Saturday, 23 October 2021 12:52

ጦርነቱ በአማራና በአፋር ከፍተኛ ውድመት አድርሷል ተባለ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  • በክልሎቹ 1ሺ 436 የጤና ተቋማት ወድመዋል
   • 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል
             
            ከቀናት  በኋላ (ጥቅምት 24 ቀን 2014) አንደኛ አመቱን የሚደፍነው የህውሃት ሃይል የቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልል ከተስፋፋ ወዲህ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው፤ 1ሺ 436 የጤና ማዕከላት መውደማቸውን አለማቀፍ የሃኪሞች ቡድን ከሰሞኑ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ባሉት 8 ወራት  ከደረሰው ጉዳት በበለጠ መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም ካወጀ ወዲህ ህወሃት  የፈጸማቸው ጥቃቶችና ሰብአዊ ውድመቶች በእጅጉ የከፋ መሆኑን ሪፖርቱ ያስገነዝባል።
ቀደም ሲል  በጦርነቱ 678 ሺህ 130 ያህል ሰዎች መፈናቀላቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ባለፉት 3 ወራት ገደማ በህውሃት ወረራ ተጨማሪ 1.2 ሚሊዮን ዜጎቹ በተለይ ከአፋርና ከአማራ ክልሎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በርካታ የጅምላ ግድያዎች መፈጸማቸውን፣ የግለሰቦች ንብረት መውደማቸውንና የጤና ተቋማትና ት/ቤቶች መዘረፋቸውን በሪፖርቱ ተመልክቷል።
የህወሃት ሃይል በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት እያደረሰ  መሆኑን ያስታወቀው የአለማቀፍ የሃኪሞች ቡድን ሪፖርት፤ በተለይ ከጤና ተቋማት ጋር በተያያዘ 271 የጤና ማዕከላት፣ 1,143 ክሊኒኮች፣ 22 ሆስፒታሎች በድምሩ 1,436 የጤና ተቋማት መዘረፋቸውንና  መውደማቸውን ጠቁመዋል።
በአንጻሩ ቀደም ብሎ  ወደ ትግራይ እርዳታ የማድረሱ ተግባር ያለ ችግር በተለይ የህክምና መሳሪያዎችና አልሚ ምግቦችን ወደ ትግራይ  ያጓጓዡ 211 ተሸከርካሪዎች ሳይመለሱ መቅረታቸውን ያወሳው ሪፖርቱ፤ በዚያም ሳቢያ በአሁን ሰዓት  የህክምናና አልሚ ምግብ እርዳታ አቅርቦቱ መስተጓጎሎን ጠቁሟል። በተጨማሪም ወደ ትግራይ የሚጓጓዝ 2,500 ሜትሪክ ቶን እርዳታ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተጠባበቀ መሆኑን ሪፖርቱ አስታውቋል።
በአጠቃላይ የህክምናና አልሚ ምግቦች ድጋፍ በመስተጓጎሉ በአፋርና አማራ ክልል ያሉ ተፈናቃዮችን ጨምሮ በትግራይ የሚገኙ 92 ሺህ 835 ህፃናትና ነፍሰ ጡር ሴቶች ለእርዛት መዳረጋቸው ነው  ሪፖርቱ የጠቆመው።
በአሁን ወቅት ህውሃት በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ዋግህምራ፣ ሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎን ጨምሮ በአፋር ክልል ዞን 1 እና ዞን 2 በተባሉ 7 ግንባሮች ጦርነት መክፈቱ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
በአጠቃላይ በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልል ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለው በየአካባቢው በሚገኙ 32 ያህል መጠለያ ካምፖች ተጠልለው ይገኛሉ ተብሏል።

Read 12837 times