Saturday, 15 September 2012 11:50

ዕንቁጣጣሽ - ርዕሰ አውደ አመት

Written by  ታደሰ አ.
Rate this item
(26 votes)

በግዕዝ አውደ ዓመት ይባላል - ርዕሰ አውደ ዓመት - የበዓላት ሁሉ የበላይ፣ ራስ ማለት ነው፡፡ በአማርኛ ደግሞ እንቁጣጣሽ፣ የዘመን መለወጫ ወይም ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል፡፡ የዘመን መለወጫ የሚለው ግልፅ ስለሆነ ሁለቱን ስያሜዎች ለየብቻ እንመልከታቸው፡፡ በመጀመሪያ ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ የተሰየመው በነቢዩ ዘካሪያስ ልጅ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እንጂ በሐዋርያው/ ወንጌላዊው ዮሐንስ አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ በብሉይና ሃዲስ መካከል የተፈጠረ እና «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ የኖረ፣ በመጨረሻም በሄሮድስ ትዕዛዝ ጭንቅላቱን የተቆረጠ ትልቅ ሰማዕት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የቤተክርስቲያን አባቶች የበዓላትን ስርአት ሲሰሩ፣ ይህ በዓል ለመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ መታሰቢያ እንዲሆንና በእሱ ስምም እንዲጠራ በመወሰናቸው ነው፡፡

ሁለተኛው ዕንቁጣጣሽ ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉና ተራ በተራ እንያቸው፡፡ አንደኛው በኖህ እና በልጆቹ ዙሪያ የሚያጠነጥን፡፡ ሴም፣ ካምና ያፌት ሶስቱ የኖህ ልጆች ናቸው፡፡ ኖህ አህጉራትን ለሶስቱ ልጆች አከፋፍሎ ሲሰጥ ለካም አፍሪካ ደረሰው፡፡ ካም ወደ አፍሪካ የገባው እና መጀመሪያ የረገጠው ኢትዮጵያን ሲሆን ወሩም ምድሪቱ በአደይ አበባ ያሸበረቀችበት የመስከረም ወር ነበር፡፡ በምድሪቱ ውበት በመደመሙና ይህ ዕጣም ለእሱ ስለደረሰው ተደስቶ “ዕንቁ ዕጣ ወጣልኝ” አለ፡፡ እንግዲህ እንቁጣጣሽ ለሚለው ቃል አንዱ የየት መጣ ሀሳብ /Etymology/ እንዲህ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ምድሪቱ በአደይ ፈክታ ሲመለከት “ዕንቁ ዕፅ አወጣሽ” ከሚል ነው እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜ የመጣ የሚል ነው፡፡

በዚህኛው አካሄድ “ዕንቁ” ከኦይስተር ቅርፊት /pearl/ ውስጥ የሚገኝ ትንሽ ድቡልቡል፤ ጠንካራ አንጸባራቂ፤ ነጭ ውድ ጌጥ/ ለጌጥነት የሚያገለግል ነገር/ ሲሆን “ዕፅ” ደግሞ በግዕዝ የአማርኛው “ተክል” አቻ ነው፡፡ ስለዚህ የተክሉን መልክ ከዕንቁ ጋር በማነጻጸር የምድሪቱን ውበት ለመግለጽ የተጠቀሙበት ነው፡፡

ሶስተኛው ደግሞ የቀዳማዊ ምኒሊክ እናት ንግስት ሳባ ሰለሞንን ለመጎብኘት በሄደችበት ጊዜ ንጉሱ “ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ” ብሎ መስጠቱን መሰረት አድርጎ የሚነሳ ሃሳብ ሲሆን ወሩም ወርሃ መስከረም ነበር፡፡

አዲስ ዘመን ከወቅትና ከመልክአምድራዊ፣ ከባህልና  ከኃይማኖት አንጻር

አዲስ ዘመን የሚከበርበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛ ወንዞች የሚጎሉበት፣ ገበሬው የክረምቱን ወራት አርሶ ዘርቶ አርሞ ወዘተ… የአዝመራውን አላባ የሚጠብቅበት፣ የጥጋቡ ዘመን የሚመጣበት፣ ብርሃናት ዑደታቸውን ጨርሰው አዲስ የሚጀምሩበት  ወዘተ. ሲሆን ሁኔታውን ከወቅቶችና ከመልከአምድራዊ ሁኔታ ጋር አሰናስሎ መመልከት ይቻላል፡፡

መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣

እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ፡፡ የሚለው ግጥም ወቅትና መልከአምድርን የሚመለከት ነው፡፡ በክረምት ወንዝ እስከሚጎድል /ድልድይ እንኳን ያኔ አሁንም በየጎጡ አይታሰብም/ ዘመድና ዘመድ የማይገናኝበት መሆኑን ያመላክታል፡፡

ሁለተኛው በኖኅ ዘመን ምድርን ያጥለቀለቃት የጥፋት ውሃ የደረቀበት በመሆኑ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሃፍ ውስጥ መጽሃፈ ኩፋሌ ላይ በአስረኛው ወር፣ የተራሮች ራስ ታየ ይልና፤ ምድር በመጀመሪያው ወር መባቻ መታየቷን ይመሰክራል፡፡ /ኩፋሌ ምዕ 7፤1/ ከዚህ በተጨማሪ ሄሮድስ የቅዱስ ዮሐንስን ጭንቅላት ያስቆረጠበትን፤ በዚህም የቅዱሱን ሰማዕትነት ለመዘከር ነው የሚሉ ሀሳቦች ናቸው፡

ይህን ሁኔታ ከኃይማኖት አኳያ የተሰነዘረ ሃሳብ ብሎ መመደብ ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል ከባህላዊ ዳራ አንጻር የምንመለከታቸው ሲሆኑ ጭፈራው፣ ምርቃቱ፣ ችቦ ማብራቱ፣ ድግሱ ወዘተ. ናቸው፡፡ ዝናቡ የምህረት፣ እህሉ የበረከት እንዲሆን፣ ሰላም እንዲወርድ ይጸለያል፡፡ “እህል ይታፈስ ገበሬ ይረስ፤ አራሽ ገበሬውን ሳቢ በሬውን ይባርክ...” እየተባለ በሽማግሌዎች ይመረቃል፡፡ ጭፈራዎቹም የባህሉ አንድ አካል ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል የተወሰኑ ስንኞች ወስደን እንመልከት፡፡

የጎመን ምንቸት ውጣ፣

የገንፎ ምንቸት ግባ፡፡

አይዞሽ ነፍሴ ፣

ደረሰልሽ ገብሴ፡፡

አትኩራ ገብስ፣

ጎመን ባወጣው ነብስ፡፡

ገበሬው የአመት ቀለቡ የሚሟጠጥበት፣ ለዘር ያስቀመጣትን እህሉን ለመሬት አደራ ሰጥቶ /የዘር እህል አይበላም/ ቶሎ የሚደርሱትን እነጎመንን እየተመገበ ይከርማል፡፡ መስከረም ጥቅምት ላይ በተለይ የገብስ ዘሮች ይደርሱና ገንፎም በሶም ይበላል፡፡ ስለዚህ በዘመን መለወጫ ጊዜ ጎመን ሲቀቅልበት የከረመውን ምንቸት ውጣ እያለ በአዲስ ተስፋ የገንፎ ምንቸቱን ግባ ሲልና፤ ወደዚህኛው ምግብ የሚዞርበትን ሁኔታ ሲገልጽ እንሰማለን፡፡ በሽታውን፣ ችግሩን፣ ተንከሊሱን ሁሉ በችቦ የተስፋ ብርሃን እንጎሮጎባሽ እያለ በመተርኮስ ያባርራል፡፡

እዚህ ላይ ለነፍሱ ገብስ እንደደረሰለት ያስገነዝብና ተመልሶ ገብስ በዚህ እንዳይኮራ፣ የጎመንም ውለታ እንዳይረሳ “ገብስ፤ ነፍሴን አትርፎ ለአዲስ ዘመን ያደረሰኝ ጎመን ነውና አትንቀባረር” ለማለት “አትኩራ ገብስ፣ ጎመን ባወጣው ነፍስ” ብሎ ሸንቆጥ ያደርገዋል፡፡

ችቦም ድቅድቁን ጨለማ የሚሰነጥቅ ብርሃን ስላለው፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሄዳችን ትዕምርት ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ለመስቀል ያገናኘን!

 

 

Read 53117 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 15:34