Saturday, 23 October 2021 13:01

የህወሓት ታጣቂዎች በ4 የደቡብ ወሎ ከተሞች ላይ ውጊያ ከፍተዋል

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(9 votes)

  - በውጫሌ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል ።
   - በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ አምባሰል ተለሁደሬና ወረባቦ ላይ ጦርነቱ ቀጥሏል።
    - የተፈናቃዮች ቁጥር ከአቅም በላይ ሆኗል ተብሏል
      
           በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ በሚገኙ 4 ወረዳዎች ላይ ከህውሃት ታጣቂ ሃይሎች ጋር ውጊያ እየተካሄደ ነው። ሰሞኑን የውጫሌ ከተማን ተቆጣጥሮ የነበረው አሸባሪ ቡድኑ፣ በከተማው ነዋሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል ተብሏል።
የሕወሓት ታጣቂ ሃይሎች ባለፈው ሰኞ ለጥቂት ሰዓታት ተቆጣጥረዋት የነበረውን ታሪካዊቷን  የውጫሌ ከተማ የመከላከያ ሰራዊትና የአካባቢ ሚሊሺያዎች  በወሰዱት እርምጃ  ከተማውን ከአሸባሪው ቡድን  አስለቅቀዋል። በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የውጫሌ  አካባቢ በመንግስት ቁጥጥር ስር ቢሆንም፣ ታጣቂ ቡድኑ  ጎልቦ ወደሚባል አካባቢ ቆርጦ መግባቱንና ከመንግስት ሃይሎች ጋር ውጊያ መግጠሙን ምንጮች ጠቁመዋል። ታጣቂው ቡድን በደቡብ ወሎ አቅጣጫ ደሴ ከተማን ለመያዝ የሞት ሽረት ትግል እያካሄደ ነው ተብሏል ።
ከውጫሌ ከተማ ከመኖሪያ  ቀዬአቸው  ሸሽተው ኮምቦልቻ ከተማ ከገቡ ተፈናቃዮች መካከል አብዛኛዎቹ ሕጻናትና ሴቶች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። ከተፈናቃዮቹ መካከል ያነጋገርናቸው ተመስገን አያሌውና ሀብቴ ጌቱ የተባሉ ወጣቶች እንደሚገልፁት፤ የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች በውጫሌ ከተማ በቆዩበት ጥቂት ሰዓታት ለመስማት የሚከብዱ ዘግናኝ ድርጊቶችን በነዋሪው ህዝብ  ላይ  ፈጽመዋል። ባለፈው እሁድ አመሻሽ ላይ ቡድኑ በከተማዋ  ላይ በፈጸሙት የከባድ መሣሪያ ጥቃት ሁለት ወንድማማቾችን ጨምሮ  የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አልፏል ።
የደቡብ ወሎ ዞን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሠይድ አህመድ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት አሸባሪው ቡድን ሰሞኑን በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ ከሚገኙ አስር ከተማ አስተዳደሮች ግማሽ ያህሉን በመውረር ከተሞቹን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ውጊያ እያካሄደ ነው። በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ በሚገኙ የገጠር ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች አሸባሪውን ቡድን ለመመከት ወደ ግንባር እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ መደረጉና በርካታ ወጣቶች ጥሪውን ተቀብለው ውጊያውን መቀላቀላቸውን  አቶ ሰይድ ገልጸዋል።
አሸባሪው ቡድን የከፈተውን ጦርነት በመሸሽ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ ደሴና ኮምቦልቻ የሚገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት  እየጨመረ መምጣቱንና የተፈናቃዩ ቁጥር ከተሞቹ ለመቀበል ከሚችሉት በላይ መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በህዝቡ ላይ የሚፈጽመው ዘግናኝ ወንጀል በሚዲያ ሊገለጽ የማይችልና አሰቃቂ ነው ያሉት ሃላፊው፣ ዝርዝር የጉዳት መጠኑን የሚገልጽ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሠራ ነው ብለዋል። ይህንን በንጹሃን ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት አቅሙ የደረሰ ሁሉ ወደ ግንባር እንዲገባና ህዝቡም በደጀንነት ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ መደረጉን ጠቁመዋል።
በትላንትናው ዕለት ቀጥሎ በዋለው ውጊያ በህውሃት ታጣቂ ቡድኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑንና ቡድኑ በንጹሃን ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት፤ ንብረት ማውደምና ዘረፋ  መቀጠሉን የአካባቢው ምንጮች ጠቁመዋል።
የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤  የህወሓት ታጣቂ ኃይሎች በውጫሌና ጭፍራ አካባቢዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት፣ ከ30 በላይ ንጹሃን ሰዎችን መግደላቸውንና በርካቶች መፈናቀላቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

Read 14401 times