Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 13:13

ኢህአዴግ “የፓርቲውን ሊ/መንበር በምስጢር መያዝ ባህሌ ነው!” እንዳይለን

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“የስዊድን ጋዜጠኞችስ ተፈቱ! የእኛስ?” (የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኛ)

“ጠ/ሚኒስትር ለመሾም ምህላ እንጂ ስብሰባ ምን ይሰራል?” (ሽማግሌ ጐረቤቴ)

አዲስ ዓመት እንዴት ነበር? (ከዋጋ ንረቱ ውጭ ማለቴ ነው) እኔ የምለው … ለአውዳመቱ  በግ ስንት እንደገባ ሰማችሁ አይደል? … በግ ነጋዴውን ጠጋ ብላችሁ ስትጠይቁት ምን ይላችኋል መሰላችሁ? “24 ውሰደው!” ግራ ይገባችሁና “ምንድነው የምትለው?” ስትሉት “ሰምተሃል!” ብሎ ሊያሾፍባችሁ ይሞክራል፡፡ (“ሼፉ” ፊልም ላይ እንዳለችው ገፀባህርይ) “አትሸጥም እንዴ?” ትሉታላችሁ ኮስተር ብላችሁ! “በቃ ከ23 ውሰደው!” ይላችኋል - ፍርጥም ብሎ፡፡ ምን ማለት መሰላችሁ? 2300 ብር ማለቱ ነው፡፡ ይታያችሁ … አንድ በግ በ2300 ብር! ለነገሩ በጉ እንኳን ሊቀር ይችላል፡፡ የማይቀረው ምን መሰላችሁ? የጤፉ ነገር ነው፡፡ ጤፉ ሊቀር ይችላል የሚባል አይደለም (አበሻ ምን ሊበላ?) በአሁኑ አካሄድ ግን ለእነ ጤፍ ምትክ ካልፈጠርንላቸው የምንከርም አልመሰለኝም! ከእነሩዝ ጋር ዝምድና ብንፈጥር ነው የሚሻለን፡፡ (የቻይና ደጀ-ጠኚ አደረግኸን ካላላችሁኝ በቀር) መቼም ጤፍ ተወደደ ብለን የረሃብ አድማ አናደርግም! ሳንነጋገር እየራበን? የምን አድማ!

ይሄን ፅሁፍ እያጠናቀርኩኝ ሳለ በኢቴቪ “ሥነፆታ” በተባለ ፕሮግራም በዓሉን አስመልክቶ ተሞክሮአቸውን የሚያጋሩ ዘመናዊ ባልና ሚስት ቀርበው ነበር፡፡ ሚስት ሲናገሩ፤ ዳቦውንም ጠላውንም ራሳችን ካላዘጋጀነው ልንል አይገባንም፤ ሲሉ በሰጡት ምክራዊ አስተያየት “እኛ ለምሳሌ ዳቦ አንጋግርም… outsource ነው የምናደርገው… ለሌላው ሰው የሥራ እድል መፍጠር አለብን” ብለዋል፡፡ (ውጭ አስጋግረን ነው የምናመጣው ማለታቸው መሰለኝ) ያለው ማማሩ አሉ! ዕድሜ ለNGO! ያልፈጠረልን ቃል የለም፡፡ (አሜሪካ እስርቤትና ገራፊዎችን outsource ስታደርግ አይቶ ለሚቋምጥ ይብላኝለት!) ግን ስንቶቻችን ነን እንደሴትየዋ outsource (በውጭ ጉልበት ማስጋገር) ማድረግ የምንችለው? (እዬዬ ሲዳላ ነው! አሉ) እናላችሁ ይቺ outsource የምትባል ነገር ለጊዜው ትለፈን፡፡ ባይሆን መንግስት የአንዳንድ ዳተኛ ተቋማቱን አመራር outsource ማድረግ ይችላል (አቅም አለዋ!)

እኔ የምለው… እነዚያ ያለፈቃድ ድንበር ተሻግረው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፤ እንዲሁም ከኦነግ ጋር ተባብረዋል በሚል ተከሰው የ7 ዓመት እስር የተበየነባቸው ሁለት ስዊድናዊ ጋዜጠኞች በነፃ መለቀቃቸውን ሰማችሁ? (በነፃ ሳይሆን በይቅርታ ማለቴ ነው!) እኔማ እሰይ፤ እንኳን ተፈቱ አልኩ፡፡ ግን ለፈረንጆቹ አዝኜላቸው እንዳይመስላችሁ (ለኒዮሊበራል አቀንቃኝ እንዴት ይታዘናል?) የእነሱ መፈታት ለአገር ገፅ ግንባታ ይጠቅማል ብዬ ነው፡፡ መቼም ከኢትዮጵያ እግራቸው ሲወጣ የሚያወሩት አይታወቅም እንጂ ከወህኒ እንደወጡ ለኢቴቪ ጋዜጠኛ እንደተናገሩት ከሆነ፣ እግር እስኪነቃ ዓለምን ቢያካልሉ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ህዝብ፣ መንግስት፣ የእስር ቤት አያያዝ፣ የይቅርታ ባህል ወዘተ የትም አይገኝም ብለዋል፡፡ እንዲህ ያለ የፈረንጅ ምርቃት ከየት ይገኛል ጃል! (ብቻ ፉገራ እንዳይሆን!)

እኔ የምለው ግን… ለፈረንጆች ብቻ የተዘጋጀ ልዩ ወህኒ ቤት አለ እንዴ? ምን ላድርግ… ምስጋናቸው ሲበዛብኝ እኮ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከእስር የተለቀቀ አንድም አበሻ እንደ ስዊድኖቹ የእስር አያያዙን ሲያመሰግን ገጥሞኝ አያውቅም (ለነገሩ አበሻ ጨለምተኛ አይደለ!)

የሆኖ ሆኖ እንኳንም አመሰገኑን … እኛም ታዲያ ለምስጋናቸው … ካባና ባህላዊ የሃገር ልብስ ሸልመን ብንሸኛቸው አይከፋም (ወይስ ሄደዋል?) ትንሽ ያሰጋኝ ምን መሰላችሁ? አገራቸው ሲገቡ “እኛ የተናገርነው ስለሌላ አገር የእስር ቤት አያያዝ እንጂ ስለ ኢትዮጵያ አይደለም” ብለው እንዳይሸመጥጡ ብቻ ነው! (ለነገሩ ኢቴቪ ድምፃቸውን ቀርፆት የለ!) የእኒህን ጋዜጠኞች ከእስር መፈታት የሰማ አንድ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኛ ወዳጄ ምን አለ መሰላችሁ? “የስዊድን ጋዜጠኞቹስ ተፈቱ… የእኛስ?” ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡ (የኢህአዴግ ተወካይ እመስለዋለሁ እንዴ?) እኔም ግን ዝም አላልኩትም፡፡ አሰብኩ አሰብኩና “እሱማ ፖለቲከኞችም እኮ አሉ!” አልኩት፤ (በሽብርተኝነት ተከሰው የረዣዥም ዓመት እስር የተፈረደባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ማለቴ ነው) (እድገታችን ዙሪያ ገብ እንዲሆን እኮ ነው!)

እኔ የምለው ግን … አዳዲስ ደረጃቸውን የጠበቁ ወህኒ ቤቶች የመገንባት ዕቅድ በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን … ላይ አልተካተተም እንዴ? ሰሞኑን “ኢህአዴግ ጠ/ሚኒስትር እያሰሰ ነው!” የሚል ርእስ የሆነ ቦታ ወጥቶ አይቻለሁ፡፡ ለምን ያስሳል? ይመርጣል እንጂ! ሁለት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች ይሾማሉ የሚባል ወሬም ሰምቻለሁ፡፡ በአዲሱ የድህረ መለስ አስተዳደር ጠ/ሚኒስትሩና ምክትሉ እኩል ሥልጣን ይኖራቸዋል ሲባልም የሰማሁ መሰለኝ (አዲስ አገር ነው እንዴ የምናቋቁመው?) በኋላማ ኢህአዴግ - “በጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት የተነሳ አንድም የሚለወጥ ነገር የለም” ሲል የተናገረው ትዝ አለኝና እፎይ አልኩ፡፡ ለነገሩ ምንም የሚያሰጋን ነገር እኮ የለም! (ዕድሜ ለህገ-መንግስታችን!) በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር ሲካሄድ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ ብቻ ነው ትንሽ የፈራነው (“የሥልጣን ባለቤት ህዝብ ነው!” የምትለዋን መፈክር ስወዳት!)

አንድ የ60ዎቹ የተማሪ አብዮት አቀጣጣይ የነበረ ወዳጄ፤ አንዱ ሁለት ሌላው ደግሞ ሦስት ጠ/ሚኒስትሮች ይሾማሉ እያለ ሲያወራ ሰምቶ ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? “እኔ አስራ ሦስትም ጠ/ሚኒስትሮች ቢሾሙ ግዴለኝም… ብቻ በቅጡ ይምሩን!” (እሱም አበዛው - ለአንድ አገር 13 ጠ/ሚስትሮች? እጩዎቹ አራት አራት መሰሉት እንዴ? ወይስ ምርጫውን ህዝባዊ ማድረጉ ነው?)

የሹመት ነገር ሲነሳ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የእንቁጣጣሽ እለት በኢቴቪ የተነገረው የመከላከያ አዛዦች የሹመት ዜና! (ተንበሸበሹ እኮ!) እኔን ያልገባኝ ግን … ኢቴቪ ምስል - አልባ  ዜና ማቅረቡ ነው! (ካሜራዎቹ ሁሉ ተበላሹበት ወይስ የካሜራ ባለሙያዎቹ ጠፉበት?) ሌላው ቢቀር በሞባይል የተነሳ ፎቶ እንኳን እንዴት ጠፋ? የኔ ነገር! ታሪክ ነው ብዬ እኮ ነው! (ትንፋሼ ተቀርፆ ይቀመጥ ማልቀሻ …ያለው ማን ነበር?)

ዘወትር ባገኙኝ ቁጥር ሦስት መንግስት በልቼአለሁ እያሉ የሚያደርቁኝ አንድ ጐረቤቴ አሉኝ (ጀግንነት መሰላቸው እንዴ?) “አሁንም ቤተመንግስቱ ባዶ ነው?” ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ጠ/ሚኒስትር አልተሾመም ወይ ሊሉ ፈልገው ነው፡፡ አዲሱ የአገራችን ጠ/ሚኒስትር የሚታወቀው ከኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ እንደሆነ ነገርኳቸው… “ስብሰባ?” ብለው አምባረቁብኝ፡፡ “ስብሰባ ምን ይሰራል… በዚህ ጊዜ የሚያስፈልገው ምህላና ፀሎት ነው እንጂ!” አሉኝ ኮስተር ብለው፡፡ ሳቄን ለማፈን ሞከርኩ - ባይሳካልኝም፡፡ አዛውንቱ ግን የከሸፈውን ሙከራዬን አላጤኑትም፤ ስለዚህ ሃሳባቸውን ቀጠሉ “አልሰማህም እንዴ? አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ ፀሎትና ምህላ እየተደረገ እኮ ነው” አሉኝ፡፡ ሃይማኖትና መንግሥት ለየቅል ናቸው ልላቸው ፈልጌ ውዝግብ ከመፍጠር በቀር ምንም ፋይዳ እንደሌለው አሰብኩና ዝምታን መረጥኩ፡፡ ያኔ ነው በፌስ ቡክ ላይ ፖስት የሚደረጉ በሚመስሉ ሃሳቦች የተጥለቀለቅሁት፡፡ ጉዳዩ ደግሞ ያው የፈረደበት የጠ/ሚኒስትሩ ሹመት ነበር፡፡ መጀመርያ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ፤ “መለስ ሚኒስትሮችን ከተቃዋሚዎች የመሾም እቅድ ነበራቸው” ያሉኝ ትዝ አለኝና ተቆጨሁ (ባደረጉት ነበር ብዬ!) ግን አሁን ኢህአዴግ በሆነ ተአምር ከተቃዋሚ ጐራ ጠ/ሚኒስትር ቢያጭስ? ምን ትላላችሁ? (ልብ አድርጉ! ቢያጭ ነው ያልኩት) ቆየት ብዬ ኮሚክ ሀሳብ መጣብኝ፡፡ “ጠ/ሚኒስትር ከዳያስፖራ ያስስ ይሆን?” የሚል፡፡ እንዳትሳሳቱ … ኢህአዴግ ከዳያስፖራው ለጠ/ሚኒስትርነት የሚሆን ሰው የሚያፈላልገው ከራሱ ፓርቲ ሰው አጥቶ አይደለም፡፡ ሥልጣን የማጋራት የረዥም ጊዜ ህልሙን እውን ለማድረግ መልካም አጋጣሚ ነው በሚል ካለው ቀና አገራዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ (የሥልጣን መተካካት በሚለው ስትራቴጂው እኮ ዓለም ያደንቀዋል!)

ይሄ ሁሉ እንግዲህ የእኔ የብቻዬ ሃሳቦች ናቸው፡፡ እውነቱን የምናውቀው ከኢህአዴግ የም/ቤት ስብሰባ ነው፡፡ ለፓርቲው ሊ/መንበርነትና ምክትል ሊ/መንበርነት የመረጣቸውን ሰዎች የምንሰማው ከእሱ ብቻ ነው፡፡ ብቻ የፓርቲዬ ባህል አይፈቅድልኝም ብሎ የሾማቸውን ከመግለጽ እንዳይታቀብ! (ባህሌ ነው ካለ ምን ይደረጋል?) መልካም ዘመን ለእኔም ለእናንተም፤ ለኢህአዴግም ለተቃዋሚዎችም እመኛለሁ፡፡

 

 

Read 3932 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 13:31