Sunday, 31 October 2021 16:15

አንድ ዓመት ያስቆጠረው የመንግስትና የህውሐት ታጣቂዎች ጦርነት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

በስምንት ወሩ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል
ጦርነቱን ለማስቀረት የሚያስችሉ ዕድሎች የመከኑት በህውሐት ሃይሎች ነው

  የፊታችን ረቡዕ አንደኛ አመቱን በሚደፍነው በኢትዮጵያ መንግስትና በህውሐት ታጣቂ ሃይሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት አሁንም የቀጠለ ሲሆን በእርግጠኝነት መቼ እንደሚቋጭ አይታወቅም።
ሰሞኑን መንግስት በመቀሌ ከተማ ውስጥ የሚገኙና ታጣቂ ቡድኑ ለስልጠናና ለሎጂስቲክ የሚጠቀምባቸውን ማእከላትና ተቋማት በአየር እየደበደበ እንደሚገኝ የመከላከያ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከትናንት በስቲያ ለሰባተኛ ጊዜ ባደረገው ድብደባ ታጣቂ ሃይሉ ለወታደሮች ማሰልጠኛና ለትጥቅና አልባሳት ማደራጃነት ሲጠቀመባቸው የነበሩ ቦታዎችን አውድሟል።
በዚህ አንድ ዓመቱን ባስቆጠረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን በግፍ ተገድለዋል፣ በዘር ማንነታቸው ብቻ ተለይተው የተጨፈጨፉ ሺዎች በጅምላ ተቀብረዋል። ሚሊዮኖች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል፣ በርካታ የቁም እንስሳት በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ንብረትም ወድሟል።
ጦርነቱ በዚሁ ከቀጠለ የሚሞተውን የሚፈናቀለው ህዝብና የሚወድመው ንብረት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሄዱ አይቀሬ ነው። ይህ ሁኔታ ታዲያ አገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍላት እንደሆነና በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ። ይህ ዘገባ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ የተጀመረውና እስከአሁን የቀጠለው ጦርነት አጀማመርና ሂደት ምን እንደሚመስል ለማስታወስ ይሞከራል።
ከጦርነቱ ጅማሬ በፊት
የፌደራል መንግስቱና የትግራይ  ክልል አስተዳደር ቁርሾ መገለጥ የጀመረው ሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ.ም ህውሃት የፌደራል መንግስቱ ከኤርትራ መንግስት ጋር ሰላም ለመፍጠር ማቀዱን የሚተች መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ነው። ህውሐት በዚህ መግለጫው ከኤርትራ መንግስት ጋር የሚደረገውን ሰላማዊ ግንኙነት የማይቀበል መሆኑንም አሳውቆ ነበር።
ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ህውሐት የኢህአዴግን መክሰምና የአዲሱን ፓርቲ ብልፅግና መዋቀር አስመልክቶ ተቃውሞውን በማሰማት፣ የአዲሱ ፓርቲ  አባል እንደማይሆንም አሳወቀ። ከወር በኋላ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ህውሐት በማግስቱ  በሚካሄደውና የብልፅግና ፓርቲን መዋቅር እውን በሚያደርገው ጉባኤ ላይ እንደሚያገኝ አሳወቀ። ሁኔታዎች እየተካረሩ መሄዳቸውን ቀጠሉ። የጥምቀት በአል በድምቀት በሚከበርበት በጎንደር ከተማ ውስጥ  በተፈጸመው የሽበብር ተግባር ላይ የትግራይ ክልል  ገዥ ፓርቲ እጅ እንዳለበት በመጥቀስ የአማራ ክልል መግለጫ አወጣ። ህወሐት ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ በመጻፍ ብልጽግና ተብሎ ከተዋቀረው አዲስ ፓርቲ ጋር የንብረት መካፈል እንዲደረግ ጠየቀ። በዚህ መሰረትም ጥር 26 ቀን 2013 ምርጫ ቦርድ ለህውሐትና ለብልፅግና ንብረት አከፋፈለ።
በፌደራል መንግስቱና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው ልዩነት እየሰፋ ሄዶ ህውሃት በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አሳወቀ። የፌደራል መንግስቱ ምርጫው ህጋዊነት የሌለው ነው ሲል ገለጸ። ህውሐት ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ምርጫ አካሄደ። መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም የህውሐት አባል የሆኑ የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ወደ ትግራይ ክልል እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ። ከቀናት በኋላ የፌደራሉ መንግስት ወታደራዊ የስልጣን ሹምሽር ሊደረግ ነው መባሉን ተከትሎ፣ የትግራይ ክልል መንግስት ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም “ማዕከላዊው መንግስት ይህንን ማድረግ አይችልም” ሲል መግለጫ አወጣ። ከዚህም አልፎ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝን እንዲመሩ የተሾሙት ሜጀር ጀነራል በላይ ስዩም ወደ ክልሉ መግባት እንደማይችሉ አስታወቀ። ይህንን ተደጋጋሚ የህውሃት ጥፋትና እርምጃ የማዕከላዊ መንግስት እንደማይታገስ አስጠነቀቀ። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የህውሐት ታጣቂ ቡድን በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሃይል ላይ ድንገተኛ የጥቃት እርምጃ ወሰደ። በማግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የመከላከያ ሰራዊት በህውሃት ላይ የሃይል እርምጃ እንዲወሰድ  ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ከአገር መከላከያ ሰራዊት ተቀንሰው የነበሩ 3 መኮንኖች ወደ ሰራዊቱ እንዲመለሱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጠ።
የመከላከያ ሰራዊት በህውሃት ታጣቂ ሃይሎች ላይ በወሰደው እርምጃም በጥቂት ቀናት ውስጥ መቀሌ ከተማ በመግባት፣ ቡድኑ ለተለያዩ የወታደራዊ አገልግሎቶች የሚጠቀምባቸውን ቦታዎች ተቆጣጠረ። በርካታ ቁጥር ያለው የነፍስ ወከፍና ከባድ መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ።
በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶች
በህውሃት ቡድን ጠብ አጫሪነት የተቀሰቀሰው ጦርነት፤ ሺዎችን ለሞት ሚሊዮኖችን ለመፈናቀል በመዳረግ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ህውሃት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በማይካድራ ንፁሃን ላይ በፈፀመው ጥቃቱ ከ600 በላይ ሰዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በወቅቱ ያወጣው መረጃ አመላክቷል።
በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ውስጥ በምትገኘው የማይካድራ ከተማ አሰቃቂው ጥቃት የተፈጸመው ጥቅምት 30 ቀን 2013 ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ነበር። ጥቃቱ እስከሚቀጥለው ቀን ጠዋት ድረስ የቀጠለ ሲሆን በጥቃቱ የሞቱት 600 ሰዎች ለአፈር የበቁት ከ3 ቀናት በኋላ ህዳር 2 ቀን 2013 ዓ.ም መከላከያ አካባቢውን ከተቆጣጠረ በኋላ ነበር። በዚህ ግድያ በየሜዳው ወድቀው ከተገኙት ንጹሃን በተጨማሪ በርካታ የጅምላ መቃብሮችም ተገኝተዋል።
ይህንን ጭፍጨፋ አስመልክቶ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፤ በጥቃቱ ከ600 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና በድርጊቱ ውስጥም ሳምሪ የተባለው መደበኛ ያልሆነ የወጣቶች ቡድንና የአካባቢው ፖሊስና ሚሊሻ እጃቸው እንዳለበት ይፋ አድርጓል።
ታጣቂ ቡድኑ በአማራ ክልል  በደብረ ታቦርና በውጫሌ በአፋር ክልል እንዲሁም በሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረሰው ጥቃት ከ490 በላይ ንፁሃን ሰዎች መገደላቸውና  ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደግሞ መፈናቀላቸውን ሪፖርቶች አመልክተዋል።
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከክልሉ  ከወጣበት ሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ ታጣቂ ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጽመውን ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው። ቡድኑ በሰዎች ላይ ከሚፈጽመው የግድያ ጥቃት በተጨማሪ የአገርና ህዝብ ንብረትን ማውደም እንዲሁም የቁም እንስሳትን ተኩሶ መግደል፣ የደረሱ ሰብሎችን ማቃጠል ይገኙበታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ እንደገለጸው የሕውሃት ቡድን በትግራይ ክልል አራቱም አቅጣጫዎች ወደ መቀሌ የሚያስገቡትን አራት ድልድዮች አፍርሷል። በሽሬና አክሱም መካከል የሚገኘውን አስፓልት መንገድ በግሬደር አፍርሶታል። የአክሱም አየር ማረፊያ፣ በርካታ የሃይማኖት ቦታዎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ት/ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ባንኮችና የመንግስት መ/ቤቶችን ዘርፏል፤ አውድሟል። መንግስት በተለያዩ አውደ ግንባሮች ከታጣቂ ሃይሉ ውጊያ እያካሄደ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም በጀመረው የአየር ጥቃትም እስከ አሁን ለሰባት ጊዜያት ያህል ድብደባ ማካሄዱንና በድብደባውም የህውሐት ታጣቂ ሃይሎች ለወታደራዊ ማሰልጠኛ የሰው ሃይል ማደራጃ እንዲሁም የአልባሳትና ትጥቅ ማምረቻ ቦታዎችን አውድሟል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቅቃል ተብሎ የታሰበውና ለአንድ አመት የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት በአፋጣኝ የሚቋጭበት መንገድ ካልተገኘ አገሪቱን ለከፋ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ቀውሶች እንደሚዳርጋት ምሁራን ይገልጻሉ። በወልዲያ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ መምህሩ ዶ/ር ይበልጣል አድማሴ እንደተናገሩት፤ በጦርነቱ እየጠፋ ያለው የሰው ህይወትና እየወደመ ያለው ንብረት፣ አገሪቱን ከፍ ያለ ዋጋ የሚስከፍላት ነው ብለዋል። ጦርነቱን በአፋጣኝ ለማስቆም የሚቻልባቸውን መንገዶች ሁሉ መፈለግና የወደሙ የአገር ሀብትና ንብረቶችን ለማቋቋም በተጠናከረ መልኩ ሊሰራ እንደሚገባም ተነጋግረዋል።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ጦርነት አገሪቱ በ8 ወራት ብቻ ከ100 ቢሊዮን በላይ ወጪ ለማድረግ መገደዷን መግለጻቸው ይታወሳል።

Read 11714 times