Sunday, 28 November 2021 00:00

ቀና በል!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጨቅላ እኔነቴ_እግሩ ተወላክፎ
ሰው ፍለጋ ወጣ_ባዶ ልቡን አቅፎ
በእውር ድንበር ጉዞ_ባዶ እግርን ይዞ
ሰው ወዴት ይሄዳል_ልቡን ተገንዞ ?
ኮሽ ባለ ቁጥር_ጨርቁን ሜዳ ጥሎ
ሰው እንዴት ይኖራል_ጥላውን አባብሎ?
በፈጠረኝ አፈር_ቆሜ ከጭቃው ላይ
በገዛ ሀገሬ_አቀርቅሬ ብታይ
አጥንቱ ተነስቶ_ከመሬቱ ብቃይ
<ቀና በል> ይለኛል ........................
የአባቴ ደም ሥጋ_ቆሞ ከአደባባይ!
አቀርቅሮ መኖር_ተጋብቶ ከስቃይ
እንደው ለመሆኑስ_መች ያምራል በኔ ላይ?
ያልለመደብኝን_መኖር እውነት ሽጦ
አይችልም አንጀቴ ........................
ጠብታ ሊጠጣ_ብርጭቆ ጨብጦ!
እድል ሊያዳልጠኝ
ቀን ገፍቶ ሊጥለኝ
ህላዌነት ጠፍቶ_ወራጅ ወንዝ ሊወስደኝ
ጎርፍ እንደ ደግ ሰው_አጫዉቶ ሊነጥቀኝ
ገደል አፋፋ ጠርቶ_እንላፋ ሲለኝ
በይሁዳ ከንፈር …………..
ሳሩን አየሁ ብዬ_ዝላይ መቼ ሊያምረኝ?
የየኔታ ጥበብ_እንደ እርሳስ ሞርዶ
ምላጭ ያደረገኝ_ገና ጥንት ማልዶ
ሀሞቴ የሚያፈልቅ_እንደ ጫካ ውሃ
ተራራ ነው ልቤ .............................
ባዶ እግሬን ብሆንም_አልምሰልህ ደሃ!
ዳሩ ለነገሩስ ...........
ለጥፍሩ ሳይሳሳ_የሄደ አይናቅም
ባዶ እግር የወጣ ................
እንቅፋቱን ፈርቶ_በእጆቹ አይሄድም!
እናልሽ ሀገሬ ………..
ዙርያሽን ቢከብም_ድቅድቁ ጨ ለማ
ያመንሽው ጨክኖ_ቢረግጥሽ በጫማ
ከንፈርሽ ተሞልቶ_በትንሳኤ ዜማ
ጠላት እያዘነ
እንደ ውብ ጨረቃ
ገና ከፍ ብሎ_በዓለም ላይ ይታያል_የልደትሽ ሻማ!
(ነፃነት አምሳሉ)

Read 1340 times