Sunday, 07 November 2021 19:11

ዳሽን ባንክ የውጪ ምንዛሬ ማንቀሳቀሻ ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ለሰራተኞቹ ዘመናዊ ጂም ገንብቷል
                                       
              የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ፈር ቀዳጅ የሆነው ዳሽን ባንክ ደንበኞቹ በውጭ፤ አገር ሲንቀሳቀሱ በውጪ ምንዛሬ የሚጠቀሙበትን አዲስ ቴክሎጂ ይፋ አደረገ።
“ምንጊዜም አንድ እርምጃ ቀዳሚ” በሚል መሪ ቃሉ የሚታወቀው ባንኩ፤ ከአሜሪካን ኤክስፕረስ ጋር በመተባበር ነው “ዳሽን አሜሪካን ኤክስፕረስ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የዴቢት አገልግሎት ካርድ ነው ይፋ ያደረገው። “ዳሽን አሜሪካን ኤክስፕረስ” ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ፍሰት ለሚያስተናግዱ ተቋማት በጣም አስፈላጊና አመቺ ካርድ መሆኑን የገለፀው ባንኩ፣ ደንበኞች ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ከውጪ ምንዛሬ አካውንታቸው በቀላሉ ገንዘብ በማውጣት ግብይት መፈጸም ያስችላቸዋል  ተብሏል።
እንደ ባንኩ ሃላፊዎች ገለጻ፤ ካርዱ ከዚህም በተጨማሪ ከጥሬ ገንዘብ ውጪ ግብይት ለመፈጸም የሚያስችል ሲሆን ጥሬ ገንዘብ ይዞ በመንቀሳቀስ ከሚመጡ የትኞቹም ስጋቶችና ችግሮች ደንበኞችን እፎይ ያሰኛልም ተብሏል።
አሜሪካን ኤክስፕረስ ካርዱን በመጠቀምም፣ በዓለም አቀፍ አሜሪካን ኤክስፕረስ የኤቲኤም ኔትወርክ በኩል የንግድ ሥራዎቻቸውን ማከናወን እንደሚችሉም ተጠቁማል።
የዳሽን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር ዳሽን ባንክ የዘርፉ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እድገትና የህግ ማሻሻያዎች የፈጠሩትን እድል በመጠቀም ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠትና ይህን መሰል የዘርፉን የፈጠራ ውጤቶች በማቅረብ ሁሌም ቀዳሚ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።
ወደ ውጪ ለሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን በቀላሉ ክፍያ ለመፈጸም እንዲችሉ እድል የፈጠረውን ይህን ካርድ በማስተዋወቁ ዳሽን ባንክ ከፍተኛ ኩራት ይሰማዋል ሲሉም አቶ አስፋው ዓለሙ አክለዋል።
በአፍሪካ የአሜሪካን ኤክስፕረስ ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ጀምስ ዋይናይና በበኩላቸው፤ ካርዱ ኢትዮጵያዊያን ይበልጥ አስተማማኝና ቀላል በሆነ መንገድ ዓለምአቀፍ ክፍያ መፈፀም እንዲችሉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል፤ ባንኩ የሰራተኞቹን ምርታማነት ለማሳደግና ጤናቸውን ለመጠበቅ በማሰብ በዋናው መስሪያ ቤቱ 16ኛው ወለል ላይ እጅግ ዘመናዊ ጂምናዚየም የገነባ ሲሆን እያንዳዱ ሰራተኛ እንደየድሜው፣ የጤናው ሁኔታና የሰውነቱ ክብደትና ቅለት ሁሉንም ዓይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በመስራት ጤናውን የሚጠብቅበት ነው ተብሏል። ጂምናዚየሙ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የተለያዩ  የአካል እንቅስቃሴ መስሪያ ማሽኖች የተገጠሙለት ሲሆን ለማሽኖቹ ብቻ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉም ተገልጿል።
ጂምናዚየሙ ሳውና ባዝና፣ ሻወር ቤትና ሌሎች  ተያያዥ አገልግሎቶችም የተሟሉለት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ባንኩ በዚሁ ወለል ላይ የህፃናት ማቆያን በዘመናዊ መልኩ ያደራጀ ሲሆን በዚሁ ማዕከል ህፃናቱ የሚታከሙበትና የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ የሚሰጥበት ክሊኒክም ከፍቷል።


Read 1663 times