Saturday, 06 November 2021 00:00

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን ይላል?

Written by 
Rate this item
(0 votes)


      የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የአገርን ህልውና እና ሉዓላዊነት እንዲሁም የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን፡-
1. በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል መከላከያ ኃይልን ወይም የትኛውንም ሌላ የፀጥታ አካል በማሰማራት ሰላምና ፀጥታ እንዲያስክብሩ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፤
2. እድሜያቸው ለወታደራዊ አገልግሎት የደረሱና የጦር መሳርያ የታጠቁ ዜጎች ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ፣ ወታደራዊ ግዳጅ እንዲቀበሉ ወይም ይህን ማድረግ የማይችሉ ሲሆን በአማራጭ ትጥቃቸውን ለመንግሥት እንዲያስረክቡ ሊያዝ ይችላል፤
3. የሰዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን ይችላል፤
4. ማናቸውም የሕዝብ የመገናኛና የሕዝብ መጓጓዣ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል፤
5. ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ አዋጅ ተፈጻሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ይችላል፤
6. ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅት ንብረት የሆነን ማንኛውንም ቤት፣ ህንጻ፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማንኛውንም ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ ይችላል፤ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ የጦር መሳሪያዎችን መውረስ ይችላል፤
7. ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቀቁ ለማዘዝ ይችላል፣
8. ከፍተኛ የፀጥታ ችግር እና ስጋት በተፈጠረባቸው የአገሪቱ ክፍሎች የአካባቢ አመራር መዋቅርን በከፊልም ሆነ በሙሉ፣ ማገድ፣ መለወጥና በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ አመራር መተካት ይችላል፤
9. በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራልም ሆነ የቁስ ድጋፍ ያደርጋል ብሎ የሚጠረጥረውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት እንቅስቃሴ በሚመለከተው ባለሥልጣን በኩል እንዲታገድ ወይም ፍቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል፤
10. በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራል ድጋፍ ያደርጋል ብሎ የሚያምነውን የመገናኛ ብዙኃንን ወይም ጋዜጠኛ በሚመለከተው ባለሥልጣን በኩል እንዲታገድ ወይም ፍቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል፤
የተከለከሉ ተግባራትና ግዴታዎች
1. ሁሉም ሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በአዋጁ መሰረት የሚያወጣቸውን መመሪያዎችና የሚሰጣቸውን ትዕዛዞች የመቀበል ግዴታ አለበት።
2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አላማ የሚቃረን፣ የሚቃወምና ለሽብር ቡድኖች አላማ መሳካት አስተዋፅኦ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጭት የተከለከለ ነው።
3. በየትኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የገንዝብ፣ የመረጃ፣ የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።
4. አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በተዋረድ ውክልና ከሰጣቸው አካላት ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።
5. ከመከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ወይም ሌሎች ፈቃድ ከሚሰጣቸው የፀጥታ አካላት ወይም ከእነዚህ አካላት እውቅና እና ፈቃድ ውጭ ማናቸውንም የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
6. በከተሞች አካባቢ የነዋሪ መታወቂያ የመንጃ ፈቃድ፣ የሠራተኛ መታወቂያ፣ ፓስርፖርት ወይም ከእነዚህ ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው። [ዜጎች እነዚህን ሰነዶች የሚያገኙበት መንገድ ተመቻችቷል]
7. ማንኛውንም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ የሥራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀም የተከለከለ ነው።
8. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ሰበብ በማድረግ የግል ጥቅም ለማግኘት ስልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል እርምጃ መውሰድ የተከለከለ ነው።
የወንጀል ተጠያቂነት
1. የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎችና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም እንደጥፋቱ ክብደት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።
2. የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎችና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን በመተላለፍ የተፈፀመው ወንጀል በሌሎች ሕጎች ከዚህ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ የከበደው ቅጣት ተፈጻሚ ይሆናል።
3. በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የተፈፀሙ የአዋጁና በአዋጁ ማዕቀፍ የወጡ መመሪያዎች ጥሰቶች የአዋጁ ተፈጻሚነት ጊዜ ቢያበቃም፣ የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነት በመደበኛው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሰረት ይቀጥላል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም  ጀምሮ  ለስድስት ወራት የሚቆይ ነው።

Read 1028 times