Sunday, 31 October 2021 19:32

በ”አንጎድልም” የመከላከያው የጥበብ ቀንዲል

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

ከመከላከያ ሰራዊት ልብ ሁልጊዜ የባሩድ ሽታ ግሳት፣… ሽለላና ቀረርቶ ብቻ ሳይሆን የተስፋ አበባዎች ሽታ ፣ የልማት መረዋ ደወል ይደመጣል። በጥበብ ሰማይ ላይ የነጻነት ቀለሞች ያዘሉ ቢራቢሮዎች ይበርራሉ።
ዓለም ላይ ብዙ ወታደሮች በእናት ሀገርና በአባት ሀገር ጥሪ ብቻ ሳይሆን በጥበብ ጥሪ ተጠምደው የውበት ሻማዎችን ለኩሰው የፍጥረትን አድማስ አስክረውታል። የትካዜ ጤዛዎችን አርግፈው በእንባ ነጠብጣቦች የሚያማምሩ ስዕሎችን በአዳም ልብ ህይወት አስቀምጠውታል።
ሔሜንግዌይ ወታደር ነበረ! ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ክፍሌ አቦቸር፣ አንዳርጌ መስፍንና ሌሎችም! በመንገዳቸው አፈሙዝ ጎን ብዕራቸውን ጠምደው በአራት ዓይኖች ልህቀት፣ ደመና ሰብስበው፣ ጥበብ አዝንበዋል!... የጦር ሜዳንና የብዕርን ውሎ ባንድ ጠምደው አርሰዋል!
ሰሞኑን የተመረቀው  “አንጎድልም” የሚለው የግጥም መድብል  አሥራ አንድ አባላትም ከዚሁ ጎራ የሚመደቡ ናቸው። መጽሐፉ በጥቅሉ 103 ገፆች ያሉት ሲሆን በ46 ገጾቹ ግጥሞችን ያካተተ የግጥም ስራዎች መድበል ነው።
አጠቃላይ ጭብጡ ሲታይ በወታደራዊ ተልዕኮዎች ላይ ቢያተኩርም፣ ሌሎችም ሁለንታዊ የሆኑ ሀሳቦችን ያንፃባርቃል። ለምሳሌ ልማታዊ ህልሞች፣ ባህልና ቅርስ የአባቶች አደራ፣ የትውልድ ፍቅር፣ የነጻነት ናፍቆቶች ይደመጡበታል።
ምናልባት የተለየ የሚያደርገው ኢሮስ የሚባለው የፍቅር ዝርያ አንድ ያለ መኖሩ ነው። ይህ ደግሞ የወቅቱን፣ ዐውድ አጢኖ፣ ስሜቱን መዝኖ ሀገር በምጥ ባለችበት አደባባይ “አይነኬ” መዝሙር ነው በሚል ተገድፎ ይሆናል። ግን ደግሞ “Storge” የሚባለው የፍቅር ዓይቶች ፊሊዮም በመጠኑ ይጤንበታል።
በቅርፃዊ ምደባው ባብዛኛው የትካዜ፣ የሐዘንና የምስጋና ግጥሞች በጥቅሉ “መዲና” በሚባለው ሰፈር የሚመደቡ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። እንደዚሁም የትዝታና የናፍቆት ግጥሞች አሉበት። የተወሰኑ ተራኪ ግጥሞችም!
ወታደር ሰው ነው። ሰው ሁሉ ግን ወታደር አይደለም። ከማህበረሰቡ የተመዘዙ ስለሆነ እኛን እኛን የሚል የሕይወት ጠረን አላቸው። ራሳቸው ብቻ ባሰመሩት መስመር ባገኙት ሥልጠና የቀረፁበት መልኩ አላቸው።
ሰው ስለሆኑ ማህበራዊነትን የሚማሩት እንደ ሁላችንም ከእናታቸው ቢሆንም፣ ስልጠናውና ትምህርቱ የሰጣቸው ሌላ አደራና አተያይ አላቸው። ታዲያ እነዚህ በጦር ሜዳ እሳት የተፈተኑ፣ በውጊያ ግንባር ሀገር በመጠበቅ የተካኑ ወታደሮች እንደ እኛ ስለ እናት የሚሉት ብዙ ስላላቸው በመጽሐፍ ውስጥ ሁለት ግጥሞች አውጥተዋል። ከነዚህ ውስጥ የመቶ አለቃ በላቸው ስመኝ አንዷ ናት።
“እምዬ” ይላል ርዕሱ።
አውቃለሁ፡-
የናት አንጀት ጨክኖ
ወጥቶ አደር … እንድሆን አምኖ
ስቆ እንዳልሸኘኝ ልብሽ
እንደተበተነ ሀሳብሽ፣
አይቻለሁ፡
“ደህና ሁን… ብለሽኝ ስትመለሽ
መኪናው ተንቀሳቅሶ … ገና ከፊትሽ ስሸሽ
አይኖችሽ እንባ አርግዘው
ጥርሶችሽ ፣ የጭንቅ ፈገግታ መልሰው፣
አውቃለሁ፡
ፊትሽ ዞር እንዳለ
እግርሽ መቆም እንዳልቻለ፣
ሃሳብሽ ሁሉ እንደዋለለ፣
አውቃለሁ፡
ሸኝተሸኝ ስትገቢ
አንድም ባገር ጠላት አረሽ…
አንድም ለኔ ለልጅሽ አዝነሽ ስታነቢ!!...
እንዲህ ይቀጥላል።
ይህ የእናት ፍቅር ጥልቅ ፣ የማህበራዊነት ፈትል ድር ሲመዘዝ፣ የተዳፈነው ከአንቀልባ የጀመረ ሕይወት መዝሙር የሰቀቀን ልቃቂት፣ የሁለት ወገን ፍልሚያ ነው። የህልውና መታደል፣ ለፍቅር ጆሮ መስጠት! እነዚህ የሕይወት ክንፎች ናቸው።
መከላከያ ሰራዊቱ በኢትዮጵያ አፈር የበቀለ፣ ባህሉና ወጉን ታጥኖ በልቡ ድሆ የኖረና ያደገ የትዝታው ቀለም በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ያሸበረቀ ነውና ሚዛኑ እዚሁ ውስጥ ይሰፈራል፣ የድንኳኑ ካስማም በዚሁ ይታጠራል!... ስልጠናው አንዳድ ሀገራዊ መልኮችና የወታደራዊ ተልዕኮ አሻራዎች በስተቀር ሁለመናው የኛ ነውና እንደኛው ልማታዊ ህልም አለው። ጦር ግንባር ሆኖ እየተፋለመ በልቡ የሚያረግዘው ጽንስ፣ በሰላም ዘንባባ የታጠረና ትውልድ ያማከለ ነው።
በ”አንጎድልም” የግጥም መድብል ውስጥ ያየሁት አንድ ሀመልማልም  ይኸው ነው። የተስፋ መዝሙር፣ የነገ ብሩህ ተስፋ!
ለዚህ ምሳሌ ከሚሆኑኝ ግጥሞች አንዱ የሻምበል ፍቃዱ እሸቱ “የጅብ ጩኸት” በሚል የተፃፈው ነው። (ገጽ 56)
ዘመን ካስቆጠረ ቁጭት - አርፎ ከተኛበት ነቅቶ፣
ከድህነት አረንቋ ስር- ከሞት አፋፍ ላይ ተነስቶ፣
ፈንቅሎ በወጣ ስሜት- ክንዱ በማይዝል ወገኔ፣
በክተት አዋጅ ተጠርቶ- ጉባ የከተመው ወገኔ፣
ሺህ ሆኖ እንዳንድ ሰው- ታሪክ ሲፅፍ ግድብ ሰርቶ፣
እዚያህ ማዶ ጅብ ይጮሃል- ለሚፈስሰው ውሃ ሞልቶ።
ይህ ግጥም የሰራዊታችንን ልብ ጽንስና የሩቅ ሕልም፣ የልቡን ትርታ የራእዩን ስዕል ማሳያ ነው። ገጣሚው የአባይን ግድብ መነሻ ቁጭት ከእንቅልፍ የመንቃት ወኔ ያሳያል። በስተመጨረሻም በተለመደው አሽሙራችን እዚያ ያሉት ላይ በምፀት ያላግጣል።
በመጽሐፉ ውስጥ እጅግ ገንኖ የሚሰማው ዐቢይ ርዕስ ጉዳይ ጎጠኝነትን ተቃውሞ ለአንድነት የሚጮህ ድምጽ ነው። መበታተን ጡንቻ አስልሎ፣ ለጥፋት መዳረጉን ወታደሩ ደግሞ ይህንን አንድነት ተጠምቶ ለአንድ ሀገር ያለ ልዩነት መሰለፉን፣ ነፍሱን መስጠቱን የሚያሳዩ ግጥሞች አሉ።
ይህ የግጥም መድበል የመከላከያ ሰራዊታችንን ህልም መመልከቻ ቪዲዮ፣ ሃሳቦቹን ማንበቢያ ድርሳን ነው እናም የሰራዊታችን መልክ እጅግ ያማሩ ጌጦች፣ የተስፋ አበባዎች ደረቱ ላይ የሰካብ ነው።
ለዚህ ምሳሌ ቢሆን ብዬ የሌተና ኮሎኔል ተስፋዬ ኤፍሬምን አንድ አጭር ግጥም እዋሳለሁ። (ገጽ 65)
“ከብረት ቆቡ ጋር”
የመሸገው አፅሙ- የበላው አፈሩ፣
ከየትኛው ወገን- ምን ይሆን ብሔሩ?
ይህ የተሰዋው- ስለ እናት ሀገሩ፣
መስጂድ ነው- በተስኪያን የት ነው መቃብሩ?
ብሔር ሃይማኖቱ- ከቶ ምንድን ይሆን?
ጀግናው ወታደሩ?... ይላል።
የህንን አንብቦ ትንሽ ማውጠንጠን፣ ለዘረኝነት በሽታ፣ ጠብታ መድሃኒት ይሆናል። ወታደሩ የሚሞተው ለሀገሩ እንጂ ለሰፈሩ አይደለም። የሰፈር መዝሙር ሀገር የመበተን ምኞት ቅዠት ነው። ለሀገር መሞት ግን የትውልድና የሀገርን ልዕልና የማስጠበቅ ሕልም ነው… እያልን ልንተነትንነው እንችላለን።
በአጠቃላይ መጽሐፉ ውስጥ የተካተቱትን ግጥሞች ስናያቸው፣ ሃሳባቸው የተውጠነጠነ በጥበብ ተፈትለው ወረቀት ላይ የሰፈሩበት መቸት ለአሁን የቀረበ እንደሆነ በጭብጣቸውና በያዟቸው ሁነቶች መነሻነት እናጤናለን።
ለምሳሌ ላነሳው የምፈልገው የሻምበል ገዛኸኝ ታደሰ-ግጥም በቅርቡ-ምዕራባወያንና-የነርሱ ጋሪዎች-ያሴሩብንን ሴራ የተመለከተ ሀሳብ-ነው፡፡ ርዕሱ “አዲዮስ ማስመሰል” ይላል፡፡
ከእውነት ፍርድ መንበር…ውሸት ቢንሰራፋ፤
ዓለም ቢደናገር-ሰማዩ ቢደፋ
አንዳንድ ሀቅማ አለ!
ከተማስሎ ልቆ-ሀገር የሚያነቃ
ድንበር የሚያሻግር….እብሪት የሚደቃ
አንዳንድ ሀቅማ አለ!
ካኮረፈ ዘመን-ሀሴት የሚጠራ
በቀናት መካከል ጥላቻ የሚፈራ
አንዳንድማ ሀቅ አለ!
ከመሸሸግ ዕጣ…መጋለጥ ባኖረ
ሰው ለምን ይጠፋል…ብሶት እያደራ!
ዓለም-የተደናገረበት፣ጥሬ ቅዠት፣በዓለም አደባባይ-ፍትህ አጥቶ ሲንከራተት፤…ይህን የሚያሸንፍ-ሀቅ፣በጨለማ ውስጥ ብርሃን አርግዞ፣ በሞት ጥሩንባ፣የህይወት ዜማ ያሰማል፤ አይሸነፍም የሚል-ሀሳብ ይዟል፡፡…. ብዙ ሲነበብ፣ብዙ ይወጣልለ፡፡…በሆታና ጊዜ ለፈቀደለት በብዙ ይመዝዘዋል!....እኔ ግን ብልጭ ለማድረግ ያህል እነሆ፡-
የሻለቃ ፈይሳ ግጥም ደግሞ ባልተለመደና ባለፉት ዓመታት በጥቂቶች ባልተወደደ
ስሜት ራሱን የሚጠራ-ገፀ-ሰብ-አስቀምጧል፡፡
“ትህምክተኛ በለኝ” ይላል ርዕሱ።
ጠላት ሳላጠፋ….አርፌ ሳልተኛ
እኔ ጠመንጃ ያዥ..አያቴ ነፍጠኛ
ሸልሎ ፎክሮ…አድዋ የዘመተ፤
አልደፈር ያለ…. “ሃያል ነን” ለሚሉት
“አይሆንም በሚለው…ኢትዮጵያዊ ትምህክት፤
ያርበኛው ወራሽ ነኝ….ለባንዳ ማልተኛ
ሀገር ሀገር የምል….. ወልዶኝ ትምህተኛ፤
ምግባሬ ሲያንስ እንጂ…ያነስኩ የሚመስለኝ
ስም ጎደለ ብዬ..ጥቂት ቅር አይለኝ፣
ነገም ሃሳብ ሲያጥርህ…. ፈርተህ ስትገኝ
ካሻህ ትምክህተኛ….ወይ ነፍጠኛ በለኝ፤
ያውም ከጃጋማ…ከአብዲሳ የምገኝ፤
የበላይ ቴዎድሮስ…ሀገር ወዳድነት ደምቆ ያደመቀኝ፡፡
በከፊል የወሰድኩት ግጥም፤ ጀግንነትን ጥላሸት ለመቀባት፣ አንድነትን በቡድን-ለመከፋፈል - የተነዙ፣ ስያሜዎችን - ይተቻል!... ”ጀግንነት” ያስከብራል እንጂ አንገት አያስደፋም እያለ ሀሳብን በዜማ ቃኝቶ ይፎክራል። “ሌሪክ” ዘውግ-ደግሞ ለዚህ ይመቻል፡፡ …..ስሜት ንክር ሙዚቃዊ ስልት ነው!
“አንጎድልም” የተሰኘው የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት-በደቦ-ያሳተሙት መፅሐፍ አጫጭርና ረዣዥም-ግጥሞችን አካትቷል።….ማጠርና መርዘም በራሱ፣የራሱ ውበት ስላለው እንደየቁመናውና መልኩ ይመዘናል እንጂ በአሠፉሩ ብቻ አይለካም፡፡
ገጣሚያኑ እንደ የትበሃላቸው የተለያዩ ቅርፆችን ተጠቅመው፣የዘይቤ ምርጫ አድርገው አሊያም ተላምደው ባብዛኛው የዝምድና ስልት ዘይቤን ይጠቅመዋል፡፡ በይበልጥ ደግሞ ንኩር ጠቃሽ ዘይቤ ጎልቶ ይታያል፡፡ ከምሳሌ ገጽ16፣66፣67፣69..እያለ ይቀጥላል፡፡
ከዚህ ዘይቤ ውስጥ በንስነት ታሪክ ጠቃሾቹ ይበረክታሉ። ይሁንና በአንድ መፅሐፍ ውስጥ የሚካተቱ ሁሉም ግጥሞች ሸጋ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ከፍና ዝቅ ይላሉ። …..ከሃገራችን-ገጣምያን ይህን ጽዋ የማይጨብጥ ማንም የለም፡፡
አንድ አሜሪካዊ-የስነ ፅሁፍ ፕሮፌሰርና ተንታኝ በመፅሐፍቸው እንደ እናንተ ወርድስ ዎርዝ…ቬላ… ዋትማንና ብራውንኒንግም አንዳንዴ ቀን ይጎድልባቸዋል፡፡ …. የአንድ እናት ልጆች ሁሉም አይመሳሰሉም፡፡…. የቦታ ውስንነት ስላለብኝ እንጂ ልጠቅሳቸው የሚገባ ከልባችን ምት፣ ከነፍሳችን ድምፅ፤ ከሳቅና ለቅሷችን ጋር ዝምድና ያላቸው፤ የራሳችን የገደል ማሚቱዎች ነበሩ፡፡ ግን…ቦታ!... እናንተ መፅሐፉን አንብቡት።

Read 3753 times Last modified on Monday, 01 November 2021 07:31