርና በማንፀባረቅ ጉልህ ሚና የተወጡት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ በህልፈታቸው የተነሳ በኮፕ 18 አለመኖራቸው ወደ ኋላ የመጎተት ተፅእኖ መፍጠሩ የማይቀር ይሆናል ተብሏል፡

የዓለም መንግስታት የኪዮቶን ስምምነት ለመተካት የሚያስችል አዲስ ውሳኔ ለማድረግ ማመንታታቸው ሰፊ ትግል ያስፈልገዋል፡፡ በከፊል ስምምነት ተደርጎበት በ1977 የፀደቀው የኪዮቶ ስምምነት፤ ሃብታም አገራት የካርቦን ልቀታቸውን ከ1990-2012 ድረስ በ5.2 በመቶ እንዲቀንሱ የሚያሳስብ ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ የኪዮቶን ስምምነት ለመፈረም እያንገራገሩ ከቆዩ አገሮች ጋር በተደረጉ ድርድሮችና ውይይቶች፣ የአፍሪካን ጉዳዮች በማንሳት ተሟጋች ነበሩ፡፡ የእነዚያን አገሮች አቋም በመንቀፍም አፍሪካ ያለ ሐጥያቷ ለደረሰባት ጉዳት የገንዘብ ካሳ እንድታገኝ ሃሳብ ያቀረቡ ከመሆናቸውም በላይ ይህን አቋማቸውን በዴንማርክ ኮፐንሃገን በተደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ አንፀባርቀዋል፡፡

በአስር የአፍሪካ መሪዎች የሚመራው ቡድን ውስጥ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሳተፍ ሲሆን  አፍሪካን በመወከል የሚደራደረው የመለስ ተተኪ በመጪው አፍሪካ ህብረት ጉባኤ ይፀድቃል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ኬኒያ እና ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያን ሚና ለመተካት መዘጋጀታቸው እየተነገረ ነው፡፡መለስ ዜናዊ ከላይ በተዘረዘሩ  እና ባልተዘረዘሩ ከአየር ንብረት    ለውጥ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች አፍሪካን  በመወከል አጀንዳ የሚያቀርቡ፤ የሚከራከሩና የሚደራደሩ ነበሩ፡፡ አፍሪካ ከችግሩ አሳሳቢነት የተነሳ ይህን አንገብጋቢ ጉዳይ ይዞ የሚሟገትላት ተተኪ ትፈልጋለች፡፡ ዓለምም ተተኪውን እየጠበቀ ነው፡፡ሰሞኑን በተካሄደው ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፓውል ካጋሜ መለስን በመተካት አፍሪካን በመወከል ቻይና ተገኝተዋል፡፡

 

 

Read 47920 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 15:38