Saturday, 23 October 2021 13:07

‘ሰውም’ በቦታው፣ ‘ቡልዶዘርም’ በቦታው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሀገር ሰላም ብላችሁ በመንገድ እየሄዳችሁ ነው፣ ያውም በተወሰነላችሁ የእግረኞች መንገድ፡፡  ድንገት የሆነ ቡልዶዘር ምናምን ነገር ከፊት ለፊት ይላተማችኋል፡፡ ‘ቡልዶዘር’ በእግረኛ መንገድ ላይ ምን ያደርጋል? ተንገዳግዳችሁ ካበቃችሁ በኋላ ቀና ብላችሁ ስታዩ ምን ቢሆን ጥሩ ነው...‘ሰው’ ሆኖ የመጣ ቡልዶዘር! ቂ...ቂ...ቂ... እንደው...አለ አይደል... “ብንለታተምስ ምን ችግር አለው፣ ለምደነው የለም ወይ...” ከተባለም ወይ የምንጠቀምባቸው የእግረኛ መንገዶች በክብደት ይከፋፈሉልንማ! አሀ...ሁሉም እንደ የአቅሙ ሲሆን... አለ አይደል.... ለአቤቱታም አያመችማ፡፡
“ሰውየው እያየ አይሄድም እንዴ!”
“ምን ሆነህ ነው እንዲህ የምትጮኸው?”
“መቶ ኪሎ ምናምን ነገር ያህል እላዬ ላይ አይከመርብኝ መሰለህ!”
“የገጨህ ስድሳ አራት ኪሎ፣ አንተ ስድሳ ሦስት ተኩል ኪሎ... ምን ይጠበስ ነው የምትለው? ከተገጪነት ወደ ገጪነት ‘ማደግ’ ከፈለግህ (ቂ...ቂ...ቂ...) ከሀምሳ ኪሎ በታች ክብደት ያላቸው ምድብ ውስጥ አስገቡኝ በል!” እርፍ!
እኔ የምለው...መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...  ኸረ እባካችሁ በከተማው እንደ ከተሜ እንሁን! አሀ... ትከሻን ሳይገጩ፣ ሳይገፈተሩ፣ እግርን ሳይረገጡ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ እየሆነ ነዋ! ደግሞ ለዚህ ብለን... ‘የአዲስ አበቤዎች በእግረኞች መንገድ ላይ ላይ እንደልብ የመንቀሳቀስ መብት አስጠባቂ ኮሚቴ፣’ ምናምን እናቋቁም! ኮሚክ እኮ ነው... ቀኑን ሙሉ ‘ረሽ አወር’ የሆነባት…. ሰውና መኪና በጩኸት የሚፎካከርባት የምትመስል ከተማ ሦስት ሜትር ተኩል እሰክትንደረደሩ ድረስ ተገፍትራችሁ እንደገና በግልምጫ የምትሸነቆጡበት ከተማ! ተለትማችሁ፣ ወይም እግራችሁን ተረግጣችሁ… ይህ አልበቃ ብሎ ‘ምርቃት’ ይመስል በሚጉረጠረጡ ዓይኖች ከፍ ዝቅ የምትደረጉባት ከተማ!
“ወንድም እያየህ አትሄድም እንዴ!”
“ምን?”
“እንዴት እንደረገጥከኝ ጫማዬን አታየውም!”
“እውነት! ጫማህ እንዳይቆሽሽ ከፈለግህ፣ ለምን በአሻራ በሚከፈትና በሚዘጋ ቪ ኤይት አትሄድም!” የምር ግን እንዲህ አይነት መልስ የሚሰጡ ‘የመንገድ ላይ ረጋጮች’ ካሉ፣ ራሳቸውን ከጊዜው ጋር ‘አፕዴት’ አድርገዋል ማለት ነው! ቂ...ቂ...ቂ...
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ስለ መንገድ ላይ መላተሞች ስናወራ ሆነ ተብለው የሚደረጉትን ጠንቀቅ ማለት ነው፡፡ ተገጭታችሁ እኮ መገጨታችሁን ገና ሙሉ ለሙሉ ሳትረዱ የሚጠመጠምባችሁ፤ ገጪ ይቅርታ ጠያቂ ሳይሆን፣ ገዴላችሁም ኪሳችሁ ውስጥ ያለውን ሊጠመጥምላችሁ ሊሆን ይችላል!
የሆነ ጊዜ ሆነ የተባለ ነገር ነው...እሱዬው የሆነ ቦታ በቀጠሮ ሰዓቱ ለመድረስ እዚህ ከተማችን መሀል ላለመጋጨት እየተሹለከለከ እየተጓዘ ነው፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ጠምዘዝ ብሎ ለማለፍ ሲሞክር ዓይኖቿን ስማርተፎኗ ላይ ያደረገች  ሸላይ ከተሜ ትለትመዋለች። እሱ እንደሚለው፣ ግልምጫውን ተዉት። ተናገረችኝ ያለው ነገር ግን (“ሰደበችኝ ያላቸው ስድቦች...” ያልተባለው… ‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ ለመሆን ያህል ነው! የምር ግን ስለዚህ ‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ ስለሚሉት ነገር ማውራት አለብን፡፡ አሀ...አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ አሪፍ ነገር ቢሆንም፣ አንዳንዴ እኮ ልክ ልካችንን ‘ካላጠጡን’ ወይም — ‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ ያልሆነ አባባል ለመጠቀም—  —‘እስከ ዶቃ ማሰሪያችን’ ካልነገሩን የማንሰማው ቁጥራችነ እየበዛ ነዋ! ይኸው፣ ለ‘ስብሰባ’ የሚሆን አንድ ‘ሰበብ’ አዋጣሁ ማለት አይደል!)
እናላችሁ...ተረግጣችሁም፣ ተገፍትራችሁም አይደለም ይቅርታ ልትጠየቁ፣ ቁጣና ግልምጫው ከቀረላችሁም ዕድለኞች ናችሁ!
ከተማዋ ዓይነግቡ የሆኑ ነገሮች እየበዙባት ነው፡፡ ደስ ይላል፡፡ የእውነት እስኪበቃን ቀና ብለን የምናያቸው ህንጻዎች ማየት መጀመራችን እሰየው ነው... ውስጣቸው የሚሠሩት ሥራዎች ሀገርና ህዝብን ቀና የሚያደርጉ  እስከሆኑ ድረስ… እጆቻችን የዛች አንስሳ እንትንን እስኪመስሉ  ድረስ እናጨበጭባለን፡፡ ዘላለማችንን እድሜ ጠግበው ያረጁና፣ እንደ አዲስ ተሠርተው ከአሮጌዎቹ የተሻለ መልክ የሌላቸው ‘ህንጣዎች’ ማየት ሰልችቶን ነበራ! (በቀደም ከወዳጆቻችን ጋር ይሄን ረጅሙን ህንጣ ስናይ ምን ተባባልን መሰላችሁ... “አሁን ሰው እዛ ላይ ተቀምጦ ሥራ ሊሠራ ነው!” ልክ ነዋ...ስለ ‘ጂ ፕላስ ትዌልቭ’ ኮንዶሚኒየም ስናወራ... “አሁን ማነው አምኖ አስራ ሁለተኛ ፎቅ ድረስ የሚወጣ!” ስንባባል ኖረን… ‘ሰርቲ ምናምኑ… እኔ የምለው... እነኚህ ‘ፋይናንሽያል ኢንደስትሪ’ ምናምን የሚባሉት ውስጥ ያሉት ብቻ ናቸው እንዴ ‘ሽቅብ፣ ሽቅብ’ የሆኑ ህንጻዎች የሚሠሩት!
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... እነኚህ ሰፋ እየተደረጉ ንጣፍ እየተነጠፈባቸው የተሠሩት መንገዶች ... አለ አይደል ... በቃ አሪፍ ናቸው፡፡ ትከሻችን ቡልደዘሮች ሳይለትሙን፣ ሳንረጋገጥ እንዲህ ሰፋ፣ ጸዳ ባሉ መንገዶች መንቀሳቀሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የምር...እንደ ሽርሽር አይነት ነገርም ብንሞክር አያሳፍሩም... በቃ አሪፍ ናቸው ነው፡፡ እናላችሁ... ገና ከአሁኑ አሪፍነታቸውን የሚቀናንሱ ነገሮች ስለምናይ ነው ጥያቄ ያለን፡፡ ሁሉም ቦታ ለምንድነው ጥንቅቅ ብለው የማይጨረሱት?። ለምንድነው አብዛኛው ነገር በደህና ሁኔታ ተሠርቶ ማለቂያ አካባቢ  እዚህም፣ እዛም የግዴለሽነት የሚመሳሰሉ ነገሮች የምናየው። በደንብ ጥግ ድረስ ጡቦችን ያለበሱ ቦታዎች ምኔው? ይሄድ ይሄድና...አለ አይደል... ከአንድ ዙር በታች የሆነ ሲቀር ተንጠልጥለው የሚቀሩበት ሙያዊ ምክንያት ካለ ይነገረንና ዓይተን እንዳላየን ይለፈንማ! ክፍተቶቹ የጠቅላላውን መንገድ መልክ ነው የሚያበላሹት፡፡ እናማ...ተክሎቹና አበቦቹ ደግሞ እነሱን ሀያ አራት ሰዓት ለመንከባከብ ብቻ የተዋቀረ ክፍለ ከሌለ እመኑኝ...ከእኛ ከተሜዎች “ሆ ኬርስ!” ማለት የስልጣኔ የወርቅ ሜዳሊያ የሚመስለን ስላለን ውሀ ቅዳ፣ ውሀ መልስ እንዳይሆን!
ስሙኝማ...ዘንድሮ ትንሽዬዋን ነገር ራስ ዳሸን ተራራን ማሳከል የተለመደ ስለሆነ ‘ላለመበለጥ’ እንዳይረሳብን የምንፈልገው ነገር አለ...ሀሳብ በማቅረባችን ለከተማዋ ውበት የከተሜነት ግዴታችንን እንደተወጣን ይያዝልንማ! አሀ...ልክ ነዋ! አንድ ቀን የሆነ ወዳጃችን አጠገባችን የሆነ ነገር እንዳሰኘው አይነት እንደ ማዛጋትም ያደርገዋል እንበል...
“አንተ ዛሬ ምን ሆነሀል? ልክ አትመስልም።”
“እባክሀ ድብር ነው ያደረገኝ፡፡”
“ከመሬት ተነስቶ ድብር ይልሃል እንዴ!”
“እንደሱ ሳይሆን... ሻይ እንዳማረኝ ነገር! ኪሴ ደግሞ ባዶ...”
“አንተ ለሻይ ነው እንዴ እንደዚህ የምትሆነው! እኔ እገዛልሃለሁ፡፡ (አእምሮው ውስጥ ‘ሴቭ’ ባደረገው ሲቪ ላይ...“ያከናወንኳቸው በጎ ተግባራት...” በሚለው ባዶ ዓምድ ስር “አንድ ቀን ሻይ ላማረው ወዳጄ ሻይ በሎሚ መጋበዝ...” የሚል ይጨምርበታል፡፡
በሌላ ቀን ደግሞ በሆነ ምክንያት እንደ ማዛጋት የማድረግ ነገር የወዳጃችን ተራ ይሆናል፡፡
“አጅሬው፣ ስትንጠራራ እኮ ሦስት ቀን በዓይንህ እንቅልፍ ያልዞረ ነው የምትመስለው! ችግር አለ እንዴ!”
“እባክህ ክትፎ አምሮኝ ነው፡፡”
“ምን! አሁን አይደለም ክትፎ ምንቸት አብሽ አማረኝ የሚባልበት ጊዜ ነው?”
“አንተ ደግሞ ቴረር አታብዛ! ይልቅ የእንትና ቤት ክትፎን ጋብዘኝ እስቲ!”
“ሰውዬ፣ የትኛው እቁብ ደረሰው አሉህ?”
ይሄኔ ሲቪውን ላጥ ያደርጋታላ!
 “በዛ ሰሞን ሻይ አማረኝ እያልከ ስታዛጋ በሌለኝ ገንዘብ እንትን ካፌ ሻይ በሎሚ አልጋበዝኩህም!”
እና ምን ለማለት ነው... ከፍ ብሎ ስለ ከተማችን የቀረበው ሀሳብ አእምሯችን ውስጥ ባለው ሲቪ “የነዋሪነት ግደታ ስለመወጣት...” በሚለው ዓምድ ስር “በጋዜጣ ላይ ስለ ንጣፍ መንገዶች የቀረቡ ሀሳቦች...” የሚል ማስፈራችንን ለማሳወቅ ያህል ነው፡፡
እናማ...አንግዲህ ጨዋታም አይደል...በዚህ በኩል ከተማዋ መልክ እያወጣች፣ በዛ በኩል ከተሜነታችን መልከ እያጣ እንዴት ነው ነገሩ!
ስሙኛማ...ከተሜነት ማለት ‘መሰልጠን’ ምናምን የሚሉ ቅጣዮች ሳይገቡበት ‘ሰው’ በመሆን ብቻ ሊኖሩ ስለሚገቡ ባህሪያት ማለት ነው፡፡ በስነ ስርአት የመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ከተማም ሆነ፣ ገጠርም ሆነ፣ በረሀም ሆነ ዘወር ብሎ ማለፍ እየተቻለ፣ ሰው ላይ መከመር ‘ስልጣኔ’ ቅብጥርስዮ የሚባሉ ነገሮች አያስፈልጉትም፡፡
እናማ... ‘ሰውም’ በቦታው፣ ‘ቡልዶዘርም’ በቦታው ይሁኑልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2019 times