Saturday, 27 November 2021 13:34

#ከምንም ምድራዊ ጉዳይ በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ሃገራችንን ለማዳን፣ ኢትዮጵያችንን ለመጠበቅ ነው!;

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ ሀገራችን በውስጥና በውጪ ጠላቶች የተደቀነባትን አደጋ በጀግኖች ልጆቿ መራር ትግልና መስዋዕትነት በድል እንደምትወጣ ሙሉ እምነት አለው፡፡ ጠላቶቻችን በደማቅ የአሸናፊነት ታሪካችን ብቻ ሳይሆን በብሩህ ተስፋችንም ጭምር ፊታቸው ጠቁሯል በዚህም ዛሬም እንደ አራዊት እርስ በእርስ ሊያናክሱንና ሊያጠፋፉን፤ ማንነታችንንና ክብራችንን ሊያዋርዱ ጦርነት ከፍተውብናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአሸናፊነት የምንቋጨው ጦርነት ላይ ብንሆንም፣ ጦርነቱን ባጠረ ጊዜ አለመጨረስ የሚያስከትልብን ፈተና ከባድ ይሆናል፡፡ የተራዘመ ጦርነት እንደ እሳት ነበልባል ሀገራችንንና ህዝቦቿን ይበላል ለውጭ ጠላቶቻችንን የበረታ ጫና ተጨማሪ ዕድል ይሰጣል፡፡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳቱም እጅግ የበዛ ነው ስለሆነም መላው ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ የህልውና ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ግቡን እንዲመታና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲቋጭ፣ ዛሬ ነገ ሳትሉ የሚጠበቅባችሁን የዜግነት ግዴታ እንደምትወጡ አንጠራጠርም፡፡ የዜግነት ግዴታችንን ስንወጣ የሀገራችን ፖለቲካ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ዘንግተን አይደለም፡፡ ያለን የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለይ በእንዲህ ያለ ጊዜ ለሀገር ህልውና በጋራ መቆሙ ምርጫ የሌለው ግዴታችን በመሆኑ ነው፡፡ ሀገሬንና ህዝቤን እወዳለሁ የሚሉ ሁሉ በተግባር የሚፈተኑበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ሲተቹና አስተያያት ሲሰጡ የነበሩ ሁሉ የተናገሩትን ፈፅመው ሀቀኞች መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ቀን ደርሷል፡፡ ጥሬው ከብስሉ የሚለይበት፣ ከንግግር ያለፈ ተጨባጭ ሥራ ሰርተን በታሪክ ፊት በእውነት የምንመዘንበት የታሪክ አጋጣሚ ከእጃችን ላይ ነው፡፡ ኢዜማ ለመላው የፓርቲው አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፤ በጋራ ሊያጠፋን የመጣውን ኃይል በህብረት ለመደምሰስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ የምትገኙ አባላትና ደጋፊዎች፤ ይህን ዘመቻ ሊያጠናከርና ሊደገፍ በሚችል አደረጃጀት ውስጥ በመቀላቀል፣ በገንዘብና በጉልበት ተግባራዊ ድጋፍ በማደረግ እውነተኛ ደጀን በመሆን፤ እንዲሁም የአካባቢያችንን ፀጥታ በንቃት በመጠበቅና አጥፊዎችን በአግባቡ ለሕግ በማቅረብ ብሎም ከተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ ራሳችንን በመጠበቅ፣ ይህን የፈተና ወቅት በፅናት እንድንወጣ አደራ እንላለን፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከፊት ሆነው እየተዋደቁ ያሉ ጀግኖችን ሁሉ በርቱ ታሪካችን ደማቅ፣ ድላችንም አንፀባራቂ እንደሚሆን አትጠራጠሩ እያልን፣  ወደ ግንባር የዘመቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለጉዳዩ ክብደት የሰጡት ትኩረት ተገቢ ነው እያልን፣ በዚህ ሂደት ውስጥ የጸጥታውን መዋቅር በአንድ ወጥ አመራር አሰልፈው የሀገራችንን ድል ያፋጥኑታል ብለን እንተማመናለን፡፡ ስለዚህም ወጥ በሆነ የዕዝ ሰንሰለትና በተጠና ሀገር አቀፍ የውጊያ ስልት፣ ሃገራችንን ለመጠበቅ ቆራጦች መሆናችንን እንገልጻለን፡፡ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች፤ በዓለም አደባባይ ተገኝታችሁ ለምትወዷት ሀገራችሁ ሉዓላዊነት እያደረጋችሁ ላለው እጅግ የሚያስመካ ተግባር ኢዜማ ከፍ ያለ ክብር አለው፡፡ አንዳንድ የውጪ ሀገር መንግስታትና ተቋማት የሀገራችን ህልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከት እያደረግን ያለው ተጋድሎ  ላይ እያሳረፉ ያሉትን ያልተገባ ጫና እንዲያቆሙ ድምጻችሁን አሰምታችኋል ፤ ድጋፋችሁን የሚሹ ወገኖቻችሁንም ሳትሰስቱ እየረዳችሁ ነው። ካለንበት ውስብስብ ችግር አንፃር ሲታይ እናት ሀገራችሁ ከመቼውም ጊዜ በላይ የእናንተን አቅምና ድጋፍ አሁንም ትሻለች።  ያለ እናንተ አስተዋፅዖ የተሟላ ድል ሊገኝ እንደማይችል በተግባር ተረድተናል፡፡ ስለሆነም የምዕራባውያንን የተዛባ አመለካከት በማጥራት እንዲሁም ሊፈጠር የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቅረፍ በሚያስችል ደረጃ የተደራጀና ወጥነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ከወትሮው በላቀ ሁኔታ በያላችሁበት የዓለም ጥግ እራሳችሁን እንድታዘጋጁ አደራ እንላለን፡፡
በመጨረሻም ከልዩነቶቻችን፣ አለመግባባቶቻችንና የጎደሉን ነገሮች በፊት ኢትዮጵያ ሃገራችን ትቀድማለች፡፡ በተለይ የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት የሀገራችን ህልውና ቀዳሚ ነው።
የመጣብንን የጋራ ጠላት በጋራ መክተን የሀገረ መንግስቱን ቀጣይነት ካረጋገጥን በኋላ ልዩነቶቻችንን ለመፍታትና ቅሬታዎቻችንን ለማከም በጠረጴዛው ዙሪያ እንቀመጣለን። በዛም ወቅት ሀገራችንን የመፍረስ ስጋት ጫፍ ላይ ያደረሳት የፖለቲካ ስርዓትና አካሄድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዳይመለስ መስራት ሀላፊነታችን ይሆናል፡፡ አሁን ላይ ከምንም ምድራዊ ጉዳይ በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ሃገራችንን ለማዳን፣ ኢትዮጵያችንን ለመጠበቅ ነው! ይህንንም ስናደርግ እንደ ሀገር አብሮ መኖራችንን በማያቆሽሽና የወደፊት አብሮነታችንን በማይጎዳ ሁኔታ እንዲሆን አሁንም አበክረን እናሳስባለን፡፡
አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ አርበኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን ግምት ውስጥ በመክተት፣ የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ህዳር 15 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ አባላትና ደጋፊዎቹ ግንባር ድረስ በመዝመት፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠትና ሌሎችንም ተግባራት በመከወን የሀገርን ህልውና የማረጋገጥ ስራ ለመስራት ውሳኔን አስተላልፏል፡፡


Read 8351 times