Print this page
Tuesday, 26 October 2021 00:00

የብራዚሉ መሪ በ600 ሺህ ዜጎች ሞት እንዲከሰሱ ሃሳብ ቀረበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የብራዚል ሴኔት አባላት ፕሬዚዳንት ጄር ቦልሶናሮ፣ ኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት እንዲዳረጉና ከፍተኛ የሆነ ሁለንተናዊ ቀውስ እንዲፈጠር በማድረጋቸው ጅምላ ግድያን ጨምሮ 11 የተለያዩ የወንጀል ክሶች ሊመሰረትባቸውና ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
አንደ አንድ የአገር መሪ ህዝባቸውን ከአስከፊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጥፋት ለመታደግ ጥረት ማድረግ ሲገባቸው፣ በየአደባባዩ "ጉንፋን ነው አትደናገጡለት; እያሉ ሲያጣጥሉት በከረሙት ቫይረስ አገራቸውንና ህዝባቸውን ክፉኛ ተጎጂ በማድረጋቸው የሚወቀሱት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጄር ቦልሶናሮ፤ #እርግጥም ከፍተኛ ጥፋት ፈጽመዋልና ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ይገባል; ብለዋል የሴኔት አባላቱ፤ በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ቀውስ ዙሪያ 6 ወራትን ፈጅተው የሰሩትን ጥናት መሰረት አድርገው ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረጉት ሪፖርት፡፡
ከ1 ሺህ በላይ ገጾች እንዳሉት የተነገረው ይህ ዝርዝር ሪፖርት፣ ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ ኮሮና ቫይረስን በአደባባይ በማናናቅ፣ ህዝቡ ጥንቃቄ እንዳያደርግ ከመቀስቀስ አንስቶ ሆን ብለው ክትባት እንዲዘገይ እስከማድረግ፣ ቫይረሱ በስፋት እንዲሰራጭና ብራዚል ከአለማችን አገራት መካከል ሁለተኛው ከፍተኛ ሞት እንዲመዘገብባት ሰበብ ሆነዋልና ለፈጸሙት ጥፋት ሊቀጡ ይገባል ሲል ምከረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
ሶስተኛ የስልጣን ዘመናቸውን በማገባደድ ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ፣ 11 የወንጀል ክሶች ሊመሰረቱባቸው እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ በቀረበበት ሪፖርት ላይ በቀጣይ 11 አባላት ያሉት የሴኔት ኮሚቴ ድምጹን እንደሚሰጥበትና ክሶቹን ለመመስረት ሌሎች ሂደቶች መሟላት እንደሚኖርባቸው የጠቆመው ዘ ጋርዲያን፤ ከእሳቸው በተጨማሪ ልጆቻቸውና የቀድሞው የጤና ሚኒስትራቸው ኤድዋርዶ ፓዙኤሎም በተመሳሳይ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚገባ በሪፖርቱ መጠቀሱን አመልክቷል፡፡
ቦልሶናሮ ቢያንስ በስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሎ ባይጠበቅም፣ ጉዳዩ በቀጣዩ አመት በሚካሄደው ምርጫ ለመወዳደር ባላቸው ዕቅድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረሱ የማይቀር መሆኑን አክሎ ገልጧል፡፡
በብራዚል ወረርሽኙ መቀስቀሱን ተከትሎ የአገሪቱ የጤና ሚኒስትሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአለም የጤና ድርጅት በተደጋጋሚ ይሰጧቸው የነበረውን ምክርና አስተያየት ችላ በማለትና በማጣጣል፣ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ያላግባብ ለሞት እንዲዳረጉ ማድረጋቸውን ነው ሪፖርቱ የሚያሳየው፡፡
ፕሬዚዳንቱ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ከውጭ አገራት በአፋጣኝ እንዳይገቡ  በማድረግ ከ95 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ እንዲሞቱ አድርገዋል፤ በህዝባቸው ላይ ከጅምላ ግድያ ያልተናነሰ ወንጀል ፈጽመዋል ያለው ሪፖርቱ፣ አልፎ ተርፎም ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድሃኒቶችን እንዲወስድ ለህዝቡ ያልተገባ ምክር ይለግሱ እንደነበርም ተነግሯል፡፡
በብራዚል የኮሮና ሟቾች ቁጥር ከሰሞኑ 600 ሺህ መድረሱን ተከትሎ መገናኛ ብዙሃን ስለጉዳዩ የጠየቋቸው ፕሬዚዳንቱ፤ የሰለቸኝ ነገር ቢኖር ስለ ኮሮና ሟቾች መጠየቅ ነው ሲሉ በአደባባይ መናገራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 2756 times
Administrator

Latest from Administrator