Saturday, 23 October 2021 14:06

ጉስቁልናችንን ማን ሰረቀን? ስቃያችን ለምን መከነ?

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

 ሕቡዕ አሻራዎች
ባልተመደረከው፣
ባልታየው ተውኔት፣
ባልተተነተነው፣
ኢ-ክቱብ ድርሳኔ፣
ባልተሸነሸነው፣
ኢ-ሥፍር ዘመኔ፣
እልፍ ጣት አርፎብኝ፣
በማን ወጣሁ ልበል?
በማን ተቀረጽኩኝ?
(40 ጠብታዎች- ስንቅነህ እሸቱ[ኦታም ፑልቶ])
በአማርኛ ስነ-ጽሑፍ ውስጥ የአጻጻፍ ይትባህሉ ለየት የሚልብኝ አንድ ደራሲ አለ፡፡ በብዕር ስሙ ኦታም ፑልቶ ይባላል፡፡ ‹የሲሳዬ ልጆች፣ ኬክሮስና ኬንትሮስ› የተሰኘ መጽሐፉ ገጽ 104 ላይ በገፀባህሪያቱ ምልልስ አማካኝነት የሚደንቅ ሐሳብ አስፍሮ አየሁ፡፡ እንዲህ ይነበባል...
‹‹የቻይናውያን ውርደት ኮንፊሸስና ላኦ ዙን፣ የራሺያውያን ስቃይ ፑሽኪንና ዶስቶየብስኪን፣ የደቾች ሰቆቃ ቫን ጎን፣ የህንዶችና የደቡብ አፍሪካውያን ወዮታ ጋንዲንና ማንዴላን፣ የጥቁር አሜሪካውያን ህማም የጃዝ ሙዚቃን ሲወልድ፣ ምነው የሃበሻ ረኃብና ድኅነት፣ ውርደትና ሐፍረት እንዲህ መከነ?››
እንዴት የሚደንቅ እይታ ነው! በዓለም ላይ ከአይሁዳውያን ቀጥሎ እጅግ የበዛ ስደት፣ ረሃብ፣ ግዞት፣ ቸነፈር፣ ጦርነት...የተጋፈጡ ህዝቦች ብንኖር እኛው ነን። ኢትዮጵያውያን ለሺህ ዓመታት የተሸከምነው ጭቆና ጫንቃችንን ያጎበጠው ምንዱብ ህዝቦች፣ በአንድ ክርስቶስ ስም በተሳሉ ሁለት መንታ ሰይፎች እንካ ስላንትያ የተቃመስን፣ ይህን ታሪክ በደማችን የጻፍን፣ ‹ስዩመ እግዚያብሔራዊ› ሺህ ፈላጭ ቆራጭ ነገስታትን ያገለገልን፣ ከሺንብራ ኩሬ እስከ አድዋ የሞትን የተጋደልን፣ ለጭቃ ሹም ያደገደግን፣ ለምስለኔ ያገለደምን ህዝቦች... እኛው ነን... እኛው!
በእርግጥ ‹በራሳችን› ፊደል እንጽፋለን። ፊደል አለን፡፡ ሆኖም ዛሬም ሚሊዮናት ወገኖቻችን መሀይማን ሆነው እናያለን። በዓመት በአማካይ አስር ገጽ የማያነቡ፣ በዓለም አቀፍ የሐሳብ ገበያ ምንም ሐቲት ያላዋጡ የተናቁ ሕዝቦች ነን፡፡ ሙዚቃን በኖታ በመጻፍ የመጀመሪያዎቹ ሆነን ሳለን ሙዚቃ የማይገባቸው ዘላኖች ተብለን እንሰደባለን። ለአክሱም ሐውልትና ለላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ዛሬም ከሺህ ዓመታት በኋላ ባዕድ ነን፡፡ እነዚህን እጹብ ድንቅ የኪነ-ሕንፃ ጥበባት ያቆምን እኛ፣ የምንኖረው ዛሬም በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ነው፡፡
እናስ ጉስቁልናችንን ማን ሰረቀው? ስቃያችን ለምን መከነ? ኦታም ፑልቶ ለዚህም ተከታይ ጥያቄ የተጠቀሰው ገፅ ላይ መልስ አለኝ ይላል፡፡
‹‹የራሳችንን ሸክም እንኳን ለብቻችን ለመሸከም ስለማንፈቅድ ነው፡፡... ታዲያ የሁላችንንም ቀንበር ተሸክሞ አርነት የሚያወጣን መሲህ ከወዴት ይምጣ? የእያንዳንዳችንን የሰቆቃ ዝቃጭ ጨልጦ ትንሳዔያችንን ያውጅ ዘንድ ማንን እንጠብቅ? እስራዔላውያንን ከግብፅ ባርነት ያወጣው ማህበርና እድር ነበር? አይደለም፡፡ አረባውያንን ከድንቁርናና ከጣኦት አምልኮ የታደገው ማህበርና እድር ነበር? አይደለም። አንድ ሰው ነው፡፡ አንድ ሰው ብቻ... በፈሪነታችን፣ በሽሽታችን፣ በግለ እምነት አልባነታችን... ፍጹም ድህነትን የመሰለ ሀብት፣ ፍጹም ውርደትን የመሰለ ክብር፣ [እንዴት] እንዲሁ ባክኖ፣ ፍጹም ከንቱ ሆኖ ይቅር?...››
ጭቆና ለአንድ ዓይነት የሕይወት ለዛ ግኝት፣ የኪነት ፈጠራ፣ የጀግንነት ሙያ፣ የጋራ ተጋድሎ መነሻ ነጥብ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ከዚህ ሁሉ ስቃያችን፣ መታረዛችን፣ መገለላችን፣ ለዓለም ሁሉ በተለፈፈ መራባችን... ቀለም አጥቅሰን የሚወክለን አንድ ዓይነት ምስል መፍጠር አልቻልንም፡፡ ስንኝ ቋጥረን ዜማ አልብሰን ለመዝፈን መውተፍተፋችን ባይቀርም ዛሬም ዓለም ሁሉ የሚያውቀን በረሃብ ተምሳሌትነታችን ብቻ ሆኗል። የእልፍ አዕላፋት እንስቶቻችን እንባ፣ የጭሰኞችን ሁሉ ዋይታ የሚውጥ የሚያሰርግ የደደረ ሰብዕናችን ከየት መጣ? እናስ ጉስቁልናችንን ማን ሰረቀን? ስቃያችን ለምን መከነ?
የአሜሪካ የእርስበእርስ ጦርነት እንደ አብርሃም ሊንከን ያለ የማይናወጥ ብልህ መሪን ፈጠረ፡፡ የህንዳውያን ጭቆና የምዕተዓመቱን ታላቅ ሰብዕና ጋንዲን አስገኘ። የአፓርታይድ አሰቃቂ አገዛዝ ለእኛ እንኳን የተውሶ ጀግናችን የሆኑትን ኔልሰን ማንዴላን አጎላ፡፡ የአየርላንዳውያን በእንግሊዞች በኃይል መወረር ለጆርጅ በርናንድ ሾው ዓይነት ጠቢባን መነሻ ቁጭትን እንደሰጠ ይታመናል፡፡ የእኛ ለሺህ ዓመታት የተለጠጠ ስፍር ቁጥር የለሽ መጫረስ፣ እንዴት አንድ ዓይነት የሕይወት ለዛ አንድ ጀግና መፍጠር ተሳነው? የእኛ ፍጅት የእሪያዎች ነበር እንዴ? ከሆቺሚኒ እስከ ቼጉቬራ ጭቆና ጀግኖችን ይፈጥራል፡፡ እኛ ጋ ሲመጣ ይህ እንዴት ሊሰራ አልቻለም?
መገለልና መናቅን ያክል ቁጭት፣ መራብንና በሰንደቃላማችን መለመንን ያክል ውርደት፣ መሰደድን ያክል ግዙፍ ሐፍረት ተከናንበን እንዴት አንድ ጋንዲን፣ አንድ ማንዴላን፣ አንድ ፑሽኪንን፣ መፍጠር ተሳነን? የጋራ ስቃይን ያክል ውድ ሀብት ይዘን እንዴት በህብረት የምንዘምረው አንድ መዝሙር አጣን? እውነትስ የእኛ የሺህ ዓመታት ስቃይ፣ ጭቆና፣ ጉስቁልና፣ ረሃብ፣ እጦት፣ ቸነፈር...የሆነ ዓይነት ንጥር ግኝት፣ ጀግንነት፣ ጥበብ መፍጠር ለምን ተሳነው? ለምን? ጥበብም ሆነ ታላላቅ ሰዎች የሚፈጠሩት ይህን በመሰለው ተቃርኖ ውስጥ አልነበረምን? ስቃያችንን ማን ሰረቀን? እና ለምን ከዚህ የስቃይ ሀብታችን ወርቁን ማውጣት ተሳነን? ለምን? እናስ ጉስቁልናችን ለምን መከነ? ስቃያችንን ማን ሰረቀን?


Read 899 times