Wednesday, 03 November 2021 14:29

ዋሊን የተሰኘ አዲስ የቢራ ምርት ወደገበያ ገባ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

የካንጋሮ ኢንደስትሪያል ግሩፕ አካል የሆነው ዩናይትድ ቤቨሬጅስ አክሲዮን ማኅበር ዋሊን የተሰኘ አዲስ የቢራ ምርት ለገበያ ማቅረቡ ተገለፀ። በኦሮሚያ ክልል ሞጆ ከተማ ከ88 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በሆነ መነሻ ካፒታል ዘመናዊ የቢራ ፋብሪካ በማቋቋም ከሶስት አመት በፊት ስራውን በይፋ የጀመረው ይኸው ድርጅት፤ የማምረት አቅሙን የሚያሳድግ የፋብሪካ ማስፋፊያ ማጠናቀቁን እንዲሁም የአዲሱን የዋሊን ቢራ ወደገበያ መቅረብ በማስመልከት በስካይላይት ሆቴል ደማቅ ፕሮግራም አካሂዷል። በፕሮግራሙ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ታዋቂ የንግዱ አለም ሰዎች የተገኙ ሲሆን የኦሮምኛ ቋንቋ ስያሜ ያለው አዲሱ ዋሊን ቢራ ለታዳሚዎች የማስተዋወቅና የቅምሻ ፕሮግራም ተደርጓል።
አዲሱ ዋሊን ቢራ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለውን ተጠቃሚ ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን የድርጅቱ ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ ተሬሳ ኡርጌሳ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የበርካታ ባህልና እሴቶች ባለቤት ናት ያሉት ኃላፊው ድርጅቱ አቅም በፈቀደ መጠን ልዩ ልዩ ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴቶችን በማጉላት ህዝባችን የኔ ብሎ የሚቀበላቸውን ምርቶች ወደገበያ ማቅረባችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ኃላፊው አያይዘው እንደገለፁት ድርጅቱ ያለውን የምርት አይነቶች የበለጠ በማስፋት፣ ሀገር በቀል እሴትን ከሚያንፀባርቁ ምርቶች በተጨማሪ በአለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆኑ የመጠጥ ምርቶችን አምርቶ ለሀገራችን ገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳለውም አስታውቀዋል። አሁን ለገበያ የቀረበው ዋሊን ቢራ ፕሪሚየም ላገር ቢራ ሲሆን በተመረጡ የሀገራችን ከተሞች ለተጠቃሚዎች መቅረብ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል። አብሮነት የሚል አቻ ትርጉም ባለው ዋሊን የተሰየመው አዲሱ ቢራ እጅግ ዘመናዊ በሆነው የመጨረሻው የቢራ ጠመቃ ቴክኖሎጂ፣ በታዋቂው የክሮንስ ጀርመን ማሽነሪና ከ50 ዓመታት በላይ የጠመቃ ልምድ ባላቸው አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች የሚዘጋጅ በመሆኑ ጥራትን የሚያከብረው ህዝባችን ይህንን ልዩ ምርት በደስታ እንደሚቀበለው አንጠራጠርም ሲሉ የገለፁት ደግሞ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤፍሬም ይርጋ ኃይሌ ናቸው።
ዩናይትድ ቤቨሬጅስ አክሲዮን ማህበር በካንጋሮ ፕላስት እና በዩናይትድ አፍሪካ ቤቨሬጅስ ጥምረት እ.ኤ.አ በ2016 የተመሰረተ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። ካንጋሮ ኢንደስትሪያል ግሩፕ ወይንም ይርጋ ኃይሌና ቤተሰቦቹ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሪል ስቴት፣ በኢምፖርትና ኤክስፖርት ንግድ፣ በግብርናና መሰል የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ተሰማርቶ ላለፉት 60 ዓመታት በሀገራችን ሲሰራ የቆየ ሀገር በቀል ድርጅት ነው።

Read 3799 times