Print this page
Tuesday, 23 November 2021 00:00

ሀገርና_ሰፌድ -------

Written by  ነፃነት አምሳሉ
Rate this item
(0 votes)

‹‹--ሀገር ስትናወጥ ቀብርዋን ለማስፈጸም የስልክ ጥሪ የሚጠብቁ ገዳዮች አሰፍስፈው እየጠበቁ ነው! ብንጣላ ሊበትነን የመውጫ መንገድ ጠቋሚ ካርታ ይዞ ወደ ባህር ጉዞ ሊመራን ያሰፈሰፈ ሃይል፣ ጀልባ ላይ ቆም እየጠበቀን ነው!--››
      
            ሃቁን እናውቀዋለን፡፡ ነጋሪ አያሻንም ለነገሩ ከራሳችን ታሪክ መማር እንዴት እንቸገራለን? ለኛ ይህን መንገር እናቱን አልቅሶ ለቀበረ ሀዘንተኛ፣ ወፍ ሳይንጫጫ ማለዳ ላይ በር መትቶ፤ #እናትህ ሞተችብህ; የማለት ያህል ነው! ነገሩን ቀለል አድርገን እንመልከተው! ሰፌድ ይዞ እህል ማበጠር የእለት ኑሮአችን ክስተት ነው፡፡ የተለየ ገራሚ ነገር የለውም፡፡
ክስተቱን ከህይወታችን ጋር አጋምዶ ለተመለከተ ግን ራሱን የቻለ የማስተማርያ ዘዴ ነው፡፡ ሰው የሚማረው ወንበር ዘርግቶ ከመምህሩ እግር ስር በመቀመጥ ብቻ ሳይሆን ከራሱም ኑሮ ጭምር አይደል? እናማ ሰፌዱ የሰበዝ ስሪት ዝርግ ንጣፍ ቢሆንም የሀገር ምሳሌ ነው፡፡ ሰፌድን የእህል ዘሮች እኩል ይቀመጡበታል፡፡ <አዳለጠኝ> ብሎ የሚንከባለል እህል የለም፡፡ ከታች ሆንኩኝ ብሎ አሊያም ጥግ ላይ ተቀመጥኩኝ አሊያም ንፋሱ እኔን ነካኝ ብሎ በደል ደረሰብኝ የሚል እህል የለም፡፡ ሁሉም በስፍራው እንዲቀመጥ ሰፌዱ ራሱን ምቹ ምንጣፍ አድርጎ አቅርቧል፡፡ የአንዳንዱ እህል ጫፍ እሾህ ሆኖ ሰፌዱን ቁልቁል ሲወጋው ሰፌዱ አቆሰልከኝ ብሎ አይጥለውም፡፡ የአንዳንዱ እህል ክብደት ሲጫነው ከበደኝ ብሎ አያወርደውም፡፡ የአንዳንዱ እህል መልከ ጥፉ መሆን ሰፌዱን አናድዶት አይወረውረውም፡፡ ሰፌዱ ልክ እንደ ሰው ልጅ ሆደ ሰፊ ነው፡፡ የክረምቱንም የበጋውንም እህል፣ የበጋውንም የቆላውንም ዘር እኩል ይሸከማል፡፡ ምንም እንኳን የሰፌዱ ስፌት በቀለማት ሰበዞች ደምቆ ቢታይም፣ የቆሸሸ ወይም አቧራ ያለበት ወይም ጭቃ የነካው ቢሆንም ሳይጸየፍ  ይሸከማል፡፡
ሀገርም እንዲሁ ናት፡፡ ሁሉንም ዜጎችዋን ሳትንቅ÷ ሳትጸየፍ÷ ሳታበላልጥ ለነዋሪዎቿ ደረጃ አውጥታ ልዩነት ሳትፈጥር እኩል ትሸከማለች፡፡ ጎረበጥከኝ ብላ ደጅ የምታሳድረው፣ ለሰለስከኝ ብላ የላባ ትራስ ገዝታለት የምታስተኛው ደረጃ አንድ ዜጋ የላትም፡፡ የሚወጋትንም የሚዋጋላትንም÷ የሚያቆስላትንም የሚቆስልላትንም÷ የሚቀጥፋትንም የሚቀጠፍላትንም እኩል በምድርዋ ላይ ታስተኛለች! በዚህም አታጉረመርምም!
ሀገር የማትችለው የት አለ? ሰፌዱ የስንዴውን ብቻ ሳይሆን የእንክርዳዱንም አመል እኩል ይዞ ያስቀምጣል፡፡ ታዲያ ሀገርስ እንዲሁ አይደለች? የሚያሴርባትን አይታ እንዳላየች÷ ሊያጠፋት እሳትና ክብሪት ይዞ የሚፎክርባትን እየታዘበች÷ በስልጣኑ ተጠቅሞ ደም እንባ የሚያስነባትን <ነገ ይማራል> ብላ እያለፈች÷ በእውቀቱ ተጠቅሞ ሊያፈርሳት አዲስ አካፋ ገዝቶ የሚቆፍራትን አይታ <ይቅር ይበልህ> እያለች በምህረት ዓይንዋ አይታ ዝም ትላለች፡፡
ሀገር ማለት ትንግርት ናት! ለክብርዋ ብሎ በድንበር ምሽግ ውስጥ ተደፍቶ የሚቀበርላትን አይታ እያለቀሰች÷ በተራ ዜግነቱ ከሚያገኛት እንጥፍጣፊ ገቢ ግብር ገብሮ ሲደግፋት እየተደነቀች÷ ለራሱ ኑሮ ወር መድረስ እያቃተው ለተቸገረ ለማካፈል ማዕዱን የማይደብቅ ዜጋዋን አይታ ፈጣሪዋን እያመሰገነች÷ ክፉ ቀን ደጅዋን ሲመታ ለሀገር ጥሪ ደም አጥንት ገብሮ ሊያኖራት ወረፋ ይዞ ሊሞትላት የሚራኮተውንም አይታ እየተደመመች ልክ እንደ ሰፌድ ሁሉን አቅፋ የምትኖር ህያዊት ርስት እናት ሀገር ነች፡፡
ለሁሉም ቀን አለው ይባል የለ ታዲያ? ቀን ስልህ የሳምንት መቁጠርያ እንዳይመስልህ! ቀን የምልህ ፈራጅ ጊዜን ነው! አዎ ስንዴው ስንዴነቱ ታዉቆ ወደ ጎተራ÷ እንክርዳዱም ከነቀዝ ጋር ያለውን ፍቅር እስከ እሳት ድረስ እንዲቀጥል ጊዜ ፈራጅ ዳኛ ሆኖ በራሱ ዙፋን መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ ያን ጊዜ ስንዴውን እንደሚያነፍሱት እናቶች ለሀገር ሟች÷ ለባንዲራ ተጋዳይ ÷ ለእውነት ዘበኛ÷ ለህሊና ዳኛ÷ ለሃቅ አንገት የሚሰጡ ዜጎች እንደ ችግኝ ፈልተው እንደ ሰራዊት ተምመው ውዲት ሀገራቸውን ለማስቀጠል የባህር መሻገርያ ዘንጋቸውን ይዘው ስለ ህዝባቸው መቆማቸው አይቀርም፡፡ ያን ጊዜ ክፉዎችን ከደጋጎች÷ ቅኖችን ከተንኮለኞች÷ አጥፊዎችን ከአልሚዎች ይለያሉ፡፡ እድል ፈንታው ሁሉ ከንፋስ ጋር የሆነ ገለባ ማንነት ያለው ዜጋም ፍርድን ይቀበላል፡፡
ቅን÷ ደግ÷ የዋህ÷ ርህሩህ ዜጎች ለሀገራቸው ቀጣይ ዕድል ፈንታ የይሁንታ ድምጻቸውን ሲሰጡ የእግራቸው ዱካ በረገጠበት ሁሉ ሰላምን ፍቅርን፣ በጎነትን፣ ደግነትን ይዘራሉ፡፡ በዚያው ልክ ምድሪቱ ላይ ሆነው ሀገር የሚያጎሳቁሉትን÷ ዜጎችን የሚያማርሩትን÷ በብሔር ከፋፍለው ቁርሾ የሚያዋልዱትን÷ በእምነት ልዩነት አሳበው አጥፍቶ መጥፋትን የጽድቅ መንገድ አድርገው የሚያውጁትን÷ እውነትን ለሀሰት በቀብድ የሚሸጡትን እየቀጡ መልካም ዜጎችን ለሀገር ግንባታ÷ አጥፊ ዜጎችን ከሰፌዱ ላይ አራግፈው ለመቀጣጫ ይደርጋሉ፡፡
በመጨረሻ “እፍ” “እፍ” እየተባለ እህሉ በነፋስ ጠርቶ ሰፌዱ የስንዴዎች ብቻ ማረፍያ እንደሚሆነው ሁሉ ቀናኢ ትውልድ ህግ÷ ፍትህ÷ እውነትና ህሊናን አስቀድመው ፈራጅ የሆኑ ለታ እውነተኛ ዜጎችም የእውነት ፀሀይ ወጥቶላቸው የፊት ወንበር ላይ የሚቀመጡበት ቀን ይከሰታል፡፡ ይብላኝላቸው ለእንክርዳዶች! ሀገርና ሰፌድ እኛነታችንን የምናይባቸው መንታ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
የሰፌዱ ክብር የሰበዙ ቀለም ሳይሆን እህሉ ነው፡፡ የሀገር ጌጥና ውበት ባዶ ስምዋ ሳይሆን ሁሉንም ዜጎችዋን እኩል ይዛ መኖርዋ ነው፡፡ ሀገርን መውደድ ማለት ገዢ ስርዓትን መደገፍ ሳይሆን የሌሎችን ወንድሞችና እህቶች ማንነት በደስታ ተቀብሎ አብሮ የመኖር ህላዌነት ነው፡፡
ሰፈዱ ሲበተን እህል አይቀመጥበትም፤ ተፈላጊነትም የለውም፤ ክብርም አያገኝም፤ ለሰው ቢሰጡት አያስመሰግንም፤ ቢያውሱት ውለታ አይሆንም፤ ቢሰቅሉት ውበት አይሰጥም፡፡
ሀገርም እንዲሁ ነች! ሀገርም ብትፈርስ ክብር የለንም! ብትጎሳቆል ደስታ አናገኝም! ብትጨነቅ ሰላም አይኖረንም! ብንዘፍን ሲቃ ነው! ብንዘምር ዋይታ ነው! ብንበላ ረሃብ፣ ብንጠጣ ጥማት ነው! ብንለብስ የሚያቃጥል ብርድ ነው! ብንናገር አድማጭ ማጣት ነው!
ሀገር ስትናወጥ ቀብርዋን ለማስፈጸም የስልክ ጥሪ የሚጠብቁ ገዳዮች አሰፍስፈው እየጠበቁ ነው! ብንጣላ ሊበትነን የመውጫ መንገድ ጠቋሚ ካርታ ይዞ ወደ ባህር ጉዞ ሊመራን ያሰፈሰፈ ሃይል፣ ጀልባ ላይ ቆም እየጠበቀን ነው! ከዚህም ሲብስ ከዓለም ካርታ ላይ ሊያጠፋን የፖለቲካ ላጲስ ይዞ ዙርያችንን የሚዞር ጸረ-ኢትዮጵያ ሃይል ፊሺካ ለመንፋት ጉሮሮውን እየሳለ ይገኛል፡፡
እናሳ ምን ተሻለን? የሚሻለንማ ለእህላችን ሰፌዳችን÷ ለህልውናችን ደግሞ ሀገራችንን መጠበቅ÷ መንከባከብና ገፋ ሲልም መስዋዕትነትን ከፍለን እድሜዋን ማስቀጠል የዜግነት ግዴታችን ይሆናል፡፡


Read 4705 times