Saturday, 13 November 2021 12:28

የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኩባንያው ከቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲወጣ ተወሰነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኘውና በጨርቃ ጨርቅ ምርት ላይ የተሰማራው ኬ.ኢ.አይ ኢንዱስትሪ ኢንጅነሪንግ ኮንሰልታንሲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ የፓርኩን ህገ ደንቦች ባለማሟላቱ  ከፓርኩ ለቆ እንዲወጣ ተወሰነ።
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ  ፓርክ በሼድ ቁጥር 18 ውስጥ በሚገኘውና  በኮሪያዋ ባለሃብት ሁዋን ራዩ ባለቤትነት የሚመራው ፋብሪካው ለረጅም ጊዜ  ያለ ስራ በመቆየቱና የኩባንያው የስራ ብቃትና አቅም ለፓርኩ የሚመጥን ባለመሆኑ ከፓርኩ ለቆ እንዲወጣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማናጅመንት ኮሚቴ ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2014 መወሠኑን የኮሚሽኑ አንድ ከፍተኛ የስራ ሃላፊ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ለረጅም ዓመታት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ መቆየቱ የተጠቆመው ኩባንያው ከመንግስት በኩል በርካታ ድጋፎችን እያገኘ የቆየ ቢሆንም ዝቅተኛውን የኤክስፖርት መመዘኛ ማሟላት አልቻለም ተብሏል፡፡
ኩባንያው በሼዱ ውስጥ ያሉትን ማሽነሪዎች አውጥቶ ሌሎች ብቃቱ ያላቸው ኩባንያዎች  እንዲጠቀሙበት በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማናጀመንት መወሰኑንና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ሂደቱን እንዲያስፈፅም ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡
ኩባንያው ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ከመውጣቱ በፊት የግብር ጉዳይ፣የኦዲትና የመሳሰሉት ሂደቶችን ማለፍ እንደሚጠበቅበት የገለፁት ሃላፊው፤ ኩባንያው የፓርኩን ደንቦች በመጣስ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ሲሠጡት እንደነበር አመልክተዋል፡፡
ኮርያዊው ባለሃብት ሁዋን ራዩ በሚመራው ኩባንያና በግለሰቡ ላይ የተለያዩ የወንጀል ጥቆማዎች ለቦሌ ፖሊስ መምሪያ መቅረቡንም ለአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል የቀረቡ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡
ኬ.ኢ አይ ኢንዱስትሪ ኢንጂነሪንግ  ኮንሰልታንሲ ሃ/የተ/የግ/ማህበር ፈጽማቸዋል ተብለው በፖሊስ ከቀረቡ ጥቆማዎች መካከል ጊዜው ባለፈ የንግድ ፍቃድ መስራት፣ የማማከር ፍቃድ ሳይኖረውና የማማከር አገልግሎት ሳይሰጥ ክፍያ መቀበልና ክፍያውን ወደ ውጪ ማሸሽ ከሰራተኞች የሚሰበሰብ የጡረታ ገንዘብ ሊመለከተው አካል ያለማስተላለፍ የአደይ አበባ ቁጥር 2 ፋብሪካ በኢንቨስትመንት የወሰዱበት መንገድ የተጭበረበ ነው፣ ባለሃብቱ በኢትዮጵያ የመኖሪያ ፍቃዳቸውን ሳያድሱ ከሁለት ዓመት በላይ እየኖሩ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው፡፡


Read 1215 times