Wednesday, 03 November 2021 00:00

“ሽብርተኛ እየተባባሉ መፈራረጁን አቁመን እንነጋገር”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የታጠቁና በውጊያ ላይ ያሉ ተቃዋሚ ቡድኖችን ያሳተፈና ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሄራዊ ውይይት እንዲካሄድ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፊኮ) ጠየቀ፡፡
መንግስት በአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል መግባባትን ለመፍጠር ሁሉን አካታች ውይይት በሚቀጥለው እንደሚካሄድ አስታውቋል። ኦፊኮ በዚህ ሁሉን አካታች ውይይት ውስጥ ለመሳተፍ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተ መግለጫ ሰሞኑን አውጥቷል፡፡ በዚህ መግለጫውም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአፋጣኝ እንዲቆምና ተፋላሚ ወገኖች ለውይይት እንዲቀመጡ፣ ብሄራዊ ውይይቱ ታጣቂ ተቃዋሚ ቡድኖችን ያካተተ እንዲሆን፣ ውይይቱ በገለልተኛ ነፃ አካላት እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚል ባለ አራት ነጥብ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የኦፌኮን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹን ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ አነጋግራቸዋለች።
በብሔራዊ ውይይቱ ላይ ለመሳቱፍ ያቀረባችኋቸው አራቱ ቅድመ ሁኔታዎች ተቀባይነትን አግኝተው በውይይቱ ላይ እንድንሳተፍ ያደርገናል ብላችሁ ታስባላችሁ?
ለማካሄድ የታሰበውን እውነተኛና ሀቀኛ ብሔራዊ ውይይት ከሆነና አገሪቱ ከገባችበት ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያወጣት የሚችል ሁሉን አቀፍ ውይይት ከሆነ፣ ያቀረብናቸውን አራት ቅድመ ሁኔታዎች መቀበል የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም፡
ካቀረባችሁት ቀድመ ሁኔታ መካከል አንዱ ጦርነቱ እንዲቆምና ተፋላሚ ወገኖች ለወይይት እንዲቀመጡ የሚል ነው። በህውሃት ሃይሎችና በመንግስት መካከል የሚደረገውን ጦርነት ማለታችሁ ነው?
አዎ፣ እሱንም የሚያካትት ነው። ግን ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ፣ በአሁኑ ወቅት ጦርነት የማይካሄድበት የአገሪቱ ክፍል የለም። በአፋርና በሱማሌ በኩል፣ በኦሮሚያ ሁሉም አካባቢዎች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ 200 ሰዎች እንደ ጎመን በአንድ ቀን የታጨዱበትና  ተጠያቂ  እንኳን የሌለበት፣ በደቡብ፣ በጋምቤላ፣ በአማራና ቅማንት በኩል… በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ጦርነት አለ። እነዚህ ሁሉ ጦርነቶች ቆመው ሁሉም ወገን በአገሩ ጉዳይ ላይ ቁጭ ብሎ የጋራ ውይይት ሊያደርግ ይገባል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከፈረጃቸውና በርካታ ንፁሃንን በግፍ እየገደሉ ካሉ ሽብርተኛ ከተባሉ ወገኖች ጋር እንዴት ውይይት ማድረግ ይቻላል ብለው ያምናሉ?
ማነው አሸባሪ ያላቸው? የተወካዮች ምክር ቤት ነው አይደል። የዚህ ምክር ቤት አባላት ደግሞ ከአንድ ፓርቲ የወጡ ናቸው። የጠሉትን ሰው የተለያየ የጅብ ቆዳ ማልበስ የተለመደ ተግባር ነው። ይህ መፈራረጅ ቆሞ ሁሉም ወደ መድረክ ይምጣ ነው የምንለው። የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሁሉም ኢህአዴግ የነበሩ አይደሉም? ኢህአዴግ ደግሞ አሁን ብልፅግና ሆኗል። ለምንድነው እውነቱን የማንነጋገረው። እነዚህን ወገኖች ሽብርተኛ ያሏቸው የብልፅግና አባላት ናቸው።
እዚህ ላቋርጥዎትና እነዚህ ሁለት ቡድኖች ማለትም ህውሃት እና ኦነግ ሸኔ በንጹሃን ላይ እየፈጸሙት ያለው ወንጀልና ዘግናኝ ጭፍጨፋ “አሸባሪ” ሊያሰኛቸው አይችልም እያሉኝ ነው?
 በእውነት እንነጋገር ከተባለ በየአካባቢው የሚደረገውን ጭፍጨፋና ሽብር የሚያካሂደው አንድ አካል ብቻ ነው። በአሁኑ ወቀት በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ ለተካሄደው ጭፍጨፋና ለሞቱ ሰዎች ሁሉ ተጠያቂው ገዥው መንግስት ነው።
በአገራችን አብዛኛው አካባቢዎች በንፁሃን ላይ የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን፣ ግድያዎችንና የንብረት ውድመቶች የተፈጸሙት መንግስት አሸባሪ በሚል በፈረጃቸው ቡድኖች ሆኖ እያለ እንዴት መንግስት ለግድያዎቹና ለተፈጸሙት ወንጀሎች ተጠያቂ ሊሆን ይችላል? ቡድኖቹ አሸባሪ ሊባሉ አይገባቸውም ማለትስ እንዴት እንችላለን?
ከሶማሌ የተፈናቀሉትን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኦሮሞዎች፣ ከጉጂና ጌዲኦ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ያፈናቀለው መንግስት ነው። ለዚህ አንድም ሰው ተጠያቂ አልሆነም። ወረድ ብሎ በምዕራብ ኢትዮጵያ በወለጋ በኩል 200ሺ ህዝብ ተፈናቅሏል።
እነሱ ግን “ጎላን በጎሳላይ ለማነሳሳት ይሞክራሉ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ንፁህ ህዝብ ነው፤ በምንም ሁኔታ አይነካካም። እያሉ የሚያሴሩትን ሴራ ሁልጊዜም እየተቃወምን ነው ያለነው። በቅማንትና በአማራ በወልቃይትና ጠገዴ መካከል ችግር የፈጠረው ማነው መንግስት ራሱ ነው። ለዚህ ሁሉ ጣጣ የዳረገን ኢህአዴግ ነው። ራሳቸው ኢህአዴጎቹ ዛሬ ለሁለት ተከፍለው እሳት እያነደዱብን ነው። ስለዚህ እከሌ አሸባሪ ነው። እከሌ ንፁህ ነው ማለት አንችልም። መፈራረጁን እናቁምና- እንነጋገር ነው የምንለው አለምም ተነጋገሩ እያለን ነው።
የውጪ አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት  ትደግፋላችሁ ማለት ነው?
አሜሪካም ሆነች ሌሎች የምዕራብ አገራት “በውስጥ ጉዳያችን ገቡ፣ ሉአላዊነታችንን ነኩ” እየተባለ ይነገረናል። “ችግራችሁን በንግግር ፍቱ፤ አትታኮሱ” ማለት እንዴት ነው ሉአላዊነትን መዳፈር የሚሆነው። እኛ ከመበታተን እንድንድን እንጂ እንድንበታተን የሚፈልጉ አይደሉም፤ አውሮፓ ህብረትም አሜሪካም።  ለራሳቸው ሲሉ ነው የሚወተውቱት።  አገር ሲፈርስና 110 ሚሊዮን ህዝብ ሲበታተን ችግሩ ወደ እነሱ መምጣቱ የማይቀር ስለሆነ ያቦካችሁትን እዛው ጋግሩ እንጂ ወደ እኛ  አታምጡት” እያሉን ነው። ይኼ ሊገባን ይገባል። እኛ ግን ለስልጣን ስንል እዚህ እየተባላን ነው።
ከቅድመ ሁኔታዎቻችሁ መካከል አንደኛው የታሰሩት አመራሮቻችንና አባሎቻችን እንዲሁም ሌሎች ፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚል ነው? በወንጀል ተግባር የተጠረጠረው በእስር ላይ የሚገኙ ሁሉ መፈታት አለባቸው እያላችሁ ነው?
ወንጀል የሰራ ሰው በስራው ወንጀል መጠየቁና መቀጣቱ ተገቢ ነው። ማንም ሰው ቢሆን ማለቴ ነው። ግን ስልጣን  ስለአለን የፈለግነውንና የጠላነውን ሰው ሁሉ እያሰርን ወንጀለኛ ነው ማለት አይቻልም።
ለምሳሌ የእኛ አባሎችና አመራሮች ከሃጫሉ ሞት በኋላ  በግፍ ታስረዋል። ከ206 ቢሮዎቻችን መካከል አሁን ክፍት የሆኑት 3 ብቻ ነው። ቢሮዎቹ በሙሉ ተዘግተዋል። ሰዎቹ ታስራዋል፣ ንብረቶቻችን ተዘርፈዋል። ቢሮዎቹን ይመሩ የነበሩ ሰዎች  በሙሉ እስር ቤት ነው ያሉት። ፍ/ቤት በነጻ የለቀቃቸውን ጭምር ፖሊስ አልቅም ብሏል። “የበላይ አካል አትፍታ ብሎኛል” ይላል። የእነ አቶ ጁዋር መሐመድና የእነ አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ ሰዎች ቀደም ብለው የተያዙት ከሃጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ ነው ተብለው ነበር። ያ ሳይሆንላቸው ሲቀር በሌላ አሳበው አስረዋቸው ነው ያሉት። እነሱም የሕግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ፍ/ቤት አንመላለስም ብለው ቀሩ። እስክንድር ነጋም ቢሆን እኛን የሚቃወም ሰው ነው ግን፤ የዚህንም ሰው ሰብአዊ መብቱ ይከበርለት፣ ቅሬታው በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰምቶ ይፈታ” ነው የምንለው። የመጨረሻ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ይህ ብቻ። ከአሁን በፊት ኤርትራን አስገንጥለናል፤ አሁን ደግሞ ወደ ትግራይ እየሄድን ው። ይሄ ነገር ስር ሳይሰድ ቁጭ ብለን በማንግባባቸው ጉዳች ላይ እንነጋገር ነው የምንለው።
በኦፌኮ አመራሮች መካከል መከፋፈል መፈጠሩንና አለመግባባቶች መኖራቸው ይነገራል። ይህ ምን ያህል እውነት  ነው?
ይህ  ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ጉዳይ ነው። እኛን ለመከፋፈል የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው እንዲህ የሚሉት። ከዚህ ቀደም በአንድ ሚዲያ ላይ “መረራ የፈለገውን ነው የሚያደርገው፤ ኦፌኮ ተከፋፍሏል” ብለው ጽፈው ሁሉ ነበር። ግን ሀሰት ነው። እኛ በጋራ ሆነን እየሰራን ነው። ይህ የብልጽግና ካድሬዎች ወሬ ነው፤ ምንም ልዩነት በመካከላችን የለም።
ከዚህ ቀደም ግን ፕሮፌሰር መረራ “የሽግግር መንግስት እናቋቁማለን ብለው በተናሩ ጊዜ፣ እናንተ ይህ የእኛ አቋም አይደለም፤ የመረራ የራሱ ነው” ብላችሁ ነበር…?
የዛን ጊዜ የሆኑ ቡድኖች በኦሮሚያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እናቋቁም የሚል ነገር አንስተው ነበር። ግን ያኔ እኛ “ከምርጫ በፊት ብሔራዊ ውይይ ይደረግ” ፤  “የአንድ ፓርቲ አባላት ህግ አውጪውንም ተርጓሚውንም አስፈጻሚውንም ይዘውታል። ይህ ሁኔታ አግባብ አይደለም የሚለው አቋም ይዞ ነበር። አገራችንን ከጥፋ ለማዳን ሁላችንም የየራሳችንን ሃሳብ ይዘን፣ በጋራ ለመስራት እንችላለን ነው- የእኛ አቋም ይሄ ዝም ብሎ መፈራረጁና መነካከስ አገራችንን ያጠፋታል እንጂ የትም አያደርሳትም። ከሁሉም በፊት ብሔራዊ ውይይት ሊቀድምና ሁሉም ወገን  መሳሪያውን አስቀምጦ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ሊወያይ ይገባል ነው የምንለው።

Read 8487 times