Thursday, 25 November 2021 07:06

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ታሪክን እንደ ትምህርት ቤት
                              ጌታሁን ሔራሞ


           ሱከራኖ እ.ኤ.አ. ከ1945-1967 የኢንዶኔዥያ ኮሚኒስት መሪ ነበር፤ ከደች የቅኝ አገዛዝ ማክተም በኋላ የመጀመሪያው የኢንዶኔዥያ ፕሬዚዳንትና የነፃነትም ታጋይም ነበር። ሱከራኖ የለውጥ ረሃብተኛ፣ አብዮተኛና የኢንዶኔዥያ ብሔርተኝነት አቀንቃኝም ነበር። (ከሥር ምስሉ ተቀምጧል)
የወቅቱ 34ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አይዘንሐወርና የሲ.አይ.ኤ. ወኪሎች ሱከራኖን የጎሪጥ ማየት የጀመሩትና እግሮቹንም እሳት ውስጥ ለመክተት የዛቱት በእሱ አዘጋጅነትና ፈር ቀዳጅነት እ.ኤ.አ. በ1955 ዓ.ም ከጃካርታ ደቡብ ምሥራቅ በቅርብ ርቀት በምትገኝ በባንዳንግ ከተማ የተደረገውን ኮንፍረንስ ተከትሎ ነበር፤ ይህን ኮንፍረንስ አሜሪካ በኑፋቄነት መድባ ነበር። ምክንያቷ ደግሞ ይህ ነበር፦ ቀደም ሲል በደቡብ ምሥራቅ እስያ አሜሪካ “SEATO” የሚባል ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጥምረትን አቋቁማ ነበር። ሱከራኖ ፕሬዚዳንት ሆኖ ቤተ መንግስት ከገባ በኋላ ለ”SEATO” ማርከሻነት በገለልተኝነት ዶክተሪን ላይ የተመሠረተ ሌላ የታዳጊ ሀገራትን ኮሚኒስታዊ ተቀናቃኝ ጥምረት ለማቋቋም ቆርጦ ተነሳ። በኮንፍረንሱ 29 ሀገራት ከእስያ፣ ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ ተሳታፊ ነበሩ፤ ፀረ-ቅኝና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ትግሎችን መደገፍ የስብሰባው አንዱም የመወያያ ርዕስ ነበር።
ሱከራኖ የሦስተኛ ዓለም ሀገራትን ጥምረትን ለመመስረት ያደረገው ጥረት በአሜሪካኖቹ አልተወደደለትም፤ ጭራሽ ኮንፍረንሱ ለሲ.አይ.ኤ. ምክትል የፕላን ዳይሬክተር ለሆነው ፍራንክ ዊዝነር ለአሜሪካ መንግስት “I think it’s time we held Sukarno’s feet to the fire” የሚለውን መልዕክት እንዲያስተላልፍ ሰበብ ሆነለት። አሜሪካኖቹ እንደዛቱት የሱከራኖን እግሮች እሳት ውስጥ መጨመር ጀመሩ፤ ተልዕኮአቸውን የሚያስፈፅምላቸውን አማፂ ቡድንን ኢንዶኔዥያ ውስጥ አቋቋሙ። እስከ አፍ ጢሙም አስታጠቁት። ኢንዶኔዥያ የሲ.አይ.ኤ. መፈንጫ ሆነች። የአሜሪካ የጦር አይሮፕላኖች የገበያ ቦታ ሳይቀር ያለ ርህራሄ ደበደቡ። ከብዙ የሲ.አይ.ኤ ጣልቃ ገብ ጥቃቶች በኋላ እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም. የሱኩራኖ መንግስት ላይ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዶ በምትኩ አሻንጉሊቱን ፕሬዚዳንት ሱሃርቶን አሜሪካ ለኢንዶኔዥያ ፕሬዚዳንት አድርጋ ሾመች። በሙያው የሲቪል ኢንጂነሪንግ ዶክተር የሆነው ሱከራኖ፣ በአሜሪካኖች ሴራ ሕልሙ ተጨናገፈበት።
ሀገርን መምራት የሀገራዊ ፖለቲካ ዕውቀትን ብቻ ሳይሆን ቀጠናዊውንና ዓለም አቀፋዊውን የፖለቲካ ግንኙነት ክህሎትን የሚጠይቅ ከባድ ኃላፊነት ነው። አንዳንዴም “ሙያ በልብ” የሚለውን ብሂል ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ የሚሆንበት ወቅት አለ። ብልህ ከታሪክና ልምድ ጥልቅ ዕውቀትን በመቅሰም ለዛሬ የአመራር ጥበብ ግብዓትን ይሸምታል።
ባለፈው ረቡዕ (01/03/14) የሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ይህን ብለው ነበር፦
“ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ለማሰባሰብና አንድ አድርጎ ጠንካራ ቀጠናን ለመፍጠር ያደረገችው ጥረት ብዙ አደጋና የውጪ ተፅዕኖ ጋብዞብናል፡፡”
ከላይ አምባሳደር ሬድዋን ያስቀመጡት ማጠቃለያ፣ አሜሪካ ሀገራችንን ለምን እንጠመደቻት በማወቁ ረገድ ዓይን ከፋች ምልከታ ነው ማለት ይቻላል። አሜሪካ ላይ ላዩን ሲታይ “ሰብዓዊ ገለመሌ” እያለች የምትደሰኩረውን የሽፋን ሰበብ እየገለጡ፣ እውነተኛው ምክንያቶቿንና ዓላማዎቿን በጥልቀት መፈተሽ በቀጣይነት ለምንወስዳቸው ውሳኔዎች መንገድ ከፋች ነው። እናም ዋናው መልዕክቴ ከታሪክና ልምድ እንማር የሚል ነው። ገዥው ፓርቲ ብልፅግና በአንድ ወቅት ፕራግማቲዝምን ገቢራዊ እንደሚያደርገው በአንዳንድ ስብሰባዎቹ ሲገልፅ ነበር። ታዲያ የፕራግማቲክ ውሳኔዎች መነሻቸው በዋናነት ታሪክና ልምድ (History and Experience) ስለመሆኑ ልብ ማለት ግድ ይላል። ፕራግማቲዝም የራሱ የሆኑ ውስንነቶች ቢኖሩትም በአንዳንድ ወቅቶች ጥቅም ላይ ልናውላቸው የምንችላቸውን የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመሻማት ዕድሉ ሊኖር ይችላል። አሜሪካኖች የብዙ ታዳጊ ሀገራትን ሕልምና ተስፋ አጨልመዋል። ከነርሱ ጋር የሚኖረን የትኛውም ዓይነት ተግባቦት፤ በዕውቀትና በሳይንስ እንዲሁም በታሪክ ግንዛቤ የታሸ መሆን አለበት።

_______________________________


                        ሚሌ ለምን ?
                        ዮሐንስ አንበርብር


          የጅቡቲ ኮሪደርን መቆጣጠር የኢትዮጵያ እስትንፋስ ላይ እንደ መቆም ነው የሚሉ የውጭ ተንታኞች ያስቃሉ። ምክንያቱም ከድሬደዋ - ደወሌ - ጅቡቲ የተገነባ ባለ ስድስት መስመር (Lane ) የክፍያ መንገድ ተጠናቆ ለትራንስፖርት ክፍት ከሆነ አንድ ዓመት ማስቆጠሩን የማያውቁ የውጭ ተንታኞች፣ ሚሌ በህወሓት ኃይል ተያዘ ማለት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እስትንፋስ አበቃለት ሲሉ ይዘላብዳሉ። በደቡብ በኩል የተገነባው ተመሳሳይ ዘመናዊ መንገድ ኢትዮጵያን ከኬንያው ሞምባሳ ወደብ ያገናኘ መሆኑንም አውቀው ይዘነጉታል። የህወሓት ኃይል ሚሌን ተቆጣጠረ ...ሊቆጣጠር ነው...የሚሉ መረጃዎችን እየነዙ ያሉት ደግሞ የውጭ ዜጎች መሆናቸው ያስገርማል። ህወሓት አፋር ላይ የደበቀው ምን እንደሆነ ማወቅ የመንግስት ኃላፊነት ቢሆንም ፤ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር የምትዋሰንበት ቅርቡ መስመር የሚገኘው በአፋር በኩል መሆኑ ግን ግልጽ ይመስለኛል። ከጦርነቱ ጀርባ ያለው የአሜሪካ ፍላጎት who should control the Red Sea የሚለውን መመለስ እንደሆነ ከግምት ማስገባት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። አሜሪካ አሁን ካለው ቀውስ ልታተርፍ የምትችለው ህወሓት የአፋርን ቀጣይ እጣ ፈንታ መወሰን የሚችል ከሆነ ነው።በቅርቡ በአሜሪካን አገር ከህወሓት ጋር ስምምነት ከፈጸሙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የአፋር አብዮታዊ አንድነት ግንባር ( ARDUF) ነው። ይህ ግንባር የተመሠረተው ኢህአዴግ ስልጣን በያዘበት ወቅት ሲሆን ዋነኛ ዓላማው ወደ ኤርትራ የተካለሉ አፋሮችን፣ ከኢትዮጵያ አፋሮች ለመቀላቀል እንደሆነ ይታወቃል። የኤርትራ አፋርን ከኢትዮጵያ ለመቀላቀል የትጥቅ ትግል የጀመረው ARDUF፤ ከረጅም ዓመታት እንቅልፍ በኋላ ዛሬ ለምን ባነነ ማለትም ያስፈልጋል።

____________________________________

                    ታሪክ ራሱን እየደገመ አይደለም
                           ተስፋ በላይነህ


          በጉጉት ሲጠበቁ የነበሩት እውቁ የታሪክ ፕሮፌሰር ሐቀኛው ባሕሩ ዘውዴ ይህንን ፅፈዋል:: የአማርኛ ትርጉሙን ከመኃል ዋና ጭብጥ በመውሰድ በአጭሩ ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ::
--------
[ታሪክ ራሱን እየደገመ አይደለም።
የአሁኑ ወቅቱ በ1983 ዓ.ም ደሴ በወያኔ ከወደቀች በኋላ ወያኔ ወደ አዲስ አበባ ከተጓዘበት ወቅት ጋር ጥቂት ተመሳሳይነትን አሳይቷል። ነገር ግን፣ አሁን 2014 ዓ.ም ነው:: ዛሬ 1983 ፈፅሞ አይደለም!
ያኔኮ፣ ወያኔ የኤርትራን ነፃ አውጭ ግንባር ሃይሎች ሙሉ ድጋፍና ትብብር አግኝታለች፣ ኤርትራዊያን የኤርትራን ነፃነት ለማግኘት ትይዩ ጦርነት እያካሂዱ ነበር። በሙሉ ድጋፍ ነበሩ!
አሁን ሁለቱ የቀድሞ ወዳጆች የመሃላ ጠላቶች ሆነዋል። ከዚያም በገዢው ደርግ ላይ የራሱ ቅሬታ የነበረው የአማራ ህዝብ፣ ለህወሓት ዋና ከተማውን መንገድ ጠርጓል። አሁን ያ ዘመን ተቀይሯል::
ዛሬ ? ወያኔ በአማራ ሬሳ ላይ ለመዝመት አስቦ ይሆን? የሕወሃት ቃል አቀባይ ከአንድ ጊዜ በላይ አሁንም ከአማራ ልሂቃን ጋር ለመወራረድ ሒሳቦች እንዳላቸው መግለጹ ተዘግቧል። ህወሓት ገና ከጅምሩ በአማራው ላይ በግልፅ የጥላቻ መንፈስ አሳይቷል፡፡ በ1967 የትጥቅ ትግሉን የከፈተበት ማኒፌስቶ ላይ ፀረ-አማራ አቋም መያዙን አስፍሯል። በማኒፌስቷቸውም የተጠቀሰው በ1880ዎቹ ዓ.ም አፄ ምኒልክ ከነገሱበት ጊዜ አንስቶ ህወሓት/ኢህአዴግ፣ በ1983  ስልጣን እስኪረከብ የነበረውን ጊዜ በሙሉ የጨለማ ዘመን አድርጎታል።

_____________________________________

                   ፃድቋ ህውሓት! «አማን መዝሙር»
                            ዘውድአለም ታደሠ


            የህውሓት ወዶ ገብ ደጋፊዎች፤ ህውሓት ታማልዳለች ሊሉ ምንም አልቀራቸው። በገባችበት ከተማ ሁሉ እንደ አባባ ጃንሆይ ገንዘብ እያደለች ፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ህሙማንን እየፈወሰች፣ ሙታንን እያስነሳች፣ ባለፈችበት መንደር ሁሉ እንደ ሙሴ ውሃ እያፈለቀች ምርኮኞቹን እያጠጣች ከሰማይ መና እያወረደች፣ እያበላች የምትዋጋ አስመስለው ሊተርኩልን ይጋጋጣሉ፡፡
የኔ ዘመዶችማ አሸማቀው ሊገድሉኝ ነው። የትናንቱን ሰቆቃ ረስተው ከህውሓት ጋር ትኩስ ፍቅር ይዟቸዋል። ህውሓትን ያመነ የዘላለም ህይወት አለው ማለት ነው የቀራቸው። ፕሮፌሰር ተብዬዎቹማ በስመ ወያኔ ስም አምነው፣ ሚኒሶታ የህውሓት ቢሮ ውስጥ «እምበር ተጋዳላይ» እየተዘመረ ሳይጠመቁ አልቀረም፡፡ ማይ ብራዘር፤ ሰው ሁሉ የሚናገረው አንድ አባባል አለ፡- “ስትሄድ የመታህ ድንጋይ ስትመለስም ከመታህ ድንጋዩ እሱ ሳይሆን አንተ ነህ” መቀሌ ከገባች በኋላ «የፌደራሊስት ያለህ» እያለች ነጠላ ዜማ መልቀቅ የጀመረችው ህውሓት፤ ቅልጥ ያለች አሃዳዊ እንደሆነች ሶማሌና አፋርን ሄደህ ጠይቅ።
 የኦሮሚያን ፕሬዚዳንት ከአራት ኪሎ የምትልክ ዘመናዊ ፊውዳል እኮ ነበረች፤ ኦቦሌሳ! በደህናው ጊዜ ያልሰጠችህን ነፃነት እንዲህ በበቀል ጦዛ ስልጣን ብትይዝ ትሰጠኛለች ብለህ ካመንክ ወይ ጅል ነህ፣ ወይ ጅብ ነህ! ለማንኛውም ሰዎች የኢትዮጵያ አምላክ ሲሉ፣ እነ ልደቱ «ኢትዮጵያ ደግሞ የራሷ አምላክ አላት ወይ?» ብለው ሲሳለቁ ሰምቻለሁ።
አባቴ አዎ የራሳችን አምላክ አለን። ዞር ዞር ብለህ ሰባ ሰማኒያ አመት የሞላቸውን አዛውንት ጠይቅ። ኢትዮጵያን ያልገጠማትና ያላለፈችው ችግር ምድር ላይ የለም። አምላኳ ጉልበተኛ ስለሆነ ሊሰብራት የመጣን እየሰበረ ወደመጣበት መልሶታል!

________________________________




               “ማነህ፥ ከየት ነህ? “ ካሉህ....
                      ታምሩ ዓለሙ


         ስማኝማ “ማነህ፥ ከየት ነህ? ካሉህ...እንዲህ በላቸው፤
ከአፍሪካ ብቸኛዋ ቅኝ ካልተገዛች፥ ሀያላኑን ድል ከነሳች የነፃነት ቀንዲል ምድር የተገኘሁ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ በላቸው፤ የሚኒልክን ጀግንነት የጣይቱን ብልጠት አስታውሳቸው፡፡
እናንተ የነፃነት ቀን ስትዘክሩ እኛ ግን የድል ቀን እናከብራለን በልና ስለ አድዋ ገድል ኮራ ብለህ አስተምራቸው፡፡
በሁለቱም ፆታዎች በኦሊምፒክ ወርቅ ያጠለቁ የመጀመሪያ አፍሪካዊያን አትሌቶች ከበቀሉባት የጀግኖች አምባ የተገኘሁ የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ በላቸው፤ የአበበ ቢቂላን የባዶ እግር አሻራ ፥ የደራርቱ ቱሉን የሳቅና የእምባ ድል ታሪክ ጥቀስላቸው፡፡
ከአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ብቸኛዋ የራሷ ፊደል ካላት ባለ ሆሄ ምድር ሀ...ሁ...ብዬ አፌን የፈታሁ ሀበሻ እኮ ነኝ በልና ንገራቸው፡፡
ከብዙዎቹ ቀድማ ክርስትናንና እስልምናን ከተቀበለች፥ እኔም ከአባቶቼ እምነቴን የተረከብኩ አቢሲንያዊ ነኝ በላቸው፤ በመፅሀፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርአን ስሟ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ሀገር እንዳለችህ ጠቁማቸው፡፡
አዎ “ማነህ፥ ከየት ነህ?” ካሉህ እንዲህ በላቸው...
የላሊበላ፣ የፋሲልና የአክሱም የጥበብ አሻራዎችን፥ የተፈጥሮ ስጦታዎችን እያነሳህ፣ የግዮን ውሀን የተጎነጨሁ እድለኛ ፍጡር ነኝ ብለህ ማንነትህን አሳያቸው፡፡
ስለ ዋርካው ምስለኔ ፍትህ፥ ስለ የኔታ ፊደል፥ ስለ ገዳ ስርዓት፣ ስለ ዙምራ ስልጣኔ እየዘከርክ፣ የባህልና የትውፊት ሀብታም ከሆነች ሀገር ስምህ መታተሙን አረጋግጥላቸው፡፡
አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለሟን አፍሪካዊያን የተጋሯት፥ የሰንደቅ ቀለሟን ብዙዎች የተቀባበሏት የነፃነት አውራ፣ የቀስተደመና ምልክት መጠሪያ እንዳለችህ ንገራቸው፡፡
የቡና መነሻም ቢሆን የኔዋ ኢትዮጵያ ነች በልና ከአቦል እስከ በረካ እየጋበዝክ አጫውታቸው፡፡
የቀዳሚ የሰው ዘር ምንጭ የሉሲና የአርዲ ቅሪተ አካል መገኛ ሀገር እንዳለችህም ከዘነጉት አስታውሳቸው፡፡
“ማነህ፥ ከየት ነህ?” ካሉህ ይህንንም ጨምርላቸው....
የአያት አባትህን ፈለግ ተከትለህ ወዳጅህን አርሂቡ ብለህ የምትቀበል፣ ለሀገርህ ጠላት ግን ምህረት እንደሌለህ ታሪክህን እያወሳህ አስጠንቅቃቸው፡፡
ሀገሬ የእርዳታና የብድር ጥገኛ ብትሆንም ለመፅዋቹ ብዬ ብኩርናዬን በምስር የምሸጥ ኤሳው አይደለሁም፤ ሀገሬን በዲናር የምለውጥ ባንዳ አይደለሁም በልና አሳፍረህ መልሳቸው፤ ይህ ቀን አልፎ ቀና የምትል ሀገርና ህዝብ አለኝ ብለህ ለሴራቸው እጅ እንደማትሰጥ በሚገባቸው ቋንቋ አስረዳቸው፡፡
ታሪክህ የድሮ፥ ጀግንነትህ የጥንት ነው ቢሉህ እንኳን፣ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ብለህ ንገራቸው፤ እኔም የዘመኔ ሚኒልክ እኔም የእድሜዬ ጣይቱ ነኝና ለምድሬ እድገትና አንድነት የምለፋ ፍም ትውልድ ነኝ በልና ቆፍጥነህ ሴራ ሳይሆን ስራ ሰርተህ አሳያቸው፤ ባለዙፋን ቢቀያየር የማልቀይራት ሀገር አለችኝ፤ በእሷ አትምጡብኝ ብለህ መልሳቸው፡፡
ደግሞ እንዳትረሳ ይህንንም ጨምርላቸው፦ በዘመን አመጣሽ ማዕበል የማትናወጥ የአምላክ የቃልኪዳን ሀገር አለችኝ በላቸው፤ ማን ትባላለች ካሉህ፤ ኮራ ብለህ ዘና ብለህ ቀና ብለህ ፈገግ ብለህ፣ ኢትዮጵያ መሆኗን አስረግጠህ ንገራቸው፡፡
አዎ በቃ በኩራት፤ “ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ” ነኝ በላቸው!!!
__________________________________



                         “ህዝበ ውሳኔ” ዋስትና አገር አ ይፈጥርም...
                              እስክንድር ከበደ


            ሶማሊላንድ የራሷን ነጻ ሀገር ለመሆን ለምን አቃታት? አንቀጽ 39 አይነት የራስን በራስ እድል እስከ መገንጠል የሚል ህገ መንግስት ማጻፍ አቅቷት አይደለም። ኤርትራ ሀገረ መንግስት የሆነችው በ1983 አመተምህረት የተሰበሰቡ የሰላምና ዴሞክራሲ ኮንፈረንስ ተሰብሳቢዎች በመወሰናቸው አይደለም። ስለ ኤርትራ ብዙ ማለት ይቻላል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጎጥና አካባቢያዊ አስተዳደሮች 100 ጊዜ ህዝበ ውሳኔ ቢያደርጉ ሀገረ መንግስት መሆን አይችሉም። ትግራይ የኢትዮጵያ ናት። መላ ኢትዮጵያውያን ህዝበ ውሳኔ አድርገው ሀገር ትሁን ቢሉ እንኳን ሀገር መሆን አትችልም። እንዲህ መሆን ቢቻል ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪካ ሀገራት የሚገኙ ተቀናቃኝ ብሔሮች ድንበር እየተሳመሩ መበጣበጥ ይጀምራሉ።የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የሀገራትን የቅኝ ግዛት ውሎች እንዳለ የተቀበለው ያለ ምክንያት አይደለም። ዶክተር ደብረጺዮን እንደሚሉት ቢቻል ኖሮ፣ በአፍሪካ ከ200 ሀገር በላይ ይፈጠሩ ነበር። የአፍሪካ ሰላም፤የአለም ሰላም ይናጋል። አንቀጽ 39 ህገመንግስቴ ውስጥ አለ ብለህ “ህዝበ ውሳኔ” “ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች” እያሉ ማስፈራራት አይሰራም። በ1983 አዲስ አበባ ሞቃዲሾ ወይም ሞኖሮቪያ እንዳትሆን በሚል የፍርሀት ቆፈን መፍጠር ዛሬ አይሰራም። ነገም አይሰራም። ማዕከላዊ መንግስት የሀገሪቱን እያንዳንዷን ድንበር ኢንች በኢንች ማስከበር አለበት። የፌደራል መንግስት የቡድኑን ጭካኔ እየቆጠረ ብቻ መዘገብ ሳይሆን ሁሉን አቀፍ ዘመቻ በማድረግ፣ የሀገሪቱን ሉአላዊነት ማስከበር አለበት። አሁን ዘመቻው ሉዓላዊት ሀገርን መከላከልና ማስጠበቅ ቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን ይገባዋል፡፡



Read 1492 times