Sunday, 07 November 2021 17:09

"ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ"

Written by  ይነጋል በላቸው
Rate this item
(0 votes)

 እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርስ የትግራይን ሕዝብ በጦር ሜዳ በማሰለፍ፣ ለሞትና ለአካል ጉዳት በመዳረግ፣ ሰውን እንደ አንድ የጦር መሳሪያ በመጠቀም፣ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ትሕነግ አቅዶና አልሞ መነሳቱን ስሰማ ራሴን ይዤ ነው የጮህኩት። ለካ በጦር ሜዳ ለሚረግፈው ሰው ግድ የሌለው ለዚህ ነው ብያለሁ።
ለራሱ ወገን ምንም አይነት ርህራሄና ሃዘኔታ ከማይሰማው ሃይል ጋር እንዴት ነው መፋለም የሚቻለው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
ጦርነቱን ትሕነግ ብቻውን አይደለም እየተዋጋ ያለው፡፡ በመረጃ፣ በዲፕሎማሲና በፕሮፓጋንዳ ከጎኑ የተሰለፉ ብዙ ሃይሎች እንዳሉም በተደጋጋሚ ታይቷል። ሰሞኑን ደግሞ ያልዘመመውን ወደቀ እያሉ እየዘገቡ መሆኑንም እያየንና እየሰማን ነው። የመጀመሪያው  እርምጃ፣ ለፕሮፓጋንዳ ዘመቻው ጆሮ በመንፈግ፣ የአጸፋ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በመክፈት  መመከት ነው።
ትግራይ ተዋሳኝ በመሆኑ የአማራና የአፋር ሕዝብ የችግሩ ገፋት ቀማሽ ሆኗል፡፡ የአማራ ሕዝብ ደግሞ በትሕነግ ቀዳሚና ዘላለማዊ ጠላት ተደርጎ የተፈረጀ መሆኑን ተከትሎ፣ በዚያ ልክ  ለፍልሚያው እራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ የአፋርም ሆነ የአማራ ሕዝብ፣ በትህነግ የተደገሰላቸው የጥፋት ድግስ ምን ያህል  የከፋ እንደሆነ በግልጽ ሊነገራቸው  ይገባል፡፡ እንቅስቃሴያቸውም ከሆይ ሆይታ ርቆ መሬት የወረደና የረገጠም መሆን ይኖርበታል፡፡
ትሕነግ በስንቅ በትጥቅና በፕሮፓጋንዳው አስቀድሞ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ በተለይ በፕሮፓጋንዳው ማዕከላዊ መንግስትንም ጭምር እየተፈታተነ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁለቱ ክልሎችም እራሳቸውን በዚህ መስመር ማደራጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ለትግራይ ህዝብ በትግርኛ ቋንቋ፣ የአማራውንና የአፋሩን ህዝብ አላማና ፍላጎት የሚነግሩ የቅስቀሳ ሥራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ አማራውም ሆነ አፋሩ ጠባቸው ሊያጠፋቸው ከተነሳው የትሕነግ ቡድን ጋር እንጂ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አለመሆኑን ደግመው ደጋግመው መግለጽ ይኖርባቸዋል።
ሁለቱ ክልሎች አገር አማን ብለው የተቀመጡ ክልሎች እንደነበሩ የታወቀ ነው። የነበራቸው የታጠቀ ኃይል ሚሊሽያና ልዩ ኃይል ነው። እሱም ያለውና የነበረው ትጥቅ ከተከፈተባቸው ጥቃት ጋር የተመጣጠነ አለመሆኑ ደግሞ በግልጽ የሚታወቅ ነው። ስለዚህም የጀመሩትን ተጨማሪ ኃይል የማሰልጠን ሥራ መቀጠል አለባቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራሉ የመከላከያ ሰራዊት፣ የሁለቱን ክልሎች የሚሊሺያና ልዩ  ኃይል የሚጎድላቸውን ትጥቅ በማሟላት እንዲሁም በስልጠናና በመረጃ በማብቃት  ሊያግዛቸው ይገባል፡፡
አሸባሪው ትሕነግ ለዘመናት በዘረፈው ገንዘብ፣ ከማዕከላዊ መንግሥት በሥልጣኑ በወሰደው የጦር መሳሪያ ፣ የትራንስፖርትና የመገናኛ መሳሪያ አቅሙ የደነደነ  መሆኑ በአጽንኦት ሊሰመርበት ይገባል። ቀደም ሲል እንደገለፅኩት፤ ሁለቱ ክልሎች ችግሩ ድንገት የደረሰባቸው እንጂ የተዘጋጁበት አይደለም። የፌደራሉ መንግስት ድጋፉን  በስንቅና በትጥቅ ብቻ ሳይሆን  በበጀትም ማድረግ ይኖርበታል፡፡
እስከ አሁን በነበረው የጦርነት ሂደት በሁለቱ ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከአዲስ አበባ መስተዳደር ጀምሮ ሁሉም ክልሎች በአይነትና በገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል፤ የተወሰነ የሰው ሃይልም ወደ ግንባር መላካቸው ይታወሳል፡፡ አሁን ችግሩ ያለበት ሁኔታ ግን ድጋፉን በዚህ መንገድ በመቀጠል መቋቋም የሚቻል እንዳልሆነ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ እናም የትህነግን ወረራ ባለበት ለመግታት ቀጥሎም ወረራውን ለመቀልበስ ከሁሉም ወገን ፈጣን እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቃል፡፡  
የትግራይ ህዝብ፤ የአማራም የአፋርም የኢትዮጵያም ሕዝብ ጠላት አይደለም፡፡ በየትኛውም አካባቢ ያሉ በትሕነግ ሥር የተሰለፉ ተጋሩዎች እራሳቸውን ከአሸባሪው ቡድን እንዲነጥሉ በማያሻማ  ቋንቋ መንገር ያስፈልጋል፡፡ አልነጠልም ብሎ ከትህነግ ጎን የቆመ ሁሉ ግን በጠላትነት ተሰልፈዋል ማለት ነው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በትህነግና በተከታዮቹ ላይ “ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ” ብሎ መነሳት አለበት፡፡ መነሳቱ ጥፋትም ሃጢያትም አይደለም፡፡ የበግ ቆዳ ለብሰው በሕዝብ መሀል የሚሹለኮለኩ የትሕነግ ቀበሮዎች ጊዜ ሲፈቅድ ምን እንደሚፈጽሙ አይተናል፡፡


Read 1477 times