Sunday, 31 October 2021 15:22

ለሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋ ተጎጂዎች ትኩረት እንዲሰጥ ኢዜማ ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል  ጦርነት ከተሰጠው ትኩረት ባሻገር በሰው ሠራሽና ተፈጥራዊ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችም ትኩረት እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጥሪ አቀረበ፡፡
በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት ሲል በመግለጫው ያመለክተው ኢዜማ፤ ወቅቱ ሃገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ተከብባ ያለችበት ከመሆኑም በላይ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል እየተደረገ ያለው ጦርነት ብዙ ስጋትን የደቀነና የሁላችንም ልዩ ትኩረት የሚሻና ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም፣ ሌሎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ትኩረት ሊሰጣው ይገባል ብሏል፡፡
በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያት እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎች የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ ዜጎቹን ከመኖሪያ እያፈናቀለና እንስሳትን፣ሰብልን እንዲሁም ንብረትን እያጠፋ መሆኑን ከሰበሰባቸው  መረጃዎች መገንዘቡን ኢዜማ አትቷል፡፡
ኢዜማ ባወጣው መግለጫ መሰረት፤ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ክፉኛ ከተጎዱት መካከል በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን፣በደቡብ ክልል ኦሞ ዳሰነች ወረዳ፣ በደቡብ ክልል በአማሮ  ወረዳ እንዲሁም በደራሼ ልዩ ወረዳ ኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳና ባስኬቶ ልዩ ወረዳ ተጠቃሽ ሆነዋል።
በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ከሚገኙ 13 ወረዳዎች መካከል በአስሩ ከፍተኛ ድርቅና የምግብ እጥረት አደጋ መከሰቱን፤ በዚህም ድርቅ ከ166 ሺህ 136 በላይ ዜጎች በምግብ እጥረት መጋለጣቸውን እስካሁንም 12 ሺህ ያህል መሞታቸውን አመልክቷል - የኢዜማ መግለጫ፡፡
በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የጊቤ ቁጥር 3 ሃይል ማመንጫ ግድብ ከመስከረም 9 ቀን 2014 ጀምሮ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት 39 ሺህ 92 አባራዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን፤ ጎርፉ ከአራት ወረዳዎች የሚገኙ 59 ቀበሌያትን በተለያየ መጠን መጉዳቱ በመረጃው ተጠቁሟል፡፡
በአካባቢው አሁንም በዳሰነች ወረዳ አሞራቴ ከተማ 5 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ከግድቡ በተለቀቀ ውሃ ምክንያት የኦሞ ወንዝ በመሙላቱ፤ መስመሩን ጥሶ በመፍሰሱ፣ በዜጎች ላይ ስጋት መደቀኑን የተለያዩ ለም የግጦሽ መሬቶችም በጎርፍ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቻው የኢዜማ ሪፖርት ያስረዳል።
በአማሮ ልዩ ወረዳ ደግሞ ራሱን ኦነግ ሸኔ በማለት የሚጠራው ቡድን፣ በአካባቢው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ጨምሮ የዜጎች ሰላምና ደህንነት እያወከ መሆኑን ጠቁሞ፤ በዚህ ችግር የተነሳም በአማሮ ወረዳ በሚገኙ 20 ቀበሌያት ነዋሪ የሆኑ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ከቤታቸው መፈናቀላቸውን አመልክቷል፡፡ በአካባቢው የሚገኘው የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክም በአነግ ሸኔ መወረሩን ኢዜማ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በአካባቢው ባሉ አጎራባች አካባቢዎች  በሲዳማ፣ አማሮ ብሬ፣ በቡርጂ፣ በጋሞና በጉጂ ያሉ ዜጎች አሁንም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ ያለው መግለጫ፤ በአካባቢው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የ3 መቶ ሰዎች ህይወት በግጭት ማለፉን ጠቁሟል፡፡ በአካባቢው ባለው ግጭት ምክንያት በአማሮ ቦሬ ሃዋሳ የሚወስደው የ213 ኪ.ሜ መንገድ በመቋረጡ ነዋሪዎቹ ከ2009 ጀምሮ በሌላ አቅጣጫ 530 ኪ.ሜትር ለመጓዝ መገደዳቸውንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች አሁንም ችግራቸው አለመቀረፉንና ለአደጋ ተጋልጠው እንደሚገኙ ያመለከተው የኢዜማ መግለጫ፤ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል የሚካሄደው ጦርነት ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ቢሆንም ለእነዚህ ዜጎችም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

Read 919 times