Saturday, 20 November 2021 15:05

ዳሽን ባንክ ባለፈው የበጀት ዓመት 10 ቢ.ብር ገቢ ማግኘቱን ገለፀ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

      በተያዘው ዓመት የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 12 ቢ ብር ለማሳደግ ባለ አክስዮኖች ወስነዋል
                           
             ዳሽን ባንክ ባሳለፍነው የበጀት ዓመት 10 ቢ ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ገለፀ፡፡ ባንኩ ይህን የገለፀው ባለፈው ሀሙስ ህዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም መቻሬ ሜዳ ውስጥ ባካሄደው ዓመታዊ 28ኛ መደበኛ እና 25ኛ  ድንገተኛ ጉባኤው ላይ ነው። በዕለቱ ባለ አክስዮኖች እስከ ሰኔ ወር  2013 ዓ.ም ድረስ የነበረውን የተከፈለ 5.4 ቢ ብር በተያዘው በጀት ዓመት ውስጥ ወደ 12 ቢ ብር ለማሳደግ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ባለ አክስዮኖቹ ይህንን የተከፈለ ካፒታል ወደ 12 ቢ ብር ለማሳደግ እንዲያስችላቸውም የካፒታል እድገቱን የማዳበር አቅም በማሳደግና ዘርፈ ብዙ ኢንቨስትመንቶችን በመደገፍ ባንኩን ይበልጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ ሥራዎች በስፋት እንደሚሰሩም በጉባኤው ተመልክቷል፡፡
ዳሽን ባንክ ባካሄደው ጉባኤ ለባለ አክስዮኖች በቀረበው ሪፖርት ባሳለፍነው የበጀት ዓመት 10 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ከማግኘቱም በተጨማሪ ከግብር በፊት  2.4 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱም ይፋ ሆኗል፡፡በዚሁ ባለፈው በጀት ዓመት ባንኩ 21.1ቢ ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉንና ይህም የተሰበሰበ ገንዘብ የባንኩን አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ 74.6 ቢ ብር ከፍ እንዳደረገው የገለፁት ሀላፊዎቹ ይህም ውጤት ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ39.4 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
እንደ ሀላፊዎቹ ገለፃ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 94.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህ የሀብት መጠን ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ38.7 በመቶ እድገት ማሳየቱን የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው አለሙ ገልፀው፣ ለዚህ  ስኬት በእጅጉ የታተሩትን የባንኩን አመራሮች፣ሰራተኞች፣ከባንኩ ጋር የሚሰሩትን ደንበኞችና አጠቃላይ ለእዚህ  እድገት ድርሻ ያላቸውን አካላት በእጅጉ አመስግነዋል፡፡ እንደሃላፊው ገለፃ  የባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ባለፈው የበጀት ዓመት ከፍተኛ እድገት ማስመዝገቡንና በአጠቃላይ ባንኩ ለስበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 4.8 ቢሊዮን ብር ማበራከቱንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በ11 ባለአክስዮን ከ25 ዓመት በፊት የተመሰረተው ዳሽን ባንክ በአሁኑ ወቅት የባለ አክስዮኖቹ ቁጥር ወደ 2 ሺህ 65 መድረሱም ተጠቁሟል፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የባንኩ ደንበኞች ቁጥር ከ3 ሚ በላይ ሲሆን የአሞሌ ተጠቃሚዎች ቁጥርም ወደ 2.4 ሚሊዮን ማደጉን አቶ አስፋው ዓለሙ በጉባኤው ላይ አብራርተዋል፡፡

Read 1901 times