Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 13:32

ጳጉሜ 10

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዛሬ ቀኑ ጳጉሜ “አስር” ነው፡፡ ለኔ፡፡ ለእናንተ መስከረም “አምስት” ሊሆን ይችላል፡፡ መብታችሁ ነው፤ አይመለከተኝም፡፡

ዝናቡ አላቆመም፡፡ ውሸትም አላባራም፡፡ የኑሮ ውድነት ከህመሙ አላገገመም፡፡ ስለዚህ ጳጉሜ ለእኔ ተራዝሟል፡፡ ተስፋዬ ተግባሬ ሲሆን አዲሱ አመት ይጀምራል፡፡ጳጉሜ አስር ለእኔ ቀን መቁጠሪያ ብቻ በቀይ የተፃፈ … በቀይ የተፃፈው አመት በአል መሆኑን ለመግለፅ ስለሆነ… ብቻዬን በአሉን አክብሬ እውላለሁ፡፡ጳጉሜ አስር፡- “የእውነት ቀን” ነው፡፡ ታስቦና ተከብሮ ይውላል፡፡ የውሸት ዝናብ በእውነት ፀሃይ ደርቆ …ውዱ ኑሮም ረክሶ ይውላል፡፡ “ስለ ነገ፤ ራሱ ነገ ይጨነቅ… ዛሬ የራሱ ብዙ ጭንቀቶች አሉበትና” ይላል፤ ክርስቶስ “በተራራ ስብከቱ” ላይ፡፡“የእውነት ቀንን” ለማክበር ከክርስቶስ አስተምሮቶች ትዝታ በላይ የሚያገለግለኝ የለም፡፡ ከክርስቶስ በላይ የክርስቶስ ትምህርቶች ይበልጡብኛል፡፡ ጳጉሜ ላይ በራሴ ቀን መቁጠሪያ ውስጥ ተቆጥሬ ለቀረሁት እኔ፡፡

ክርስቶስ፤ የሩቁን ፈጣሪ ወደ ቅርቡ ሰው አውርዶ ያስተማረ ሰው ነው፡፡ የሰማዩን ህግ ወደተራራው ጫፍ ዝቅ አድርጐ የሰበከ አርቲስት ነው፡፡ …ግን (ከይቅርታ ጋር) ክርስቶስ የሰውን ስቃይ የተጋራው ለአንድ ቀን ብቻ ነው፡ ተገርፎ እስኪሰቀል ባለችው ሰአታት ብቻ፡፡ ቢሆንም፤ እስካሁን ወደ ምድር ከተላኩ የፈጣሪ አምባሳደሮች… ፍጡሩን መስሎ የቀረበ እሱ ይመስለኛል፡፡ፍጡሩ ስል፡- በስቃይ፣ በድህነት፣ በበሽታ፣ በጭቆና… እና ወዘተርፈ አሉታዊ የህልውና ገፅታ …የሚኖሩትን ማለቴ ነው፡፡

…የግሪካዊያኑ አማልክቶች… መሳፍንቶች ናቸው፡ ለድሀ ቀርበው የድሀን ስቃይ ሊረዱ አይችሉም፡፡ ሰው ቢመስሉም… የሰው ጉዳይ ከእነሱ ጋር ተያያዥ እስካልሆነ አይመለከታቸውም …ድሀ የእውነትን ቀን ሲያከብር መሳፍንቶቹን አማልክት በማምለክ ሊሆን አይችልም፡፡

በካፒታሊዝም ስርዓት ውስጥ የሚኖሩ ምዕራባዊያን አኗኗራቸው… የምቾት ከሆነ የክርስቶስን አስተምሮት የተረዱት በመሳፍንት እይታቸው ነው፡፡ በካፒታሊዝም ስርአት ውስጥ ያለ ክርስቲያን እንደ ኒቆዲሞስ ነው፡፡ “ያለውን ንብረት ሸጦ መከተል” የሚያቅተው፡፡ …ያለውን ንብረት መሸጥ ባይችል ሊሞት ሲል ማውረስ ግን ይችላል፡

የክርስቶስ  አስተምሮት ነብሱን በተወሰነ መልክ የማይነካው ማንም ሰው አይገኝም፡፡ የተነካ በሙሉ ክርስቲያን ብሎ ራሱን ላይጠራ ይችላል፡፡ አምኖ ያልተጠመቀ፡፡ ተጠምቆ ያላመነ፡፡ …ከጥሩ ህይወት በኋላ መጥፎ (የመቀጠል ተስፋ የሌለው) ሞት የማይፈልግ ወይንም ከመጥፎ ህይወት በኋላ ተስፋ ያለው ሞት የሚፈልግ… ሰው እስከኖረ ድረስ ሁሌም ይኖራል፡፡ …የእውነት ቀንን ያለ ክርስቶስ ማክበር አይቻልም፡፡ ካልሆነ ጳጉሜ እድሜ ልክ ተራዝሞ ይቀጥላል፡፡

የእውነት ቀንን ለማክበር እውነትን ማግኘት ወይንም እውነትን መተግበር መቻል ላያስፈልግ ይችላል፡፡ የነፃነት ቀንን ለማክበር ነፃ መሆን እንደማያስፈልገው ማለት ነው (A beggar on horse back whips a beggar on foot, gunshot, revolution, …the beggars have exchanged places, but, the whipping goes on) …ብዙ የነፃነት በአላት ይከበራሉ፤ መከበሩም ይቀጥላል፡፡ የነፃነት በአል ለማክበር፤ የነፃነትን ትርጉም ማግኘትም ሆነ አግኝቶ እስከ መጨረሻው መዝለቅ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ የእውነት ቀኑንም የማከብረው በዚሁ መንፈስ ነው፡፡ ክርስቶስ ነው የዚህ ቀኔ ዋና ምሳሌ፡፡ ካርል ማርክስም ሊሆን ይችል ነበር… ግን የእሱ የድሮ እውነት ውሸት ሆኖ… በሚያምኑት ተሽሯል፡ …የክርስቶስ ግን ሊሻር አልቻለም፡፡ ጠለቅ አድርጐ ነው የተከላት፤ ወይንም ባንዲራዋን ሩቅ አድርጐ ነው የሰቀላት፡፡ ማንም ሊያወርዳት እስካልቻለ ድረስ፤ በእሷ ስር የጳጉሜውን “የእውነት ቀኔን” አከብራለሁ፡፡

ክርስትና የሚያስተምረው ስነ ምግባር… ዝቅ በማለት ከፍ ማለት እንደሚቻል ይገልፃል፡፡ በድብቅ ለሰራኸው ፅድቅ በግልፅ እንደምትቀበል ይመሰክራል፡፡ ለእውነት የተጠሙ እንደሚጠግቧት እርግጠኛ ሆኖ ይናገራል፡፡ …ወደ ፈጣሪ ፀሎት ወይንም አንኳኩቶ የጠየቀ ሁሉ መልስ እና የተከፈተ በር እንደሚሰጠው ያረጋግጣል፡፡…የክርስቶስ እውነት የሚርበው በህግ መልክ ነው፡፡ በሎጂክ ወይንም ምክኒያታዊነት የተተነተነ አይደለም፡፡ ምክኒያታዊ ከሆነው የምድር ህግ በላይ የእውነትን ፍትህ እንደሚሰጥ በሰው ልጆች ዘንድ ይታመንበታል፡፡

…ሁሉንም በእኩል ሁኔታ የሚያስተዳድር መንግስት በሰው ልጆች ዘንድ ይፈለጋል፤ በክርስትናው ህግ ግን ተገኝቷል ይለናል ክርስቶስ፡፡ …ይህንን ሲያስተምር፤ የድምፅ መቅጃ ወይንም በአለም አቀፍ ጋዜጠኞች የዜና ሽፋን አልተሰጠውም፡፡ …ስብከቱን የሰሙት ሰዎች ድሆች ነበሩ፡፡ በቄሳር (የሮማ) የጉልበተኛ መንግስት ስርአት ውስጥ ጉልበት የሌላቸው… የተረሱ ህዝቦች፡፡ አስተማሪው “የአይሁድ ንጉስ” የተባለውም ሮማዎቹን ስለማይወክል ነበር፡፡ ሮማዎችም ግን ሰው ነበሩ፡፡

…ክርስቶስ በምቾት ጆሮ አይሰማም? …ድሮ አቅመ ቢስ የነበሩት ሰዎች ዘንድሮ አቅመ ሙሉ ከሆኑ… የክርስቶስ አስተምሮት ወደ አፍሪካ መግባቱ አልቀረም፡፡ ብዙ ደሀ ያልተመቸው ወዳለበት፡፡ ወይንም አቅመ ቢስ ወደበዛበት ቦታ ሁሉ፡፡

የእውነት ቀን፤ የሁሉም የሰው ልጆች አመት በዓል አይደለም፡፡ የክርስቶስ እውነት፣ የፈጣሪ ህግ እንጂ የሰዎች ህግ አይደለም፡፡ ምናልባት ለዚህ ይሆናል ህጉን ለመተግበር እንሞክራለን እንጂ ሞልቶልን የማያውቀው፡፡

ለዚህ ነው፤ ክርስቶስን ለመሆን በመሞከር እና ሰው ለመሆን በመሞከር መሀል በሰማይ እና በምድር መሃል ተበጥሰን የቀረነው… ሁለቱንም “ፈፅመን” ሳይሆን፡፡ ለዚህ ነው፤ የክርስቶስ የእውነት ሰንደቅ ከተሰቀለችበት ዝቅ የማትለው፡፡ …ደርሶ የጨበጣት ስለሌለ፡፡

(ህግን በቀላሉ መፈፀም ሲቻል አዲስ ለመፈፀም የሚችል ህግ ይወጣል፡፡)

ለምንድነው ከክርስቶስ በኋላ በበለጠ የሚነካ እውነት እስካሁን (ለእኔ) የሌለው?... ክርስትናን ማሻሻል ወይንም ማደስ እንደተቻለው ለምን ክርስቶስን ማሻሻል አልተቻለም?... ከተራራው ስብከት የበለጠ ስብከት የሰጠኝ ለምን የለም?...

ለእኔ፤ ጳጉሜ ስምንት በየአመቱ አይገኝም፡፡ በህይወት ዘመን አንዴ ነው የሚመጣው፡፡ ሦስት መቶ ስልሳ ስድስት ቀን የለውም፤ እውነት፡፡ እውነት አንድ ነው፡፡ ይህ አንድ እውነትን የሚወክል አንድ ቀን፣ በእድሜ ዘመናችሁ አንዴ እንድታከብሩ ቢፈቀድላችሁ… ማንን ወይንም ምንን አክብራችሁ ትውላላችሁ?

እውነትን ምድራዊ በአል (እንደ እንቁጣጣሽ) አድርጋችሁ… በተፈጥሮ፣ በታሪክ ላይ ያሉ የፍልስፍና ወይንም የሀገር መሪዎችን እና አስተሳሰባቸውን (“ኢዝሞቻቸውን”) ሰቅላችሁ ስታከብሯቸው ትውላላችሁ? ወይንስ፤ ሰማያዊውን ወደ ምድር ያመጡትን ነብያት አክብራችሁ ትውላላችሁ? …ከፈጣሪ ወደ ሰው የተላከ እውነተኛ ደብዳቤ ይሻላል… ወይንስ ከሰው ወደ ሰው የተላከ እውነተኛ ደብዳቤ?

ከሰው ወደ ሰው የተላከ ምርጡ ደብዳቤ የቱ ነው?... ክርስቶስም እኮ ሰው ነበር (ፍፁም የምትለዋ ተቀጥላ ሳትጨመርበት) …እርግጥ፤ የክርስቶስ እውነት የሚሰራው ፈጣሪ እንዳለ ማረጋገጥ ሲቻል ብቻ ነው ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ …ግን፤ ማረጋገጥ የቻልነው ብቻ ከሆነ እውነት፤ ማረጋገጥ የቻልነው በጣም ኢምንት ስለሆነ እውነት የሰውን የእውቀት መጠን አክሎ ሊያንስ ነው፡፡

…የማናውቀው ስፋት ብቻ ነው ተስፋችን፡፡ የማናውቀው፤ ተስፋችን ካልሆነልን የፍርሀታችን ምንጭ መሆኑ አይቀርም፡፡

…ተስፋ፤ ከፍርሀት እና ከትርጉመ ቢስ ህልውና የሚያድነን ከሆነ… “ውሸት” ሊሆን አይችልም (ይህ አስተሳሰብ “ፕራግማቲዝም” እንዳይመስልብኝ እሰጋለሁ!) መልካም ነገር መሆኑ ብቻ “እውነት” ያደርገዋል፡፡ እንዲያውም ከፍተኛ እውነት፡፡ የእውነት “ቀኔ”፤ ምድራዊ እውነትን ብቻ ማየት የሚችል ከሆነ… የተስፋ “ቀኔ” አይሆንም፡፡ ከተጨባጩ እውነት በላይ… ተስፋዬ በጣም ሰፊ ነው፡፡ የውስጥ ሰላምንም ይሰጠኛል፡፡

በዚህ አጭር እይታ የዛሬዋን ቀን አክብሬ ውያለሁ፡፡ ነገ፤ ወደናንተ እውነታ ወደ መስከረም 5/2005 እቀላቀላለሁ፡፡ ጳጉሜዬን በተስፋ አልፌአለሁ፡፡ የእውነት ቀኔን አክብሬአለሁ፡፡

 

 

Read 2542 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 13:36