Saturday, 23 October 2021 14:42

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እውነታ?
                                      ጌታሁን ሔራሞ

            አንዳንዶቻችን... የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እውነታን (Realism) መከተል ነው... የሚለውን ማጠቃለያ በተሳሳተ መልኩ የተረዳን ይመስለኛል፤ ማለትም እውነታውን በቀጥታ ከኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ሁኔታ ጋር እናቆራኘዋለን። የአሜሪካ እውነታ ግን እሱ አይደለም። ለምሣሌ ለአሜሪካ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዶ/ር ዐቢይ መንግስት ጎን መሰለፉ ወይም አለመሰለፉ ለብቻው የሚፈይደው ነገር የለም። የአሜሪካ ዋና ጥያቄ የሚያጠነጥነው በውስጥ የፖለቲካችን ሁኔታ ላይ ሳይሆን በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ላይ ነው። ከዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ጎን በሀገር ውስጥ ማን ተሰለፈ? የሚለው ሳይሆን በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ከማን ጋር ተወዳጅቷል? የሚለው ነው።
“The Tragedy of Great Power Politics” ደራሲ የሆነው John J. Mearsheimer አሜሪካ በውጭ ጉዳ ይ ፖሊሲዋ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ፣ የእሷን አቅም የሚፈታተን ተቀናቃኝ በየትኛውም ቀጠና እንዳይኖር የሚያግዛትን “Offensive Realism”ን እንደምትከተል (በዋናነት) በመፅሐፉ አስምሯል። በዚህ ፖሊሲ ረገድ አሜሪካ በቀዳሚነት በዓይነ ቁራኛ  የምትከታተለው ቻይናን ነው። ስለዚህም አሜሪካ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ሌላ ሀገር በሉዓላዊ ድንበሩ ውስጥ ዲሞክራሲን ያስፍን አያስፍን ብዙም አያሳስባትም (የሊብራል የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ከዚህ መርህ በተቃረነ መልኩ የተመሠረተበት ወቅት እንደተጠበቀ ሆኖ)። የተመረጠው መሪ የሕዝብ ድጋፍ ይኑረው አይኑረውም ቀዳሚ ትኩረቷ አይደለም። “Offensive Realism” ትኩረት የሚሰጠው ለቀጠናዊ የኃይል አሰላለፍ (Regional Power Hegemony) ነው።
አሜሪካ ከቻይናና ራሺያ ጋር በመወገናቸው ብቻ ጣልቃ እየገባች በሕዝብ የተመረጡ መሪዎችን ከሥልጣን እስከ ማስወገድ ስለመድረሷ የሚያስረዱን የአያሌ ሀገራት ተሞክሮዎችን ማንሳት ይቻላል። ደርዘን ከሚያህሉ ሀገራት መካከልም ለዛሬ ኒካራጓን ብቻ ላንሳ፤ እ.ኤ.አ. በ1978 ዓ. ም ኒካራጓ ውስጥ በሕዝብ ድጋፍ የተመረጡ የሳንድንስታን አብዮተኞች የአምባገነኑን የሳሞዛ ሥርዓት ከገረሰሱ በኋላ በሀገሪቱ በርካታ ለውጦችን አምጥተው ነበር፤ ለምሣሌ፦
የተረጋጋና ብዝሃነትን ያማከለ መንግስት መመስረት ጀምረው ነበር።
የሞት ፍርድን በተመለከተ ከፍተኛ ማሻሻያ አድርገው ነበር።
ከ100,000 በላይ ለሆኑ ገበሬዎች የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎቻቸው ተመልሰውላቸው ነበር።
2000 ያህል ትምህርት ቤቶችን ገንብተው ነበር።
የመሠረተ ትምህርት ፕሮግራሞችን በማስፋፋት መሃይምነትን ለመገርሰስ ዘመቻ ጀምረው ነበር። በዚህም ዘመቻ ያልተማረው የሀገሪቱ ዜጋ ወደ 1/7 ኛ ወርዶ ነበር።
ነፃ የትምህርትና የሕክምና አገልግሎት ዘርግተው ተግባራዊ አድርገው ነበር።
በወሊድ ወቅት የሚሞቱትን ሕፃናትን ቁጥር በ1/3ኛ እንዲቀንስ አድርገው ነበር።
ፖሊዮን ከመላ ሀገሪቱ አጥፍተው ነበር።
እናም ምንም እንኳን ሳንዲንስታንስ በሕዝባቸው እየተደገፉ ለሀገራቸው ይህን ያህል የሚጨበጥ ለውጥ ቢያመጡም በአሜሪካኖቹ አልተወደዱም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የሳንዲንስታንስ ፖለቲካዊ ርዕዮት ወደ ሶቪየት ማዘንበሉ ነበር። የ”offensive Realism” የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ደግሞ በቀጠናው ከአሜሪካ ውጭ ሌላ ልዕለ ኃያል እግሩን እንዲያስገባ አይፈቅድም። የሳሞዛ ዳይናሲቲ ለ40 ዓመታት ያህል ኒካራጓን መቀመቅ መክተቱ እውን ቢሆንም፣ ዳይናሲቲው ለአሜሪካ ቤተኛ ነበር። ስለዚህም የወቅቱ የአሜሪካ መሪ የነበረው ትልቁ ቡሽና ሲ. አይ. ኤ. ሳንዲንስታንስን የሚቃወም ኮንትራስ የተሰኘውን ተዋጊ ቡድን በአዲስ መልክ አዋቅረው ኒካራጓ ውስጥ ጦርነት ቀሰቀሱ። የሚገርመው አሜሪካኖቹ ይህን ሁሉ ሁከት ይቀሰቅሱ የነበሩት በስመ ሰብዓዊ ጣልቃ ገብነትና ሳንዲንስታንስን ማርክሳዊ አምባገነን ናቸው በሚል አጉል ክስ ነበር። ለእነርሱ ሳሞዛ አምባገነን አይደለም። እ.ኤ.አ. በ1939 ዓ.ም. የወቅቱ የአሜሪካ መሪ የነበረው ፍራንክሊን ሩዝቬልት፣ አምባገነኑን ሳሞዛን ስለመደገፉ የተናገረው ይህን ይመስላል፦ “Somoza may be a son of a bitch, but he’s our son of a bitch.”
እናም በቡሽ ዘመንም በአሜሪካ የሚደገፉ የኮንትራስ አማፂያን ዋና ተልዕኮ መሠረተ ልማቶችን በማውደም፣ ሲቪሎችን በማሰቃየትና በመግደል የሳንዲንስታንስን ሕዝባዊ ድጋፍን ማመንመን ነበር።
ሕዝቡም ከአማፂያኑ የሚደርስበት በደል እየበዛበት ሲመጣ ተገድዶ ኮንትራስን ለመደገፍ ወሰነ። በመጨረሻም ሳንዲንስታንስ በቡሽና በሲ. አይ. ኤ. ሴራ ከሥልጣን ተወገዱ። (ምንጭ፦ Humanitarian Imperialism, By Jean Bricmont, 2006)
ከአሜሪካ “Offensive Realism” እና ከኒካራጓ ተሞክሮ የኢትዮጵያ መንግስት ብዙ ትምህርት መቅሰም አለበት ባይ ነኝ። የአሜሪካኖቹን በስመየኛ እውነታ የአሜሪካኖቹ እውነታ አይደለም። የነርሱ እውነታ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ከእነርሱ ጋር የሚገዳደሩ ሀገራት (ቻይናና ራሺያ) ልዕለ ኃያል መሆን የለባቸውም የሚል ነው። የኢትዮጵያን መንግስት ሲደግፉም ሆነ ሲቃወሙ መንደርደሪያቸው ይኸው ነው። ይህ ተፈፃሚ ካልሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ የተመረጠ መንግስት ይኑር አይኑር፤ ዲሞክራሲ ይስፈን አይስፈን ጣጣቸው አይደለም። ሌላው ይቅርና ከእነርሱ ጎን ያልተሰለፈ መንግስት የሕዝብ ድጋፍ ቢኖረው እንኳን ሕዝቡን በውክልና በሚከፍተቱት ጦርነት በማስመረር ተስፋ እስከ ማስቆረጥ ይደርሳሉ፤ ይኸው ነው!

_____________________________________________________

                            መጠያየቅ
                                 በእውቀቱ ስዩም

            በቀደም ዩቲዩብ ላይ ስርመሰመስ አንድ ለየት ያለ ፕሮግራም አየሁ፤ ሁለት አርቲስቶች መድረክ ላይ ይቀርቡና እርስበርስ ቃለ መጠይቅ ይደራረጋሉ፤ ይካካባሉ፤ ይሸነጋገላሉ ማለት ይሻላል፡፡ ቃለ መጠይቁ በገሀዱ አለም ያለውን እውነታ አያንጸባርቅም! በገሀዱ አለም፤ አርቲስት አርቲስትን ይቦጭቃል፤ አርቲስት በአርቲስት ላይ ይሸምቃል፤ አርቲስትና አርቲስት እሳትና ጭድ፥ አቤልና ቃየል፤ ኦባማና ቢንላደን ናቸው፡፡ በጠቅላላውም ባይሆን ባመዛኙ፤ እንዲል መንጌ፡፡
ባነሳሁት ፕሮግራም ላይ ወንድና ሴት አርቲስቶች ቀርበዋል፤ እና ወጋቸው እንደሚከተለው አካባቢ ነው፥
እሱ - ጎበዝ ተዋናይት መሆንሽ መላው አለም የመሰከረው ሀቅ ነው! በበጎ አድራጎት ስራሽ ትንሿ አበበች ጎበና የሚል ስያሜ አግኝተሻል፤ ቁንጅናሽም በጣም አደገኛ ነው! ትዝ እሚለኝ የመጀመርያ ፊልማችንን ስንሰራ፤ አንድ ካሜራማን ከጣራ ላይ ሆኖ ሲቀርጽ ውበትሽ ስቦት ተከሰከሰ! በአደጋው ካሜራማኑ ግራ እግሩን፤ ፕሮዱዩሰሩ ካሜራውን ሊያጣ ችሏል! ይሄ ከምን የመነጨ ነው ትያለሽ?
እሷ - ያው የፈጣሪ ጸጋ ነው! አንተም ከትወናህ ውጭ ህብረተሰቡ እማያውቀው ብዙ ተሰጥኦ አለህ፤ ስትሰብክ እንደ መጋቢ ሀዲስ፤ ስትጽፍ እንደ አቶ ሀዲስ ነህ! ሙያህ አክተር! ማእረግህ ተጠባባቂ ክቡር ዶክተር! ግርማ ሞገስህ እንደ ሃይለስላሴ፥ ደምጽህ እንደ አለምነህ ዋሴ! በዚህ ድምጽህ ህገመንግስቱን ብትተርክልኝ ራሱ አይሰለቸኝም! ይህንን ሌላም ሰው ብሎህ ያውቃል?
እሱ - መስማት የተሳናቸው ሰዎች ሳይቀሩ እንደዛ ይሉኛል! ፊልሙን በምንሰራበት ጊዜ በጣም ብዙ ውጣ ውረድ አይተናል፤ በተለይ አንቺ የከፈልሺው መስዋእትነት አይረሳኝም፤ አንዳንዴ በስራ ከመጠመድሽ የተነሳ የረባ ምግብ እንኳ የምትበይበት ጊዜ እያጣሽ ሁለት ቢቸሬ ጭማቂ፣ አንድ መካከለኛ ሰሀን ቅንጬ፥ አንድ ትሪ ፍርፍር ለኮፍ ለኮፍ አድርገሽ ቀምሰሽ የምትውይበት ጊዜ ነበር! ይሄ ጽናት ከምን የመነጨ ነው?
እሷ - የፊልም ስክሪፕት የምታጠናበት ፍጥነት ብዙ ጊዜ ያስደምመን ነበር፤ አንዳንዴ ደራሲው ፊልሙን ከመጻፉ በፊት አንተ ስክሪፕቱን አጥንተህ ትመጣ ነበር፤ ሌላው ድንቅ የሚለኝ ነገር ቀረጻ በተጀመረ ባስረኛው ደቂቃ ላይ ሰውነትህ በላብ ይታጠባል! ያ ሁሉ ላብ ከምን የመነጨ ነው?
እሱ- ከልምድ የመነጨ ይመስለኛል፡፡
እሷ- በመጨረሻ ለወጣቱ የምታስተላልፊው መልክት ካለ፥
እሱ - መጀመርያ አንቺ አስተላልፊና የተረፈውን እኔ አስተላልፋለሁ ::
ከዚህ በተቃራኒ ትዝ የሚለኝ የዋልታው ጋዜጠኛ የስሜነህ ቢያፈርስ ቃለመጠይቅ ነው፤ ስሜነህ ስቱዲዮ ውስጥ ተቀምጦ፤ መዝገበ- ሀጢአት የመሰለች ማስታወሻ ደብተሩን ገለጥ ገለብ ያደርጋል፤ ከዚያ ቀና ብሎ ከፊትለፊቱ ያለውን እንግዳ በሚያስቦካ አስተያየት ያፈጥበታል፤ እና ወደ አእምሮው የሚመጣለት ጥያቄ እንዲህ የሚል ይመስለኛል፤
“ጥሪዬን አክብረው ስለመጡ አመሰግናለሁ፤ ደደብ ነዎት እየተባለ በሰፊው ይነገራል፤ እርስዎ ምን አይነት ደደብ ደረጃ ላይ ራስዎን ያስቀምጣሉ? ከመጽሐፍና ከመከራ መማር የሚችል ደደብ ነዎት? ወይስ ጭንጫ ደደብ ነኝ ብለው ያስባሉ? ወይስ ጭራሽ አያስቡም?”
_______________________________________________

                         ውዳሴ ፍርሃት!
                             አበረ አያሌው

                እና ምን አልሺኝ - ይቅር? ልነሳ?
የጣለኝ ጠላት - ቆሞ ሲያገሳ?
ተይ ልትረፍልሽ - አድፍጬ መሬት፣
ከምታለቅሺ - ነገ በምሬት።
ማንም ቢፎክር - ማንም ቢሰለፍ፣
“ተጎንብሶ ነው - ቀን የሚታለፍ”!
አውቆ የተኛ - ፈሪሽ ነኝ እኔ፣
የፍርሃት ሊቅ - ባለጠመኔ፤
ይፎክራሉ - ግንባር ለመንደል፣
ብቻ ቢቀሩ - ዙሪያውን ገደል፤
አብሮ ነው እንጂ - ነገር የሚጥም፣
ሰው ምን ኾኖ ነው - ጦር የሚገጥም?
አልሞትልሽም - ጠቅምሽ ይመሥል፣
ኖራለኹ እንጂ - እኔ ላንቺ ስል፤
ቀኑን ላድባና - ከመሰቃየት፣
እኔን ስነሳ - ማታ ነው ማየት!

____________________________________________


                  የአህያ ቄራ ጉዳይ
                        ዳዊት ቤንቲ


        ኢትዮዽያ በአህያ ብዛት ከአለም አንደኛ የሆነች አገር ነች። ተራራማ መልክአ ምድሯ ይሄንን ግድ ስላለ አህያ የሚሊዮኖችን ምጣኔ ሀብት የሚደግፍ የጭነትና የመገናኛ አገልግሎትን ያለምንም መተኪያ የሚሰጥ እንስሳ ነው። ከGDP እስከ ዋና የህዝቡ ተግባርና ውጭ ገበያ ድረስ በግብርና ለተመረኮዘች ተራራማ አገር፣ የአህያ ቁጥር ከተነካ አገሪቱ ሁሉን አቀፍ መቀመቅ ውስጥ እንደምትገባ ማወቅ ሮኬት ሳይንስ አይደለም።
ቻይና ራሷ በባህላዊ መድሀኒቷ መተዋወቅ የተነሳ በቻይና የአህዮች ብዛት በ1990 ከነበረው 11 ሚሊዮን ወደ 3 ሚሊዮን ዝቅ ብሎባታል። የዚህ ሁሉ ምንጭ ደግሞ የአህያ ቆዳ ሲቀቀል የሚገኘው Ejiao የሚባል gelatin አለው ተብሎ በሚገመተው ሳይንሳዊ ባልሆነ መድሀኒት ጥቅም ነው። ይህ Ejiao በኪሎ እስከ 390 ዶላር ድረስ ይሸጣል።
የገናናይቱን የአሁን ወዳጃችንን ባህላዊ መድሀኒት ፍላጎት ለማርካት አህዮች እየታረዱ፣ የአህያ ቆዳና መሰል ተረፈ ምርቶች ወደዛው ይላካሉ። ቻይና ፈለገች ማለት አገር እስኪንቀጠቀጥ፣ የአገር ኪስ ተበርብሮና ተራቁቶ ይላካል። የዝሆን ጥርስና የአውራሪስ ቀንድ እንዲሁም የሴኔጋል Rosewood እልቂት ምንጩም የታላቂቱ አገር ፍላጎት ነው።
Rosewood የሚባል የሴኔጋልና የጋምቢያ ጫካዎች ንጉስ የነበረ ዛፍ አለ። ጋምቢያ በብልሹ አስተዳደር ያላትን rosewood ሙልጭ አድርጋ ጨፍጭፋ ስነምህዳሯን አራቁታ ወደዛው ስትልክ ቆየች። የራሷን አስጨፍጭፋ አልበቃትም፤ አይኗን በrosewood ሀብት ወደ በለጸገች ወደ ጎረቤት ሴኔጋል አነሳች። ጎረቤት ሴኔጋል ግን ችግሩን ተረድታ ማእቀብ ጥላ ነበር። በአፍሪካ ማእቀብ ምን ዋጋ አለው? የጋምቢያ ኮንትሮባንዲስቶች ከሴኔጋል ጥቅመኞች ጋር ተሳስረው የሴኔጋልን rosewood ሙልጭ አድርገው ጨፍጭፈው በጋምቢያ እያስወጡት ይገኛሉ።
አለምአቀፍ የባለጡንቻዎች መዋእለንዋይን ጥንካሬ መቋቋም የማይችለው የሴኔጋል ተቆጣጣሪ መዋቅር፣ ይሄንን በጭራሽ መቋቋም አቅቶት ሴኔጋል ማእቀብም ጥላ እያለ እንኳን የrosewood ደኗ እየተራቆተና በጋምቢያ በኩል ወደ ወዳጅ አገር እየተላከ ወደ ትልቅ አካባቢያዊ ቀውስ ገብታለች።
እንደ rosewood ምሳሌ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እኛ አገር አህያን ማረድ ተከልክሎ እንኳን ጎረቤት ኬንያ ስላልተከለከለ፣ አህያ በኮንትሮባንድ ወደ ኬንያ በገፍ እየተላከ እንደነበረና ብዙ ባለሙያዎች የኢትዮዽያ የአህያ ሀብት ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደነበር ዘግበውታል። ባለፈው በቢሾፍቱ የተከፈተውን ቄራ በብዙ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጩኸት ስራ ማስቆም ተችሎ ነበር።
የአፍሪካ አህዮች ከግብጽ እስከ ደቡብ አፍሪካ እያለቁ መሆኑንና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ አደገኛ ጥላ እያጠላ መሆኑን አያሌ ጥናቶች ያመለክታሉ። እነዚህ የአፍሪካ አገሮች ይሄንን ዋና ችግር ተረድተው ብዙዎቹ አህያ እርድንና ወደዛች አገር መላክን የከለከሉ ሲሆን ከእነርሱም ኡጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ቦትስዋና፣ ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊና ሴኔጋል ይገኙበታል። ቦትስዋና በአጭር ጊዜ 37% የአህያ ሀብቷን ካጣች በኋላ ነበር ከእንቅልፏ የባነነችው።
አህያ ለሚሊዮን ኢትዮዽያውያን ምንድነው?
አህያ ገበሬው እህሉን ከማምረቻ ስፍራ ወደ መውቅያ ማከማቻና ገበያ የሚወስድበት ብቸኛ የማጓጓዣ አውታር ነው፡፡
አህያ ማዳበርያውን ከማከፋፈያ ወደ ወደ ማከማቻና እርሻ ቦታ መውሰጃ ነው።
የገበሬውን አጠቃላይ የኑሮ ፍላጎት የሚያሟሉ ግብአቶችንም ሆነ ምርቶች የሚያካሄድበት የurban-rural linkage ቁልፍ ማእከል ነው።
ከተማ ውስጥ የግንባታ ቁሳቁስ፣ እህልና ውሀ ወደ መጨረሻ ተጠቃሚዎች ማድረሻ መሳርያ ነው። ሌላም ሌላም!
ጎረቤት ኬንያ በ2012 የአህያን እርድ ከፈቀደች በኋላ ብዙ አንቀላፍታ ቆይታ በፌብሩዋሪ 2020 ክልከላ ጥላበታለች። በአስር አመት ውስጥ የኬንያ የአህያ ብዛት ከ1.8 ሚሊዮን ወደ 600, 000 ሲያሽቆለቁል፥  የአህያ እርድ በዚህ ከቀጠለ በ2023 የኬንያ አህዮች ሙሉ በሙሉ እንደሚያልቁ ተተንብዮ ነበረ።
ጎረቤት ኢትዮዽያ መጡልና! ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣልም አይደል ነገሩ! ስንት በመቶ አህያ ስናጣና ኢኮኖሚያችን በስንት አሀዝ ሲመታ ነው እኛስ የምንባንነው?

______________________________________________

                          ከትናንቱ ስህተት ምን ያህል ተምረናል?
                                 ሙሼ ሰሙ


            ከ5 በላይ ትልልቅ ስታዲየሞችና ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በርካታ ኳስ ሜዳዎችን ያስገነባችው ኢትዮጵያ፣ አንዱም ስታዲየሟ ደረጃውን የጠበቀ ስላልሆነ፣ ብሔራዊ ቡድናችን ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ውጭ እንዲያደርግ መወሰኑን ከስፖርት ዞን አነበብኩ። ክስተቱ ለስፖርት ማህበረሰብም ሆነ ለሀገር ሀዘንና ውርደት መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ለምን ሊሆን ቻለ?!
አደይ አበባ ስታዲየም በጊዜ አልተጠናቀቀም!
ባህር ዳር መስፈርቱን አላሟላም!
ሀዋሳ ስታዲየም በሜዳው ብልሹነት ስራ አቁሟል!
ድሬዳዋ ከዓለም አቀፍ መስፈርት በታች ነው
አበበ ቢቂላ የመጫወቻ ሜዳ ከደረጃ በታች ነው
አዲስ አበባ ስታዲየም በእድሳት ላይ ነው (መረጃ፡- ስፖርት ዞን)
በቢሊየኖች ወጭ ተደርጎባቸው የተገነቡ ስታዲየሞቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድር ማሰናዳት የማይችሉ እንደሆኑ ካፍ ባደረገው ፍተሻ ስላረጋገጠ፣ ጨዋታችንም በሌላ ሀገር እንዲሆን ተገደናል።
ሜዳዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግም ከመነሻቸው በላይ ወጭ እንደሚፈልጉ ተገምቷል።  ያለፈው ስርዓት የልማት ትርክቱ የተዘጋ በር ገርበብ ባለና መጋረጃው በተጋለጠ ቁጥር ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የወረደባት የዘረፋ መዓት ህልቆ መሳፍርት የሌለው መሆኑ አሳዛኝ ነው። በእልፍ ፕሮጀክቶች መነሻነት በሀገራችንና በሕዝቧ ስም እያናጠረብን ያለው የውጭ ሀገር ብድር፣ ቀጣዩ ትውልድ እንኳን ለዝንተ ዓለም ከፍሎ የሚጨርሰው አይደለም።
በየዘርፉ ያለው ጉድ መጨረሻው ይናፍቃል። ያልተዘረፈ፣ ከደረጃ በታች ያልሆነ፣ ተጀምሮ መቋጫ ያላጣ፣ ባለቤቱ የማይታወቅና ቀሪ ሀብቱ የት እንደገባ የማይነገርለት ፕሮጀክት የትየለሌ ነው። የትናንቱ ልማት በአብዛኛው ላዩ እንጂ ውስጡ ቀፎ እንደነበር በተደጋጋሚ ታይቷል። ዛሬስ ልማቱ የት ደርሷል? ወዴትስ እየተገፋ ነው?! ከትናንቱ ስህተትስ ምን ያህል ተምረናል? አሁንም ጥያቄው ይህ መሆን አለበት!?


Read 2429 times