Saturday, 27 November 2021 13:37

የሽግግር መንግስት እንመሰርታለን በሚሉ ወገኖች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ተላለፈ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(5 votes)

     የፀጥታ ሃይሎችን አልባሳት በምንም ሁኔታ ለብሶ መገኘት በህግ ተከልክሏል
                          
              አሁን በአገሪቱ እየተከናወነ ያለውን የሕልውና ጦርነት አጋጣሚ በመጠቀም ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ከሚፈቅደው ውጪ የሽግግር መንግስት ወይንም ህገ-ወጥ ቅርፅ ያለው መንግስት እንመሰርታለን በሚል እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ወገኖች ላይ የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አስታውቋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጀመሩ ሰራዎችን ለማጠናከርና እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዙ አራት ትዕዛዞችን ያስተላለፈ ሲሆን ከእነዚህ ትዕዛዞች መካከል በህገ-ወጥ መንገድ ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ የሽግግር መንግስት እንመሰርታለን በማለት ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አካላት ላይ የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ  እንዲወስዱ ትዕዛዝ ተላልፏል።
ዕዙ ከዚህ በተጨማሪም የፀጥታ አካላትን መለዮ ለብሶ መገኘትንም በህግ ከልክሏል። ከህግና ስርዓት ውጪ የመለዮ ለባሾችን የደንብ ልብስ ለብሶ መገኘት  የተልዕኮ አፈጻጸሙን እያወከ እንደሚገኝ ያመለከተው ዕዙ፤ ከዚህ በኋላ በማንኛውም ሁኔታ ቦታና ጊዜ  የመከላከያ ሰራዊትን፣ የፌደራል ፖሊስን፣ የክልል ልዩ ሃይሎችንና የመደበኛ ፖሊስ ዩኒፎርሞችን የፀጥታ አካላት አባል ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለብሶ መገኘት እንደማይችልና ለብሶ በተገኘ ሰው ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ ዕዙ አስጠንቅቋል።
 የሃሳብ ነጻነትን ሰበብ በማድረግ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የሽብር ቡድኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚደግፉ መረጃዎችን በማውጣት በህልውና ዘመቻው ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያሳሰበው የዕዙ መግለጫ፤ ይህንን ማሳሰቢያ ተግባራዊ በማያደርጉ አካላት ላይ የፀጥታ ሃይሎች ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስዱ አዟል።
 ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውጤቶችን በየትኛውም የመገናኛ ዘዴ ማሰራጨት መከልከሉን ያመለከተው መግለጫው፤ በየግንባሩ የሚገኙ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ከተሰጣቸው ስምሪትና ተልዕኮ ውጪ ማንኛውንም ወታደራዊ  እንቅስቃሴዎች፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችና ውጤቶችን  የሚመለከቱ መግለጫዎችን መስጠት የተከለከለ መሆኑን አስታውቋል።
በተያያዘ ዜና፤ አሸባሪውን የህውሃት ቡድን የሚደግፉና የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስትን ከሥልጣን በማውረድ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ሚስጢራዊ ስብሰባ በዙም መካሄዱ ተጋልጧል። በዋሽንግተን ዲሲ በዙም ተካሄደ በተባለው በዚህ ስብሰባ  ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅንና  የቀድሞው የኢሲኤክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር እሌኒ ገረመውን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች መካፈላቸው ታውቋል።
በፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ ይመራ የነበረው ይኸው ምስጢራዊ ስብሰባ፤ ፕሮፌሰር ጥላሁን በየነ፣ አምባሳደር በቀለ ገለታ፣ ዶ/ር ታደሰ  ውሂብና ወ/ሪት ኩለኔ ጃለታ እንዲሁም ሁለት ምዕራባውያን ዲፕሎማቶችን ያካተተ ነበር።
ተሰብሳቢዎቹ በዚሁ ሚስጢራዊ ስብሰባቸው በድርድርም ሆነ በየትኛውም መንገድ አሸባሪውን የህውሃት ቡድን የሚደግፍ መንግስት መቋቋም እንዳለበት መክረዋል። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በማውረድ ሌላ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ይኖርብናል በሚል ጉዳይ ላይ መወያየታቸውና ከስምምነት ላይ መድረሳቸውም ታውቋል። ተሰብሳቢዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ለማስቆም እንደሚችሉና የአፍሪካ ህብረት የወከላቸው ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ በሚፈልጉት መንገድ እየተንቀሳቀሱ እንዳልሆነም መክረዋል። ይህ ሚስጢራዊ ስብሰባ  መጋለጡን ተከትሎ መንግስት ባሳለፈው ውሳኔ፣ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም በሚል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የጸጥታ አካላት እርምጃ እንዲወስዱ አዝዟል።

Read 11956 times