Saturday, 20 November 2021 14:27

አሜሪካ የኢትዮጵያ ጉዳይ እረፍት አልሰጣትም

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(7 votes)

   ኬንያ “ኢትዮጵያ እርዳታችንን ስትፈልግና ስትጠይቀን ለመርዳት ዝግጁ ነኝ ብላለች
                   
             በህወኃት የሽብር ቡድን በተከፈተውና ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት እንቅልፍ ያጣችው አሜሪካ፤ በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት የሽብር ቡድኑን ከመንግስት ጋር ለማደራደር ጥረት ማድረጓን ቀጥላለች፡፡ አገሪቱ ጦርነቱን በቅርበት የሚከታተሉ ልዩ መልዕክተኛ የሰየመች ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሃላፊዋን አንቶኒ ቢሊንክንንም  በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲመክሩ ባለፈው ሳምንት ወደ ኬንያ ልካቸዋለች፡፡
የፌደራል መንግስቱ ከህወኃት የሽብር ቡድኑ ጋር እያካሄደ ያለው ጦርነት አሳስቦኛል የምትለው አሜሪካ፤ ጦርነቱን በማስቆም  የሽብር ቡድኑን ከመንግስት ጋር ለማደራደር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ድርድሩን ለመቀበል ፍቃደኛ ካልሆነ ተደራራቢ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ስትዝት የቆየችው አገረ አሜሪካ፤ ኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚ ከመሆን የሚያግዳትን  ውሳኔ ማሳለፉን ጨምሮ  የተለያዩ በርካታ ማዕቀቦችን ጥላለች፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከኬኒያ  ፕሬዚዳንት ጋር ለመምከር  ባለፈው ሳምንት ወደ ኬኒያ ናይሮቢ ያቀኑት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ  አንቶኒ ብሊንከን፤ በ”ጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሓይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነት አቁመው ልዩነቶቻቸውን በድርድር ሊፈቱ ይገባል” ብለዋል፡፡ ተፋላሚዎቹ ተኩስ አቁመው ንግግር መጀመር አለባቸው፤ የኢትዮጵያ ግጭት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታ አደጋ ነው፤ ለኬኒያም አሳሳቢ ነው ስለዚህም ሁለቱም ወገኖች ወደ ነበሩበት ተመልሰው ሊደራደሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ በኢትዪጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በቅርበት እንዲከታተሉ የሰየመቻቸው የፕሬዚዳት ባይደን ልዩ መልክተኛ ጄፈር ፌልትማን
ልዩ መልዕክተኛው ከኬኒያው ፕሬዚዳንትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መምከራቸውና ኬኒያም ሁለቱንም  ተፋላሚ ሃይሎች ወደ እርቅና ድርድር እንዲመጡ በማድረጉ ረገድ የበኩሏን አስተዋፅኦ እንድታበረክት ሲጎትቱ ነው የቆዩት።
በዚህ መሰረትም የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በኋላ የኬኒያው የውጭ ጉደይ ሚ/ር አምባሳደር ራሴል ሰማሞ በሰጡት መግለጫ፤ “ከሁሉ አስቀድሞ ኢትዮጵያ ችግሮቿን በራሷ የመፍታት አቅምና  ጥበብ እንዳላት መቀበል ይገባናል” ብለዋል።
“ዘላቂ መፍትሔ የሚመጣው ከውጭ ሳይሆነ ከራሳቸው ከኢትዮጵያውያን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ጦርነቱ ለዘለዓለም የሚቀጥል እንዳልሆነና ሊጠናቀቅም ኢትዮጵያ በቀድሞው ጥንካሬዋ እንደምትቀጥል  ጠቁመው፤ “እባካችሁ በኢትዮጵያና ህዝቦቿ  ፈጽሞ ተስፋ አንቁረጥ፡፡ ለዚች አገር ሰላም ሁላችንም ቀና አተያይና አርዳድ ይኑረን” ብለዋል፡፡ ኬኒያ እንደ ጎረቤት አገር ማድረግ የምትችለው ኢትዮጵያ እርዳታችንን በፈለገችና በጠየቀችን ጊዜ ሁሉ እጃችንን መዘርጋት ብቻ ነው ሲሉም ተናግረዋል፤ ሚኒስትሯ፡፡
የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞ የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ኦሌሴንጎ ኦባሳንጆ ሁለቱን ወገኖች በማነጋገር ወደ እርቅና ድርደር ለማምጣት እየጣሩ ሲሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከህወኃት መሪዎች ጋር በመወያየት ለችግሩ መፍትሄ እያፈላለጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አሜሪካ ይህንኑ የኦባስንጆ የድርድር ጥረት እንደምትደግፍና ለተግባራዊነቱም ሙሉ ድጋፏን እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡
በአንድ በኩል ጦርነቱ ቆሞ ተፋላሚ ሃይሎች  ወደ ድርድር እንዲመጡ ፅኑ ፍላጎቷ መሆኗን የምትገልፀው አሜሪካ፤ መዲናዋ አዲስ አበባ አገሪቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ በማመሰልና ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በህወኃት ኃይሎች ተከባለች በማለት  ዜጎቿ በተገኘው የመገናኛ መንገድ ከአገር እንዲወጡ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እየሰጠች ትገኛለች።የአፍሪካ ህብረቱ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ በበኩላቸው፤ የሰላም መፍትሔ በማፈላለግ ሂደታቸው  የደረሱበትን ሃሳብ ለኢትዮጵያ መንገስት ከማብራራታቸውም በተጨማሪ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ላደረጉ የአፍሪካ ህብረት አምባሳደሮች በኢትዮጵያ ጉዳይ እስካሁን በደረሱባቸው ነጥቦች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

Read 11387 times