Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 13:13

“አፍሮጋዳ” እና ሌሊሳ ግርማ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በጥበቡ፣ በሀብቱና በዕውቀቱ ብዛት የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰለሞንን መወዳደር የሚችል ማንም አልነበረም፤ የለምም ይባላል፡፡ ሁሉ ነገር ሞልቶ የተረፈው ንጉሥ ሰለሞን፤ የምድር ላይ ድካሙን፣ የሕይወትን ፋይዳና ዓለምን ገምግሞ በመጨረሻ የደረሰበት ድምዳሜ “ሁሉም ነገር ከንቱ፤ የከንቱ ከንቱ” የሚል ሆኗል፡፡ እንዲህም ሆኖ በፈጣሪው ላይ ያለው መታመን ግን ጨርሶ አልጠፋም፡፡ ለዚህም ነው በንጉሥ ሰለሞን የተፃፉት መፃሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ አካል ሆነው ለዛሬ መድረስ የቻሉት፡፡

ሕይወትን፣ ኑሮንና የፍጥረት ዓለሙን ፋይዳ ምንነት መርምሮ የደረሰበትን ትርጉም ማኖር የጀመረው ማንም ይሁን ማን ጥያቄ ማቅረቡና ለፍለጋ መልፋቱ ሳይቋረጥ ዛሬ ላይ ተደርሷል፡፡ ነገም ከነገ በስቲያም ባሉት ቀን፣ ሳምንት፣ ወርና ዓመታት ይቆማል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ለብዙ መፃሕፍት ተሰንደው መቅረብ ምክንያት ሆኗል፡፡ በግጥም፣ በልቦለድ፣ በወግ … መልክ ተጽፈው የሚቀርቡ መፃሕፍት፤ በጭብጣቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስለዚሁ ርዕስ ነገር ያነሳሉ፡፡

የቡና እረከቦት ከበው ከሚጨዋወቱ ጎረቤታሞች እስከ መጠጥ ቤቶች ባንኮኒ አድማቂዎች፤ ሀሳባቸውን በጽሑፍ አስፍረው በጋዜጣና መጽሔት ከሚታተምላቸው እስከ ሙሉና ወጥ መጽሐፍ አዘጋጆች … በአጠቃላይ ሁሉንም የሰው ልጅ የሚያነጋግር ርዕሰ ጉዳይ ነው - የሕይወት፣ የኑሮና የፍጥረት ዓለሙ ፋይዳ ምንነት፡፡

የኑሮ ፈተና፣ ችግርና እንግልት መብዛት ሁሉም እንደየመረዳቱና የዕውቀቱ መጠን ስለ ኑሮና የሕይወት ፋይዳ እንዲጠይቅ ግድ ይለዋል፡፡ ሁሉም ግን አጥብቆ ጠያቂ አይሆንም፡፡ ስለ ኑሮና የሕይወት ፋይዳ አጥብቆ ከመጠየቅ “ሲንግል” ድራፍቱን ወደ “ደብል” ቀይሮ ማዘዝ የሚቀለው ብዙ ሰው አለ፡፡

በጥያቄ፣ ፍተሻና ምርመራ ገፍተው መሄድ የሚችሉት የሚደርሱባቸው ድምዳሜዎች ለግላቸው ያርካቸውም አያርካቸው ለሌሎች የሚያቀብሉት ነገር አለ፡፡ በዓለምና በሰው ልጆች ዕውቀት ላይ ጠብ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ አለ፡፡ ጠያቂዎቹ የሚደርሱበት መልስ አንዱን ቢያስደስት ሌላውን ሊያሳዝን ይችላል፡፡ ንጉሥ ሰለሞን “ዓለም ከንቱ፤ የከንቱ ከንቱ ናት” ሲል አባባሉ ማንንም የሚያስደስት አይመስልም፡፡ ነገር ግን ይህንን ያለው ጠቢቡ ሰለሞንም ሆነ ሌሎች ስለ ዓለምና ሕይወት እየጠየቁ መኖራቸውን አላቆሙም፡፡

ይህንን የመነሻ ሐተታ እንዳስቀድም ምክንያት የሆነኝ “አፍሮጋዳ” በሚል ርዕስ በሌሊሳ ግርማ ተዘጋጅቶ በቅርቡ ለአንባቢያን የቀረበው መጽሐፍ ነው፡፡

በአዲስ አበባ እየኖርኩ በከተማው ውስጥ ከማየው የመነጩ ሀሳቦችን ነው የምጽፈው የሚለው ሌሊሳ ግርማ፤ በመጽሐፉ በጠረዛቸው 38 መጣጥፎች ግን የተለያዩ ፀሐፍትን ሥራ እያጣቀሰ የሚጽፍባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ሰፋ አድርጎ ለመመልከት ሞክሯል፡

በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በተከታታይ ከሚያቀርባቸው ጽሑፎች ሰብስቦ ቀዳሚውን “የንፋስ ሕልም” ብሎ፣ አሁን ደግሞ “አፍሮጋዳ” በሚል ርዕስ መጽሐፉን ያሳተመው ሌሊሳ ግርማ፤ ጽሑፎቹ አነጋጋሪ በመሆናቸው በዚሁ ጋዜጣ ላይ ሌሎችን ለውይይት እና የተለያየ አመለካከታቸውን እንዲያንሸራሽሩ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ የሌሊሳ ግርማ ሀሳብና አፃፃፍ ለየት ማለቱን በ “አፎሮጋዳ” መጽሐፍ የጀርባ ሽፋን ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎችም አረጋግጠውታል፡፡

ደራሲ አዳም ረታ በሰጠው አስተያየት፤ “የሱን ጽሑፍ ከተለመዱት የሥነ-ጽሑፍ ዘዴዎች አንፃር መመልከት ይከብዳል፡፡” ሲል ገጣሚ ነብይ መኮንንም የደራሲ አዳም ረታን አባባል ይጋራና “ለሥነ-ጽሑፍ ቀስተ ደመና ያዋጣው የራሱ ቀለም መኖሩ ነው” በማለት የተለየ አሻራ ማሳረፍ ስለመቻሉ መስክሮለታል፡፡

38ቱ ጽሑፎች “የሀበሻ ባህል”፣ “ኪነጥበብ”፣ “ሀሳብ፣ ምናብ፣ ፍልስፍና” እና “ፖለቲካ” በሚሉ አራት ምድቦች ተከፋፍለው የቀረቡ ናቸው፡፡ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተፃፉ ናቸው - መጣጥፎቹ፡፡ ደራሲው በመጽሐፉ “ስለ ውስጡ በውጭ” በሚል ርዕስ መግቢያው ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ፡- “ሙሉ ፈላስፋ፤ ወይም ሙሉ መንፈሳዊ፣ አሊያም ሙሉ ከሀዲ ወይንም አማኝ አይደለሁም፡፡ ሁሉንም ባለመሆን ዝብርቅርቅ መሆኔ ግን በፅሁፍ ተቀምጦ ሲታይ እኔን ከመግለፅ ይበልጥ የዘመኑን መንፈስ ያስረዳል ብዬ አምናለሁ፡፡” ይላል፡፡

ዘመኑ ምን መንፈስ አለው? ደራሲው ዘመኑን ያየበትና የመዘነበት አንፃር ምንድነው? ሙሉ ፈላስፋ ነኝ ለማለት ምን አገደው? ግማሽ መንፈሳዊነት ምን ይመስላል? በከፊል ከሀዲነትስ እንዴት ያለ ነው? ሙሉ አማኝ አለመሆንስ? ሌላው ሁሉ ይቅርና በሁሉም ጉዳይ ላይ መዳረሻውን ሳይጠጋ እኩሌታው ላይ ለመቆም ለምን ፈለገ?

ስለ ኑሮ ሕይወትና ፍጥረት ዓለሙ ቀድመው ጥያቄ አቅርበው፣ ለፍተሻ ተግተው፣ ለምርምር ጥረው መደምደሚያ ያቀረቡ ሙሉ አማኝ ወይም ሙሉ ከሀዲ ካደረጋቸው ጋር ሚናውን ለይቶ መቀላቀል የሚፈልግ አይመስልም - ፀሐፊው፡፡ ከምርምር ፍላጎቱና አእምሮው ከሚያቀርብለት ጥያቄ ጋር ፍቅር የያዘውም ይመስላል፡፡

ለጥያቄዎቹ ማንም ያልደረሰበት ምላሽ ለማግኘት ይጓጓል፡፡ ከልማድ፣ ከባህል፣ ከተፈጥሮ ሕግ ታሳሪነት ነፃ ስለመውጣት አጥብቆ ይመኛል፡፡ እንደማይቻል እያወቀ “ለምን?” ብሎ መጠየቁን አያቆምም፡፡

“የተፈጥሮ ሕግም በሉት፣ የስበት ሕግ፣ ግራቪቲ አልያም መግነጢሳዊ ኃይል ሁሉም ለእኔ ባርነት ነው፡፡

ምክንያቱም ለኔ ‘ከዚህ ውጭ መሆን አትችልም’ ብሎ የሚገድበኝ ሕግ ሁሉ እንደ እግረ ሙቅ የሚያስረኝ ሰንሰለት ነው …

“ወደ ላይ የወረወርነው ሳንቲም መሬት ላይ ከማረፍ ውጭ ሌላ ምርጫ እንደማይኖረው፡፡ ቢኖረውም ተፈጥሮ እንደማይፈቀድለት፡፡ ወደ ላይ የተወረወረ ሳንቲም እንደ እፉዬ ገላ በንፋስ ተንሳፎ አይሄድም፡፡ ወደ ላይ የተለቀቀ እፉዬ ገላ እንደ ሳንቲም ተንቃጭሎ አይወድቅም፡፡ ባርነቱ እዚህ ላይ ነው፤ ሳትጠይቅ ከተሰጠህ የተፈጥሮ ማንነት ውጭ መሆን አለመቻል …

“ሦስተኛ መንገድ እሻለሁ፡፡ ወደ ላይ የተወረወረች ሳንቲም መሬት ስታርፍ በጠርዟ እንድትቆም፡፡ ምናልባት ያኔ ከባርነቴ ወጥቻለሁ፡፡ በራሴ መንገድ የነፃነት መንገድ ቀይሻለሁ…

“ሦስተኛ መንገድ ወይም ከሁለቱ የተፈጥሮ ተቃራኒዎች ውጭ የራሴን ነፃነት፣ የራሴን ዕጣ ፈንታ ለመፍጠር ሳንቲሟን ባለኝ ጉልበት ወደ ላይ ወርውሬአታለሁ፡፡ ሳንቲሟ ሕይወቴን፣ ምኞቴን፣ ተስፋዬን ትወክልልኛለች፡፡ ሳንቲሟ እስከ በረረች ድረስ ከተፈጥሮ ባርነት የወጣሁ እየመሰለኝ የነፃነት ህልም አልማለሁ፡፡ ከተፈጥሮ ባርነት ያመለጠ ግን ማንም የለም፡፡ ምግብ ባይበላ የማይራብ፣ ዕድሜው ቢገፋ የማያረጅ፣ ተስፋው ቢወድቅ ቅስሙ የማይሰበር … ቀኑ ሲደርስ የማይሞት …”

ሌሊሳ ግርማ ሀሳብ ላይ ካተኮሩ የማሰላሰል ጽሑፎቹ በአንዱ ያሰፈረውን ነው እንደ ማሳያ መርጬ ከላይ ያቀረብኩት፡፡ ጥያቄ እያነሳ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲህ ዓይነት ምላሽ ወይም ድምዳሜ ያቀረበ ቢመስልም በየመጣጥፎቹ ሲታይ ግን ፍለጋውን ላለማቆም በመጣር ሂደት ላይ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡

ስለ ሀብት፣ ጥበብ፣ ገንዘብ፣ ፍላጎት፣ ታዋቂነት፣ ሀሳብ፣ ጊዜ፣ ሂስ፣ ትዳር፣ ሴት፣ ባህል … በፃፋቸው መጣጥፎቹ በተመሳሳይ መልኩ ድምዳሜ ላይ የደረሰ ቢመስልም መጠየቁን አያቆምም፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ሙሉ ፈላስፋ፣ ሙሉ መንፈሳዊ፣ ሙሉ ከሀዲ ሙሉ አማኝ አይደለሁም ያለው፡፡ መጽሐፉ፤ ደራሲ አዳም ረታ እንደመሰከረለት፤ ጥልቅ ምርምር ሊደረግበት የሚገባ “ራሱን የቻለና ባለሙያ የሚጠይቅ ትልቅ የአእምሮ ሥራ ነው፡፡” ለማጠቃለያ እኔን ዘና ያሰኘኝና በመጽሐፉ ምስጋና ገጽ ላይ ያሰፈረውን በከፊል እነሆ፡- ምስጋናው ለየት ያለ እይታና አቀራረቡንም ያሳያል፡፡

ምስጋና

ሀ፡-

መ፡- መላው ቤተሰቤን (አባቴን ፕሮፌሰር ግርማ ሙሊሣን፣ እናቴን ወ/ሮ ማሪያ ጴጥሮስን እህቶቼን ኒኒ እና ሀዊ፤ ወንድሞቼን አንጋሱ፣ አዱኛ እና ያዕቆብን)

ሠ፡- ሠለሞን ገ/እግዚብሔር፣ ሠለሞን አበበ ቸኮል፣ ሠርፀ ድንግል ጣሠው

ሩ - ሪ - ራ፡- ራሴን

ቁ፡- ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ የደስታ ቀኖቼን፣ ቁመት ያላቸው ሀሳቦችን የተጋራናቸውን ሁሉ

ቡ - ቢ፡- ቢኒያም ዋሲሁን፣ ባ፡- ባህሩ ጀማል

ቱ - ቲ - ታ - ቴ - ት፡- ትዝታ (አርት)፣ ትዝ ያላላችሁኝ ባለውለቶቼን ሁሉ

ነ፡- ነብዩን (ከወሰን ግሮሰሪ)

አዲስ አድማስ ጋዜጣን እና ባልደረቦቹን (ከሀ-ፐ)፣ አምስት ኪሎ ያሉ ዘመዶቼን ባጠቃላይ - ኡ - ኢ፡- ኢዮብ ካሳ ኧ - ኤ እ፡- እግዜርን

ኩ - ኪ፡- ኪሩቤል ሳሙኤል

ዱ - ዲ - ዳ፡- ዳንኤል (ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ መፅሐፍት ቤት)

ጉ - ጊ - ጋ - ጌ - ግ፡- ግሩም ሠይፉ

 

ከልብ አመሰግናለሁ - ሂ - ሃ - ሄ - ህ - ሆ

 

 

 

 

 

Read 4159 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 13:31