Monday, 10 September 2012 14:43

ቶልስቶይ በፑሽኪን አዳራሽ

Written by  መልካሙ ተክሌ እና ፈርሃ ኢብራሂም
Rate this item
(0 votes)

እውቁ ሩሲያዊ ደራሲ ሌቭ ኒኮላየቪች ቶልስቶይ ከሞተ ከመቶ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ አሁንም ድረስ ግን መላው ዓለም ያነበዋል፡፡ በእኛ ሃገር እንኳን የተለያዩ ሥራዎቹ ከበፊት ጊዜ ጀምረው ተተርጉመው ለሕዝብ ደርሰዋል፡፡ አሁን በቅርቡ ከሩስያንኛ ወደ አማርኛ የተተረጎመው “አና ካሬኒና” ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ ታትሟል፡፡ ይኼ ታላቅ ደራሲ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነገ እሁድ ከተወለደ ልክ 184ኛ ዓመቱ ነው፡፡ ለ82 ዓመታት በህይወት የኖረው ቶልስቶይ ሕይወቱ ካለፈ ዘንድሮ 102ኛ ዓመቱን ይይዛል፡፡

የሥነ ፅሑፍ ጀግኖቻቸውን መዘከሩን የሚያውቁበት ሩስያውያን ቶልስቶይንም በተለያየ አጋጣሚ በየጊዜው ይዘክሩታል፡፡ ባለፈው ሰኞ ምሽትም አዲስ አበባ ፒያሳ የሚገኘው የሩስያ ሳይንስና ባህል ማዕከል ፑሽኪን አዳራሽ የዚህን ስመጥር ደራሲ ልደት ዘክሮ ነበር፡፡ መዘከሩን ያቀረበው በሩስያ ከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው ፊልም ማስተር ብርሃኑ ሽብሩ ነው፡፡ ዝግጅቱ የተጀመረው በቅርቡ ሕይወታቸው ላለፈው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለሥ ዜናዊ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የሕሊና ፀሎት በማድረግ ነበር፡፡ ፓትርያርኩ ባለፈው የካቲት በዚሁ አዳራሽ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የምትጠቀምባቸውን የድንግል ማርያም ስዕሎች አውደርዕይ መክፈታቸው ይታወቃል፡፡

ብርሃኑ ዝግጅቱን የጀመረው ስለ ቶልስቶይ ሁለገብ ባለሙያነት ያስደነቀውን በመናገር ነበር፡፡ በረዥም ልቦለድ ፀሃፊነቱ የሚታወቀው ቶልስቶይ ገበሬ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ ፀሐፌ ተውኔት፣ ፈላስፋ፣ ወታደር፣ መምህር ነበር፡፡ የሃብታም ልጅ ቢሆንም ከረዥም ልቦለድ ፀሃፊነቱ ከፍተኛ ገንዘብ በማግኘት በዓሉም ሃብታም መሆን የቻለ ደራሲ ነው፡፡ እውቁ ደራሲ በአንድ ወቅት ቁማርተኛም እንደነበር የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡

ያለውን ገንዘብ ሁሉ ፓሪስ ላይ በቁማር አስበልቶ ወደ እናት ሩስያ የተመለሰው ቶልስቶይ፤ የግለ ታሪኩ አንድ ክፍል የሆነውን “ወጣትነት”ን በማሳተም እንደገና ሊያንሰራራ ችሏል፡፡ ደራሲው በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቹ እርዳታ በማሰባሰብ በጐ ተግባሩም ይታወቃል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የዶክተር ልጅ የሆነችውን ሶፍያ አንድሬየቭናን በማግባት የትዳር ሕይወቱን የጀመረውና 13 ልጆችን ያፈራው - ሦስቱ በጨቅላነታቸው ቢሞቱም፡፡

ሶፍያ አንድሬየቭና የትዳር አጋሩ ከሆነች በኋላ የሥራ አጋሩም ሆና በማገዝ ከስኬት ወደ ስኬት እንዲወነጨፍ ብርታት ሆናዋለች፡፡ የልቦለድ ሥራዎቹን አንብባ በመተየብ አስተያየቶችን ትሰጠው እንደነበር ይነገርለታል፡የትዳር አጋሩ በዚህም ሳትወሰን የሚለብሳቸውን አዳዲስ የሚያማምሩ ሸሚዞችንም ትሰፋለት ነበር፡፡ እናቱን በሁለት ዓመቱ፣ አባቱን በዘጠኝ ዓመቱ በሞት ተነጥቆ ከአክስቱ ጋር ላደገው ቶልስቶይ ይሄ ትልቅ እገዛና የቤተሰባዊ ፍቅር መገለጫ ነበር፡፡ ሆኖም የሶፍያ እና የቶልስቶይ ትዳር ከእንቅፋቶች አላመለጠም፤ የመፍረስ አደጋም አንዣቦበት ነበር፡፡

የሩስያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ የነበረው ቶልስቶይ፤ ከሃይማኖቱ የሚፈልገውን መልስ በማጣቱ ኦርቶዶክስን ጨምሮ የክርስትያን አብያተ ክርስትያናትን በሙሉ ሙሰኞች ብሏቸዋል፡፡ በዚህም ሳያበቃ የራሱን ሃይማኖት በማደራጀት ተከታዮች አፍርቷል፡ የቶልስቶይን ድርጊት አጥብቃ ያወገዘችው ቤተክህነት ብትሆንም የመንግስት የሚስጥር ፖሊሶችም (በአሁኑ አጠራር “ደህንነቶች”) ይከታተሉት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የቶልስቶይ ሰላማዊ ተቃውሞ በመጀመርያ በሕንዱ የነፃነት ታጋይ ማህተማ ጋንዲ፣ ቀጥሎም በአሜሪካው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታናሹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ላይ ተፅእኖ እንዳሳደረ ይነገርለታል፡፡ “መንግስተ ሰማያት በውስጣችሁ ናት” የሚለው የቶልስቶይ ሥራ በሃይማኖት ላይ ያለውን ተቃውሞ ለመግለፅ የፃፈውም ይመስላል፡፡

ትምህርትና ሥራዎች

ከከበርቴ ቤተሰብ የተገኘው እጓለማውታው ቶልስቶይ፤ ተቀማጥሎ ያደገና ተንደላቆ የኖረም ነበር፡፡ ትምህርቱን የግል አስተማሪ ተቀጥሮለት ከተከታተለ በኋላ በ16 ዓመቱ የምሥራቃውያንን ቋንቋ ለማጥናት ወደ ካዛን ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ ነገር ግን ሳይስማማው ስለቀረ ወደ ሕግ ትምህርት ገባ፡፡ አሁንም ግን ስላልተመቸው ተወው፡፡ የሃብታም ከበርቴዎች ልጅ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው ከድሃ ገበሬዎች ልጆች ጋር በመጫወት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ከታላቅ ወንድሙ ጋር ወደ ካውካሰስ በመንቀሳቀስ የሩስያን ጦር በመቀላቀል ወታደር ሆነ፡፡ ምክትል መቶ አለቃ ሆኖ በክሪሚያ ጦርነትም ተሳትፏል፡፡

በ24 ዓመቱ የሥነ ፅሁፍ ህይወቱን እንጀመረ የገለፀው ብርሃኑ ሽብሩ፤ ቶልስቶይ አንዳንድ እንግዳ ነገሮችን ይናገር እንደነበር ሲጠቁም “እኔ ስፈጠር በውስጤ የሚሰማኝ አንድ ነገር አለ፡፡ ለየት ያልኩኝ ነኝ፡፡ አሁን ደግሞ አርጅቻለሁ፡፡ እድገቴንም ጨርሻለሁ” ማለቱን ተናግሯል፡፡ እንደ ረዥም ልቦለድ እና ኖቬላ ሥራዎቹ ሁሉ ዓለም ያጨበጨበላቸው ግጥሞች የነበሩት ቶልስቶይ፤ ባንድ ወቅት እነዚሁን ግጥሞቹን ሰብስቦ “ምን አይነቱ የማሳፍር ጉድ ነኝ” በማለት አቃጥሎዋቸዋል፡፡ የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ ደግሞ፤ የተንደላቀቀ የከተማ ኑሮ እንደሰለቸው ለሶፍያ በመግለፅ ወደ ገጠር መሄዱንም ጠቅሷል፡፡ አንድ የሩሲያ የወቅቱ አንጋፋ ደራሲ የወጣቱን ቶልስቶይ የጥበብ ሥራ ጅማሮ አይቶ “ይኼ ወይን ለጋ ነው፤ ግን ሲያፈራና ሲበሥል አማልክትና ሰውን ሁሉ ያጠግባል” ማለቱን ያወሳው ባለሙያው፤ ቶልስቶይ ከዚያ በኋላ የገነኑ እና እስካሁንም በተወዳጅነት የሚነበቡ ሥራዎችን እንዳበረከተ ዋና ዋና ሥራዎቹን በመዘርዘር ገልጿል፡፡

ረዥም ልቦለድ እና ኖቬላ

ቮይና ኢ ሚር (ጦርነትና ሰላም) - የቪክቶር ኡጐን “ምንዱባን” በአድናቆት ማንበቡ በዚህ መጽሐፍ ላይ ተፅእኖ አሳድሮበታል ይባላል

“አና ካሬኒና” ከ”ጦርነትና ሰላም” ይበልጥ እውነተኛ ረዥም ልቦለዴ ነው ማለቱ ይነገርለታል

“ሃጂ ሙራድ”

“የኢቫን ኢሊች ሞት”

“ልጅነት”፣ የግለ ታሪክ ረዥም ልቦለድ

“ወጣትነት”፣ የግለ ታሪክ ረዥም ልቦለድ

ከነዚህም ሌላ ግጥሞች፣ ተውኔቶችና ሌሎች አስተዋፅኦዎችም ነበሩት፡፡

ፀሐፍት ስለ ቶልስቶይ

የቶልስቶይ የልጅ፣ ልጅ፣ ልጅ፣ ልጅ የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የባህል አማካሪ ናቸው፡፡

ይሁንም እንጂ የቅምአያታቸው ሥራዎች በአግባቡ በሕዝቡና በመንግስት በመጠበቃቸው ከሌላው ሰው እኩል “ተጋፍተው” እንደሚጎበኙት ነው ብርሃኑ የሩስያ ቆይታውን ትዝታ በቁጭት ለታዳሚው የገለፀው፡፡

እኛስ የሥነፅሑፍ እሴቶቻችንን እና ጀግኖቻችንን መቼ ነው የምንንከባከብና ሥራዎቻቸውን ለቀጣይ የልጅ፣ ልጅ ልጆች የምናቆየው? እናንተ ወጣት ገጣሚያንስ ስራዎቻችሁ እንዴት ነው የሚጠበቁት በማለት የቶልስቶይ ልደትን አስመልክቶ ያቀረበውን ምልከታ አጠቃሏል፡፡የባህል አማካሪውም ሆኑ የቶልስቶይን ስራዎች የተመለከቱለት ፀሃፍት ግን እንደ ብርሃኑ አልተቆጩም፡፡ ለምሳሌ በወቅቱ የነበረው ታዋቂ የአገሩ ደራሲ ዶስትየቭስኪ “በሕይወት ካሉት ታላቁ ደራሲ” ሲል አድንቆታል፡፡ ሌላው የወቅቱ ሩስያዊ ደራሲ አንቶን ቼሆቭ ደግሞ “ሥነ ፅሑፍ አንድ ቶልስቶይን ሲኖራት ፀሐፊ መሆን ቀላል እና ምቹ ነው” ብሏል፡፡

“ቮይና ኢ ሚርን” ተተርጉሞለት ካነበበ በኋላ ፈረንሳዊው ታዋቂ ደራሲ ጉስታቭ ፍላቨርት “ድንቅ ከያኒ ድንቅ ሳይኮሎጂስቶች” ብሎታል፡፡ አየርላንዳዊው ደራሲ ጀምስ ጆይስም “ፍዝ ሆኖ አያውቅም፡፡ የማይረባ ሆኖ አያውቅም፡፡ ደክሞት አያውቅም …” በማለት ገልፆታል፡ ቨርጂኒያ ዎልፍም ቶልስቶይ የምንጊዜም ታላቅ ፀሐፊ መሆኑን አውጃለች፡፡

አሟሟት

የአና ካሬኒና ልቦለድ ዋና ገፀ ባህርይ ባቡር ጣቢያ ውስጥ ነው የምትሞተው፡፡ በኒሞኒያ በሽታ ሕይወቱ በ82 ዓመቱ ያለፈው ሊዮ ቶልስቶይም የሞተው አስታፓቮ በተባለ ከመኖርያ ቤቱ አቅራቢያ በሚገኝ ባቡር ጣቢያ ነበር፡፡

ከቤት ከመውጣቱ በርካታ ቀናት በፊትም ለባለቤቱ ሶፍያ የገዛ አሟሟቱን አስመልክቶ ይፅፍላትና ይነግራት ነበር፡፡ ፖሊስ በቶልስቶይ ቀብር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ብዛት ገድቦ የነበረ ቢሆንም በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች መቃብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በእርግጥ “የሆነ መኮንን ሞቷል” ከማለት በስተቀር ስለቶልስቶይ የሚያወቁት ብዙ እንዳልነበረ ይነገራል፡፡

 

 

 

Read 1943 times Last modified on Monday, 10 September 2012 14:47