Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Monday, 10 September 2012 14:51

መሪዎች፣ ሞታቸውና ለቅሶአችን

Written by 
Rate this item
(10 votes)

አጼ ቴዎድሮስ በመሞታቸው ምንአልባት የቅርብ ቤተሰባቸው (እሱም ከነበረ ነው) በቀር ያለቀሰ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ ምክንያቱም ሰውየው በውጭ በእንግሊዞች፣ በውስጥ ደግሞ ለዘውድ ሲሻኮቱ በነበሩ የየአካባቢው ባላባቶች ወጥመድ ውስጥ ገብተው ስለነበር ነው፡፡ ራሳቸውም ቢሆኑ በፖለቲካና በስርቆት ምክንያት ለሚገድሏቸው ሰዎች እንዳይለቀስ በአዋጅ ከልክለው ነበር ይባላል፡፡ ሀገራችን በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት ሉዓላዊት ሆና መኖሯና አሁንም ሉዓላዊት ሀገር መሆኗ አያጠያይቅም፡፡ ይሁን እንጂ በዕድሜ የመገርጀፏን ያህል የረጋ የፖለቲካ ስርዓት አልነበራትም፤ የላትምም፡፡ በዚህ የተነሳ መሪዎች ወደ ከፍተኛው የስልጣን እርካብ የሚቆናጠጡት ወይ ገድለው ነው፤ ርህሩህ ከሆኑም የነበረውን መሪ ከርቸሌ አሽቀንጥረው ነው፡፡ ዙሩ ሲደርስ እነሱም በመጡበት መንገድ ይሰናበታሉ፡፡

ሌላው ቀርቶ ልጅ አባቱን እንደ ጭዳ በግ እያረደ ስልጣን ይይዝበት የነበረው አጋጣሚ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለአስረጅ ያህል ከ17ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ 19ኛው ክ.ዘ ድረስ ከውጫዊ ጠላቶቹ በላይ ጐንደርን እንደ ቆሎ እህል ሲያምሳት የኖረው ቤተሰባዊው የፖለቲካ ትግል ነው፡፡ በጭካኔው የተነሳ ህዝቡ “ርጉም” እያለ ይጠራው የነበረው ተክለሃይማኖት፤ አባቱን ታላቁን አድያም ሰገድ ኢያሱን ገድሎ ነው ስልጣን የያዘው፡፡

ከሁለት ዓመት የንግስና ቆይታ በኋላ እሱም ተገደለና ስልጣኑ ለዳዊት ተላለፈ፡፡

አጼ ኢዮአስም በቤተሰቡ ሴራ በራስ ሚካኤል ልዑል ፊታውራሪነት በሻሽ ታንቀው ነው የተገደሉት፡፡ የኢትዮጵያ ኪነጥበብ በእጅጉ እንዲያብብ በማድረግ ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው ዳግማዊ ኢያሱ የተገደሉትም በቤተሰባቸው አባላት በተቀመመ መርዝ ነው፡፡ የቀዳማዊ ኢያሱ ልጅ ዮሐንስም በወንድማቸው በበካፋ አማካይነት እጃቸውን ተቆርጠው ነበር፡፡ ሌሎችንም በርካታ ማስረጃዎች መደርደር ይቻላል፡፡

እንደ ቆሰለ ጅብ የመበላላት አባዜ የተጠናወተው የቤተመንግስቱ ማህበረሰብ አንዱን ገድሎ ሌላውን ሲያነግስ፣ ለሞተው በማዘን ፋንታ “የሞትንም እኛ ያለንም እኛ፤ እርጋ ብለውሃል” የሚል አዋጅ እያስነገረ ያንኑ የተለመደ መርዘኛ ሂደቱን ይቀጥላል እንጂ “መሪያችን ለምን ተገደለ?” በማን ተገደለ? ገዳዩ ለፍርድ ይቅረብ ወዘተ” የሚል ጣጣ አልነበረውም፡፡

ለዚህም ነው የመንግስታት ልጆች እየተለቀሙ “ወህኒ አምባ” በሚባለው ተሪራማ ቦታ አደገኝ ወንጀለኛ ይመስል እድሜ ልካቸውን ሲጠበቁ የሚኖሩት፡፡

ለዚህም ነው “ያለንም እኛ፤ የሞትንም እኛ፤ እርጋ” የሚል አዋጅ በማስነገር የተለመደ የገዳይ ተገዳይ ድራማቸውን በቋሚነት ይተገብሩት የነበረው፡፡ ስለዚህም ነው መሪውን ገድሎ ስልጣን መያዝ፤ በአፀፋውም ገዳዩ በገደለበት ዙፋን ላይ ጭዳ ሆኖ መቅረብ፤ ይዘወተር የነበረው፡፡

ይህ ሂደት ከባህላችን ያፈነገጠ ክስተትም አስከትሏል፡፡ ማንኛውም “ተራ ሰው” እንኳ ሲሞት በወግ በባህሉ መሰረት ተለቅሶለት ወደ ከርሰ-መቃብር ይወርዳል፡፡ አብዛኞቹ መሪዎች ግን በጭካኔ ወደ ስልጣን ስለሚወጡ ሲገደሉ ወይም ሲሞቱ አይለቀስላቸውም፡፡ በአጭር አነጋገር ስልጣንን ለማደላደል እንጂ ለለቅሶ ጊዜ የለም፡፡

በ19ኛው ክፍለዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ወደ ስልጣን ብቅ ያሉት ቋረኛው ካሳም ኢትዮጵያን ሲቀራመቷት የነበሩትን የሰፈር ባላባቶች ሁሉ ጠራርገው ማጥፋት ቀዳሚ ስራቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ገድለው እንደ ነገሱ ሁሉ ራሳቸውን ገድለው ከስልጣን ተሰናበቱ፡፡

አጼ ቴዎድሮስ በመሞታቸው ምንአልባት የቅርብ ቤተሰባቸው (እሱም ከነበረ ነው) በቀር ያለቀሰ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ ምክንያቱም ሰውየው በውጭ በእንግሊዞች፣ በውስጥ ደግሞ ለዘውድ ሲሻኮቱ በነበሩ የየአካባቢው ባላባቶች ወጥመድ ውስጥ ገብተው ስለነበር ነው፡፡

ራሳቸውም ቢሆኑ በፖለቲካና በስርቆት ምክንያት ለሚገድሏቸው ሰዎች እንዳይለቀስ በአዋጅ ከልክለው ነበር ይባላል፡፡

አንድ ቀን ታዲያ የባለቤታቸው የወ/ሮ ጥሩወርቅ አባት ደጃች ውቤ በእስር ላይ እንዳሉ ይሞታሉ፡፡ ባለቤታቸው አጥብቀው ስለወተወቷቸውም ተከልክሎ የነበረው ለቅሶ ተፈቀደ፡፡ ወገኖቹ አልቀውበት በውስጡ ያነባ የነበረው ሁሉ በደጃች ውቤ ሞት እያሳበበ ሀዘኑን ተወጣ፡፡ ይህን የተመለከተች አስለቃሽም፤

“ወይ ደጃዝማች ውቤ ሁልጊዜ ደግነት፣

ዛሬ እንኳ ለድሀው እንባ አተረፉለት” በማለት ለማልቀስ የነበረውን ችግር መግለጽዋ በተለያዩ የታሪክ መዛግብት ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

የአበሻው ጠንካራ ንጉስ አጼ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ገደሉ፡፡ እንኳን አልቃሽ ቀባሪ አልነበራቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ ገና ስማቸው ሲጠራ ይርድ፣ ይንቀጠቀጥ የነበረ ህዝብም ሆነ የባህር አሸዋ ይመስል ብዙ የነበረው ሰራዊታቸው አጠገባቸው አልነበረም፡፡ እናም ቀብራቸው በንጉሰነገስትነት ማዕረግ ሳይሆን እንደ አልባሌ ሰው በጠላታቸው ናፔር ሰራዊት መቅደላ አምባ ላይ ተፈፀመ፡፡

በምትካቸውም የላስታው ገዥ ዋግሹም ጐበዜ “አጼ ተክለጊዮርጊስ” ተብለው ነገሱ፡፡ ሶስት ዓመት ለማይሞላ ጊዜ ከገዙ በኋላ በባለቤታቸው በወይዘሮ ድንቅነሽ ወንድም በበዝብዝ ካሳ ተማረኩና ሁለት ዓይናቸው በጭካኔ ወጥቶ ከአስከፊ ስቃይ በኋላ ሞቱ፡፡ እንኳን ለመሪ የሚደረግ መሪር ለቅሶ፤ ትዝ ያሉትም አልነበረም፡፡

በዝብዝ ካሳ “አጼ ዮሐንስ አራተኛ” ተብለው ነገሱ፡፡ ለአስራ ሰባት ዓመት ያህል ኢትዮጵያን ገዙ፡፡ መጨረሻም መተማ ላይ ከማህዲስቶች (ደርቡሾች) ጋር ሲዋጉ ሞቱ፡፡ እንኳን የሚያለቅስላቸው አንገታቸው ተቆርጦ ወደ ካርቱም ሲወሰድ አጠገባቸው የቆመ ታማኝ አሽከር አልተገኘም፡፡ ያ ቢሆን ኖ መጀመሪያውኑም ለሽንፈትና አስከፊ ሞት አይዳረጉም ነበር፡፡

ከእሳቸው ቀጥሎ የሰልጣን በሮች ለሸዋው ምኒልክ ተከፈቱ፡፡ ምኒልክ “እምዬ” የሚል ቅጽል ወጥቶላቸው በአጼ ዮሐንስ መንበር ተተኩ፡፡ ከሃያ አራት ዓመት የግዛት ቆይታ በኋላ በህመም ሞቱ፡፡ ግን “እምዬ” እያሉ ሲያቆላምጧቸው የነበሩ ባለስልጣኖችና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ የንጉሡን ሞት ይፋ በማድረግ በብሔራዊ ደረጃ ቀብራቸውን መፈፀም አልፈለጉም፡፡ የዚህ ምክንያቱ “ሞታቸው ከተሰማ ዙፋኑ ይናጋል፤ አገር ይበጠበጣል” የሚል ነው፡፡

እናም የአጼ ምኒልክ ሞት ለሶስት ዓመታት ጥብቅ ምስጢር ሆኖ ቆየ እንጂ ብሔራዊ ሃዘን ተደርጐ ህዝቡ የሚወደውን መሪውን እስከወዲያኛው በእንባ ሊሸኘው አልቻለም፡፡

በአጼ ምኒሊክ ኑዛዜ መሠረት ቀጣዩ የስልጣን ተረካቢ የልጅ ልጃቸው ኢያሱ ሆኑ፡፡ ግን በደጃዝማች ተፈሪ ፖለቲካዊ ተንኮልና በራሳቸው በኢያሱም አልባሌ ምግባር ምክንያት ከስልጣናቸው በተፈሪ ሃይል ተገፍትረው ከመውደቃቸውም በላይ የት እንደ ሞቱ፣ መቃብራቸው የት እንዳለ ማወቅ አልተቻለም፡፡ ስለዚህም በመሪነት ማዕረግ ሊለቀስላቸው ይቅርና እንደ ቆሻሻ የትም ተጥለው ቀርተዋል፡፡

ቀጥለው የነገሱት የአጼ ምኒሊክ ልጅ ንግሥተ ነገስታት ዘውዲቱም ቢሆኑ ለስሙ ዙፋን ላይ ይቀመጡ እንጂ የአልጋ ወራሹን የተፈሪን ፖለቲካዊ ክንድ የመቋቋም አቅም አልነበራቸውም፡፡ ህይወታቸው ያለፈውም በተፈሪ መሰሪ ተንኮል “አነር” በተባለ ስዊድናዊ ሃኪም አማካይነት ነው ተብሎ ተወርቷል፡፡ ሆኖም ከእሳቸው በፊት ከነበሩት መሪዎች ይልቅ ንግስተ ነገሥታት ዘወዲቱ ምኒልክን ቢያንስ የቤተመንግስቱ አሽከሮችና ካህናት አልቅሰው ቀብረዋቸዋል፡፡

ቀጥሎም ባለወር ተራው ንጉሠ ነገሥት ተፈሪ መኮንን ሆኑ፡፡ ተፈሪ “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ” ተብለው ከነገሱ በኋላ ለአርባ አራት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ገዙ፡፡ ህዝቡም ረጅም ዘመን ስለገዙት፣ ሰው መሆናቸውን እስከሚረሳ ድረስ አባቱን እየተወ በስማቸው እስከመማል ደርሶ ነበር፡፡

ሆኖም ለረጅም ዘመናት ሲከማች የኖረው የበደል ጽዋ ሞላና በህዝቡ ግፊት ሰው መሆናቸው ታወቀ፡፡ ከሥልጣን ወርደው ለአንድ ዓመት ያህል በደርግ እስረኝነት ከቆዩ በኋላ ሞቱ፡፡ እንኳንስ አርባ አራት ዓመት የገዙ፤ እንኳንስ በስማቸው የተማለባቸው ሊመስሉ የት እንደ ተቀበሩ የሚያውቅ ዘመድም ሆነ የስራ ባልደረባ አልነበረም፡፡ ደማቸው ደመከልብ ሆኖ እንደ አልባሌ ሰው የትም ወድቀው ቀሩ፡፡ በወቅቱ በንጉሱ ሞት ምን አልባት ከቤተሰባቸው ውጭ በወቅቱ ያዘነ ሰው ነበር ማለት ይከብዳል፡፡

የንጉሰ ነገሥቱን ስልጣን በኃይል ገርስሶ መንበረ መንግሥቱን የተቆናጠጠው ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግም ከአስራ ሰባት ዓመታት የሞት ሽረት አገዛዝ በኋላ በሃይል ያገኘውን ስልጣን በኃይል ተነጠቀ፡፡ መሪው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምም የሚጓጉለትን ስልጣን በግድ ለቀው ወደ ዚምባብዌ መረሹ፡፡ ከስልጣን በመውረዳቸው እንኳንስ ህዝቡ እንኳንስ የፖለቲካ ባላንጣዎቻቸው የሾሙ የሸለሟቸው ግለሰቦች ሳይቀሩ በደስታ ሰከሩ እንጂ ቅር የተሰኘ አልነበረም፡፡

ከእሳቸው ቀጥለው ለሰባት ቀናት ስልጣን ላይ የቆዩት ሌተና ጄኔራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳንም የሌኒንን ሃውልት ከማስፈረስና በየቢሮው ተሰቅሎ የነበረውን የኮሎኔል መንግሥቱን ፎቶግራፎች ከማስወረድ የዘለለ ሥራ ሳይሠሩ በታጋይ መለስ ዜናዊ የሚመራው ኢህአዴግ ከስልጣን ማማቸው ላይ ገፈተራቸው፡፡ ተገፍታሪው ጀኔራል ጣሊያን ኤምባሲ መሸጉ እንጂ በወቅቱ ባለመሞታቸው ያለቀሰ አልነበረም፡፡

ከጄነራል ተስፋዬም ሆነ ከኮሎኔል መንግስቱ በፊት ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶምና ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ለአጭር ጊዜያት በየተራ ቢመሩም በበታች ሹሞቻቸው እየተረሸኑ የትም እንደ ትቢያ ተጣሉ እንጂ በክብር የመቀበር ዕድል አልተሰጣቸውም፡፡

ከደርግ ቀጥለው ለተከታታይ ሃያ አንድ ዓመታት ኢትዮጵያን በፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሯት መለስ ዜናዊ ሲሞቱ ግን የተለየ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ወጣቱም፣ አዛውንቱም፣ ባለስልጣኑም፣ ተራው ሰራተኛም፣ ጋዜጠኛውም … ብቻ ሁሉም በእንባ ተራጨ፡፡ በዚህም ዓለም ሳይደነቅ አይቀርም፡፡ እንዲህ ዓይነት ለመሪ የሚደረግ ለቅሶ የሰሜን ኮሪያ መሪዎች ሲሞቱ ብቻ በቴሌቪዥን ተመልክተናል፡፡ በአገራችን ግን እንግዳ በመሆኑ ሁሉንም ያስገረመ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በዚህ ረገድ ህዝብ አልቅሶ የቀበራቸው በቤተ መንግስት ስርዓት የተቀበሩ ብቸኛ ሰው በመሆናቸው አቶ መለስ ዕድለኛ ናቸው፡፡

ሆኖም የሚገርሙ ሁኔታዎች ታይተዋል፡ ነሐሴ 15 ቀን በጥዋት መርሃ ግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ያረዳን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከመርዶው በኋላ “ብሔር ብሔረሰቦች ሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች” የሚል መዝሙር ሲያሰማን “እንዴ! መለስ በመሞቱ ነው ብሄር ብሄረሰቦች የኢትዮጵያ ልጆች የሚሆኑት?” የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ጋብዞናል፡፡

በተረፈ መላው የሃገራችን ህዝብ እንደ ማዕበል በአንድ አቅጣጫ እንዲገነፍል ስላደረጉ መገናኛ ብዙኃን የተሳካ ተግባር አከናውነዋል፡፡ የአቶ መለስ ሞት በተነገረበት ሰሞን ብዙ ሰዎች በሃሳብ እንዲሞቱ የተደረገበት ምክንያት ግን በፍጹም ግልጽ አይደለም፡፡

ፕሬዚዳንት ግርማ፣ ጀኔራል ሳሞራ፣ አቶ አለማየሁ አቶምሳ፣ ሼህ መሃመድ አሊ አልአሙዲ፣ ወዘተ.. በወቅቱ በህይወት አለ የሚባል ሰው ጥቂት ነበር፡፡ ውሎ ሲያድር “ሞቱ” የተባሉት ሰዎች ሁሉ በህይወት መኖራቸው በቴሌቪዥን ሲታዩ ወሬውን ያመረቱት ግለሰቦች ምን ያህል እንዳረሩ እነሱ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ለምን የግለሰቦችን ሞት እንደተመኙም ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት የህዝቡን ሃዘን ከባድ ያደረገው በተለይ እንዲያ በክብር ዘብ ታጅበው ሲፈልጉ ሮጥ ሮጥ ብለው፤ በሌላ ቀን ደግሞ በመሪነት ግርማ ረጋ  ብለው፣ ሲመላለሱበት በነበረው አውሮፕላን፤ እንዲያ በከፍተኛ ባለስልጣናት አሸኛኘትና አቀባበል ሲደረግላቸው የነበሩ መሪ፤ በዚያው አየር መንገድ ከል በለበሱ ሃዘንተኞች የታጀበ አስከሬናቸው መምጣቱ ይመስለኛል፡፡

እናም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ብዙ ተባለ፡፡ አንዳንዱ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ምክንያቱ ከጋናው ፕሬዚዳንት ጋር የጨረር ጥቃት ተፈጽሞባቸው ነው፡፡ ሌላ አፍሪካዊ ፕሬዚዳንትም የጥቃቱ ሰለባ ሆነው በሞትና በህይወት መሃል ይገኛሉ” ሲል፤ ሌላው ደግሞ “የለም የዋልድባን ገዳም በመዳፈራቸው መነኮሳቱ መቋሚያቸውን ዘቅዝቀው፤ መስቀላቸውን ከዛፍ ላይ ሰቅለው መሪር ሃዘን ስላዘኑ፤ አምላክ ጸሎታቸውን ሰምቶ የሃይማኖት መሪውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀሰፋቸው” እያለ ወሬውን ሲያጋግል ሰንብቷል፡፡ ያም ሆኖ ሁለቱም ወገኖች ለወሬዎቻቸው “ይህ ነው” የሚሉት ማስረጃ የላቸውም፤ ወይም አላቀረቡም፡፡

በሃዘኑ ሰሞን ሌላ ጉዳዮችም ተስተውለዋል፡፡ ሃዘን በሰላማዊ ሰልፍ የተገለጸበትን ብዙ አካባቢ በቴሌቪዥን አስተውለናል፡፡ እንደሚገባኝ ሰልፍ ለድጋፍ ወይም ለተቃውሞ የሚደረግ መግለጫ ነው፡፡ አለዚያ የቀለጠ መፈክር እያስተጋቡ መሰለፍን ምን አመጣው? “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገዳይ /እግዚአብሔርን/ እቃወማለሁ” ማለት ነው? ወይስ “ሞታቸውን እደግፋለሁ?” ግልጽ አይደለም፡፡

ህዝቡ እንደየ ባህሉ ሃዘኑን የገለጸበት መንገድ ተገቢም ትክክልም ይመስለኛል፡፡ ድብልቅልቁ የወጣ ሰልፍ ግን ባህላችንም ልምዳችንም አይደለምና ለሃዘን መግለጫ ባናውለው ጥሩ ነበር ባይ ነኝ፡፡

ወቅቱ ለብዙ ወሬ ምቹ ስለነበር በንግዱ አካባቢም ብዙ ተወርቷል፡፡ “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፎቶ በትላልቅ ሰሌዳዎች እናሰራለን” በማለት ተገቢ ያልሆነ ወጭ እንዲወጣና ብዙው ገንዘብ ወደ ኪሳቸው እንዲገባ ያደረጉ ባለስልጣናት ቁጥር ቀላል አልነበረም እየተባለም ተወርቷል፡፡ በማስረጃ አስደግፎ የሚያቀርብ ባይገኝም፡፡

ጉዳዩ ተፈጽሞ ከሆነ ግን ትልቅ የሞራል ዝቅጠት በመሆኑ በእጅጉ ያሳፍራል፡፡

ባለ ፎቶ ቤቶችም ትንፋሻቸው እስክትወጣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፎቶ በማባዛትና ለቸርቻሪዎች በመቸብቸብ ተወጥረው ሰንብተዋል፡፡ ህዝቡ የመሪውን ፎቶግራፍ የሚገዛው ፍቅሩን ለመግለጽ ነው እንበል፡፡ ግን … የአንድን ሰው ፎቶግራፍ ያለ ባለቤቱ ፈቃድ ወይም የሚመለከተው አካል ሳይፈቅድ በአደባባይ መቸብቸብ በህግ አያስጠይቅ ይሆን?

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ሃዘናቸውን ለመግለጽ በሚኒባሶች ሆድና ጀርባ ታጭቀው “መለስ አልሞተም!” እያሉ የሚጮኹ በርካታ ሰዎችንም ተመልክተናል፡፡

“ሃዘናችንን ስንገልጽ በቦታው ተገኝታችሁ አልቀረጻችሁንም፡፡ ስናለቅስም ሆነ መፈክር ስናሰማ በቴሌቪዥን አላስተላለፋችሁልንም” ብለው የኢቴቪ ባለሙያዎችን የወረፉ ባለስልጣናትና አንዳንድ ሃዘንተኞች እንደነበሩም ሰምተን ገርሞናል፡፡ ለመሆኑ ለቅሶ ቤት የሚኬደው ለመተዛዘን ነው ለመተዛዘብ? ግልጽ አይደለም፡

በቴሌቪዥን ሲተላለፉ ከነበሩት የሃዘን መግለጫዎች አንዳንዶቹ በድፍረትም ሆነ በስህተት ጥሩ ያልሆነ መልዕክት ያዘሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ጐዳና ተዳዳሪዎች ባካሄዱት የሃዘን መግለጫ ስነ ስርዓት ላይ “አባታችን ስላሉኮ ነው ጐዳና የምንተዳደረው” ብሎ ያለቅስ የነበረን ወጣት በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን አይተናል፡፡

በውጭ ያሉ አንዳንድ ወገኖችም በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚያስተላልፉትን መልእክትም በመገረም እያየነው ሰነበትን፡፡ አንዳንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት በደስታ ሲገልጽ፣ ሌላው ደግሞ አገር ቤት እንዳለው ሁሉ መሪር ሃዘኑን አስተጋብቷል፡፡ በእኔ እምነት ሞትን ለሰው ልጆች ሁሉ የሚመኙ ሰዎች ጤነኛ ናቸው አልልም፡፡ ሃሳብን በሃሳብ መፋለምና ማሸነፍ ሌላ፤ የሰውን አካል ማሸነፍ ሌላ፡

“ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚተካቸው ማን ይሆናል?” የሚለውም ሌላው ዐቢይ አጀንዳ ነበር፡፡ በመሰረቱ ይህ ጉዳይ ሁሉንም ወገን የሚመለከት ስለሆነ አወያይነቱ ተገቢ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በፓርቲውም ሆነ በመንግስት መሪነት ብዙ ጊዜ ስለቆዩ “እሳቸው ከሌሉ ሃገሪቱም የሚመሯቸው ፓርቲዎችም (ኢህአዴግና ህወሃት) ላይኖሩ ይችላሉ” የሚለው  ስጋት በአንድ በኩል ትክክል ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ሃያ አንድ አመታት ሁሉ አቶ መለስ የህወሃትንም ሆነ የኢህአዴግን መሪነት ለሌላ ማስተላለፍ አልከጀሉምና ነው፡፡

ይህ ደግሞ አንድም በፓርቲዎች ውስጥ “ለዚህ ኃላፊነት የሚበቃ ሰው የለም” ብለው ያምኑ ነበር፤ ወይም ለስልጣናቸው በእጅጉ ይጠነቀቁለት ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ ለነገሩ ዜና ዕረፍታቸው ከተነገረ በኋላ በፓርቲው ታላላቅ ባለሥልጣናት ሲነገርላቸው የነበረው ገድል፤ ከእሳቸው በቀር በፓርቲው ውስጥ ምንም ዓይነት ድርሻ የነበረው ሰው እንደሌለ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

አንድን ሰው እንከን - አልባ አድርጐ የሳለው የዚህ ዓይነቱ እጅግ የተጋነነ  አገላለጽ፣ ፓርቲውን ከጥርጣሬ ላይ ቢጥለው ላያስደንቅ ይችላል፡፡ ሁሉም ነገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ የሚያልቅ፣ የሚተነተንና የሚተገበር ከነበረ ንጉሠ ነገስቱን ተክተዋቸው ነበር ማለት ነው፡፡ እግረ መንገዱንም ፓርቲው የአንድ ሰው የግል ሃብት፣ አባላቱም ትዕዛዝ ፈጻሚዎች እንጂ ረብ ያለው ድርሻ አልነበራቸውም ቢባል ስህተት አይመስለኝም፡፡

ሃገሪቱ በአንድ ሰው ሳይሆን በህግ የበላይነት የምትመራ ከነበረ፣ መከላከያውም ሆነ ፖሊሱና ደህንነቱ ለህገ መንግስቱ ታማኞች ከሆኑ ቀጣዩ የሃገራችን ዕጣ የሚያሳስብ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በህገ መንግስቱ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ምክትሉ የእሱን ሥራ ተክቶ የመሥራት ኃላፊነት አለውና ነው፡፡

ትልቁ ችግር ሊሆን የሚችለው በነባር እና ከግንቦት ሃያ በኋላ በተቀላቀሉ ታጋዮች፤ እንዲሁም በመንደርተኝነት መሳሳብ ሲመጣ ነው፡፡

ይህ እጅግ አደገኛ ጉዳይ ነው ባይ ነኝ፡፡ ሃገሪቱንም ሆነ ህዝቡን የሚጐዳው፤ ፓርቲው ከላይ በጠቀስናቸውና በመሰል ጉዳዮች ክፍተት ሲፈጥር ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ፓርቲው በጥቃቅን ሰበብ አስባቦች ካልተዳከመና ውስጣዊ ጥንካሬውን አጽንቶ ከቀጠለ ስጋታችን ሁሉ ስጋት ሆኖ ይቀራል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘውም ሆነ ሆኖለት ማየት የሚፈልገውም ይህን ብቻ ይመስለኛል፡፡ ይህ ከሆነ እንባችን በጉንጫችን ላይ ብቻ ወርዶ የሚቀር ሳይሆን እንደ ራሄል እንባ ከፈጣሪ ፊት ደረሰ ማለት ነው፡፡

 

 

 

Read 6722 times Last modified on Monday, 10 September 2012 14:57

Latest from