Tuesday, 09 November 2021 00:00

ኤለን መስክ ከ300 ቢ. ዶላር በላይ ያፈራ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ማይክሮሶፍት በ2.45 ትሪሊዮን ዶ. የገበያ ዋጋ በአለም 1ኛ ሆነ

            ባለፈው ሰኞ ብቻ በአስር ቢሊዮኖች ዶላር ተጨማሪ ሃብት በማፍራት አጠቃላይ ሃብቱን ወደ 306.4 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ያደረገው የአለማችን የወቅቱ ቁጥር አንድ ቢሊየነር ኤለን መስክ፤ በአለማችን ታሪክ ከ300 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያፈራ የመጀመሪያው ሰው ሆኖ መመዝገቡን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
ታዋቂው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያ የቴስላ የአክሲዮን ዋጋ ሰኞ ዕለት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ፣ የኩባንያው መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ እንዲሁም የ23 በመቶ ድርሻ ባለቤት ኤለን መስክ በዕለቱ ብቻ ተጨማሪ 8.6 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ማግኘቱን ነው ዘገባው ያስነበበው፡፡
የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ በ190 ቢሊዮን ዶላር፣ የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ቤትስ ደግሞ በ165 ቢሊዮን ዶላር በአለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው ይገኛሉ፡፡
በሌላ የቢዝነስ ዜና ደግሞ፣ ታዋቂው የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት ባለፈው አርብ የወቅቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለከፍተኛ ዋጋ ኩባንያ ለመሆን መብቃቱን የዘገበው ፎርብስ መጽሄት፣ የኩባንያው የገበያ ዋጋ 2.45 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን አስነብቧል፡፤
ከአንድ አመት በላይ በ1ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የዘለቀው አፕል ኩባንያ ባለፈው አርብ ይፋ ባደረገው የፋይናንስ ሪፖርቱ ገቢው መቀነሱን መናገሩን ተከትሎ የኩባንያው የአክሲዮን ዋጋ በ4 በመቶ ያህል ማሽቆልቆሉንና በዚህም አጠቃላይ የገበያ ዋጋው ወደ 2.3 ትሪሊዮን ዶላር በመቀነሱ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
የዝነኛው አይፎን ሞባይል አምራች የሆነው አፕል በአለማችን ታሪክ ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የገበያ ዋጋ ያስመዘገበ የመጀመሪያው ኩባንያ መሆኑን ያስታወሰው፣ ከ2 ትሪሊዮን በላይ ሃብት በማስመዝገብም ቀዳሚው እንደነበርና በሐምሌ ወር 2020 አንስቶ ደግሞ የአለማችን ቀዳሚው ባለከፍተኛ የገበያ ዋጋ ኩባንያ እንደነበር አክሎ ገልጧል፡፡
የገበያ ዋጋቸው ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ከደረሰ ሌሎች ታላላቅ የአለማችን ኩባንያዎች መካከል፣ የጎግል ባለቤት አልፋቤት፣ አማዞን እና ታዋቂው የኤሌክትሪክ መኪኖች አምራች ኩባንያ ቴስላ እንደሚገኙበትም የፎርብስ ዘገባ አስታውቋል፡፡

Read 8097 times