Print this page
Saturday, 16 October 2021 00:00

በህወኃት ወረራ የተፈናቀሉ የሰቆጣ ነዋሪዎች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

  7ሺ የሚደርሱ ተፈናቃዮች በአንድ ኮሌጅ ውስጥ ይገኛሉ
   አንድ ክፍል ውስጥ 60 ተፈናቃዮች ያድራሉ
    በመንገድ የወለዱ፣ የሞቱና ከመኪና ወድቀው የተጎዱ ስደተኞችም አሉ
                 
               ከአማራ ክልል የዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ ተፈናቅለው በአብነት ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ከ7ሺ በላይ ስደተኞች እጅግ በከፋ ችግርና ረሃብ ውስጥ እንደሚገኙና ለህይወታቸው በሚያሰጋ የጤና ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ገለፁ። መንግስትና ህዝብ ይድረስልን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የሰቆጣ ከተማ ከጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ጀምሮ በህውሃት ታጣቂ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መግባቱን የተናገሩት እነዚሁ ተፈናቃዮች፤ ከዚያች ምሽት ጀምሮ የመኖሪያ ቀዬአቸውን ጥለው በእግርና በተለያዩ የመጓጓዣ መንገዶች በመጠቀም አብነት ወረዳ መድረሳቸውን ገልጸዋል። የወረዳው ህዝብና አስተዳደር ተፈናቃዮቹን ተቀብሎ በወረዳው ውስጥ በሚገኝ የግብርናና ቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ እንዲያርፉ ያደረጋቸው ቢሆንም፤ በቂ የምግብና የሕክምና አገልግሎት እያኘን አይደለም ብለዋል። በመጠለያው ውስጥ ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል አብዛኛዎቹ አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ህጻናት በመሆናቸውና በቂ ምግብና ህክምና  እያገኙ ባለመሆኑ ለከፋ የጤና ችግር ረሃብና ሞት  ይጋለጣሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ተፈናቃዮቹ ተወልደው ያደጉበትን ቀዬ ጥለው ለስደት የተዳረጉበትን አጋጣሚ የሚያስታውሱት እጅግ በበዛ ሃዘንና ትካዜ ነው። ዕለቱ የበዓል ዋዜማ ምሽት አገራችን አሮጌውን ዘመን አሰናብታ አዲሱን የምትቀበልበት… ህዝቦቿ “የጎመን ምንቸት ውጣ የገንፎ ምንቸት ግባ” ብለው ችቦ የሚለኩሱበት፣ የ2014 አዲስ ዓመት  ምሽት።
በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ 02 ቀበሌ ውስጥ የሚኖሩት የነቴዋ ድረስ ታረቀኝ መንደር ነዋሪዎችም አዲሱን ዓመት በደስታ ለመቀበል እየተዘጋጁ ነው። አመሻሽ ላይ ነዋሪው ችቦ ለመለኮስ እያዘጋጀ ባለበት ወቅት ድንገት መንደሯ ትርምስምሷ ወጣ። የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች ከተማዋን ተቆጣጥረው  በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ማድረስ  መጀመራቸው ከዳር እዳር ተሰማ። አብዛኛው የመንደሯ ነዋሪ ነፍስያውን ለማትረፍ ቤቱን እየጣለ መሸሽ ጀመረ። እናቶች ህፃናት ልጆቻቸውን እየታቀፉና እያዘሉ፣ አባቶች እንኮኮ እያሉ፣በጨለማ እየወደቁ እየተነሱ ሽሽታቸወን ቀጠሉ። ይህን የሽሽት ጊዜ ቴዎድሮስ እንዲህ ያስታውሰዋል፡- “ሰዓቱ ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ  ይሆናል፤ ድንገት ሰፈራችን ጩኸትና ሩጫ ሲበዛ ወደ ውጪ ብቅ ብዬ ሁኔታውን ለማየት ሞከርኩ። ሁሉም ይጮሃል ይራወጣል። ገቡ ገቡ ይባባላል። ወደ ቤቴ ተመለስኩና የአራት ዓመት ልጄን  እንኮኮ ብዬ፣ ትንሿን ለእናቷ አሳዝዬ ከቤት ወጣሁ። ወዴት እንደምሄድ አላውቅም፤ ከቤት ስወጣ ምንም ነገር አልያዝኩም። ደመነፍሴ ወደመራኝ ቦታ ስንጓዝ አድረን ሌሊቱ ሊነጋ ሲቀርብ፣ አንድ የጥንት መኪና አገኘን- መኪናው “ህፃናትና ሴቶችን ብቻ ነው የምጭነው” በማለቱ ልጆቼንና ባለቤቴን አሳፍሬ፣ እኔ ከሌሎች ስደተኞች ጋር በእግራችን ጉዞአችንን ቀጠልን. 30 ኪሎ ሜትር ገደማ እንደተጓዝን ሌላ መኪና አግኝተን ለምነን በመሳፈር አብነት ከተማ ደረስን። እዚህ ከደረስን በኋላ ልጆቼንና ባለቤቴን በመጠለያ ካምፕ ውስጥ አገኘኋቸው። አሁን በመጠለያው ውስጥ አለን- ከሞቀ ቤትና ንብረታችን ተፈናቅለን የሰው እጅ እያየን እንድንኖር ተፈርዶብናል ለሰው የምንተርፍ አርሶአደሮች የሰው ጥገኛ ሆነን፣ ቁራሽ ልመና ላይ እንገኛን።
“በመጠለያው ውስጥ እንደኛ ከየቤታቸው ተፈናቅለው የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች  ስላሉ እጅግ በከፋ ረሃብና ስቃይ ውስጥ ነን። በአንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ሆነን ስለምናድርም ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጥን ነው። መንግስት በሽፍቶች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ወስዶ ወደ ቀዬአችን እንዲመልሰን፣ እስከዚያ ድረስ በረሃብ ከመሞት እንዲታደገን ነው የምንለምነው” ብለዋል አቶ ቴዎድሮስ።
የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች የሰቆጣ ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ የመኖሪያ ቀዬአቸውን ትተው ለስደት የተዳረጉ ሌላው ተፈናቃይ አቶ የኔነህ ስመኝ፣ ሁኔታውን እጅግ አስከፊ፣ ተስፋ አስቆራጭና አሳዛኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ የኔነህ ከሌሎች ተፈናቃይ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን በ2014 አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለስደት ሲወጣ፣ ደካማ እናትና አባቱን እዛው   ቤቱ ውስጥ እንዳሉ ትቶአቸው ነበር። የህውሃት የቅጣት በትር በተለይ በወጣች ላይ የከፋ መሆኑን የተገነዘቡት ወላጆችም፤ እሱ ቀዬውን ትቶ እንዲሰደድ ገፋፉት። የኔነህ በሰቆጣ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የገበሬ ማህበራት ውስጥ በሙያው በማገልገሉ አካባቢዎችን ለማወቅ እድል ነበረው። በእነዚህ የስደት ቀናት ውስጥ ያያቸው ዘግናኝና አሳዛኝ ሁኔታዎች እድሜውን በሙሉ ከህሊናው የሚፋቁ እንዳልሆኑ ይገልጻል።
እጅግ ከአቅም በላይ በሲኖትራክ መኪና የተጫኑ ስደተኞች መካከል በግድያው ሳቢያ  የሞቱ ህጻናን፣ በመንገድ ላይ ምጣቸው መጥቶ ጥላ ስር የተገላገሉ ነፍሰጡር ሴቶችን፣ ልጆቻቸውን በጨርቅ አዝለው ከሞት ሊታደጉ የሚውተረተሩ አባቶችን እና ሌሎች በርካታ አሳዛኝ ሁኔታዎችን  አይቷል። ከብዙ ድካምና መንገላታት በኋላ ከሰቆጣ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አብነት ወረዳ ደረሱ። በወረዳው በሚገኘው የግብርናና ቴክኒክ ኮሌጅ እንደሱ ከየቀያቸው ተፈናቅለው ከተሰባሰቡና በሺዎች ከሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ጋር አብረው መዋል ማደሩን ቀጠለ።
በዚያ መጠለሊያ ጣቢያ ውስጥ ያለው የተፈናቃይ አያያዝ ግን ለጤና እጅግ አሳሳቢና ትኩረትን የሚሻ እንደሆነ ይናገራል። በአንዲት አራት በአራት በማትሆን ክፍል ውስጥ ከ60 በላይ ሰዎች እንዲውሉና እንዲያድሩ ማድረጉ፣ ተፈናቃዩን ለከፋ የጤና ችግር ማጋለጥ ነው። የሚለው የኔነህ፤ በአንድ ክፍል ውስጥ ወንድና ሴት ተፈናቃዮችን በጋራ ማሳደሩ ደግሞ ለሌላ የከፋ ሁኔታ የሚያጋልጥ እጅግ አደገኛ ጉዳይ ነው ብሏል። ይህንኑ የየኔነህን ስጋት የሚጋሩ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ  የሚገኙ ተፈናቃዮች በርካታ ናቸው። ወረዳው በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ወደሚገኙ ቦታዎችና ተቋማት በመውሰድ አለያም ጊዜያዊ ማረፊያ በማዘጋጀት፣ ህዝቡን በመተፋፈግ ሳቢያ ከሚመጡ አደገኛ የጤና ችግሮች ሊታደገው ይገባል ብለዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን የኮሮና ወረርሽኝ ቢቀሰቀስ ሊከተል የሚችለው አደጋ ሊታሰብበት ይገባል ብሏል። የኔነህ ከቤቱ ጥሏቸው የወጣው ወላጆቹ በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ አለመቻሉንና ይህም እጅግ እያሳሰበው መሆኑን ተናግሯል። የአንድ አመት ከአራት ወር ህፃን ልጇን ይዛ ከቤቷ በመውጣት በስደት አብነት ወረዳ የምትገኘው ፀሐይ ታያቸው በበኩሏ፤ “መጠለያ ካምፑ ከልጆች ጋር ለመቆየት የማይቻልበት አስቸጋሪ ቦታ መሆኑን  ጠቁማ፤ ህይወታችን ተርፎ እዚህ መድረስ በመቻላችን ግን ዕድለኞች ነን ። ስንቶቹ በየሜዳው ቀርተው የለ ትላለች። በመጠለያ ካምፑ ውስጥ ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ ህይወትን ለማቆየት እንኳን የማይበቃና እጅግ አነስተኛ ነው በተለይ የህፃናት ምግብና የንጽህና፤ መጠበቂያ በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ ለከፍተኛ ጭንቀት ዳርጎናል” ብላለች።
የሰቆጣ ከተማ ከንቲባው አቶ አሸብር ግርማን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፣ በእብነት ወረዳ ቁጥራቸው ከ7ሺ የሚበልጡ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህን ተፈናቃዮች መመዝገብና ማደራጀቱ ጊዜ በመውሰዱ ሳቢያ ተገቢው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በወቅቱ ሳይደርሳቸው ዘግይቷል ብለዋል።
ይህንን ችግር ለማስወገድ ቀን ከሌት በመስራት፣ የምዝገባና የማደራጀቱን ስራ ሰርተው ያጠናቀቁ በመሆኑ የእርዳታ  አቅርቦት ስራው ከትናንት ጀምሮ ቀጥሏል ብለዋል። ይህንን የከንቲባውን ምላሽ ተፈናቃዮቹ አይቀበሉትም። እርዳታና ድጋፍ የሚደረገው በትውውቅና በዝምድና ነው። የስራ ኃላፊዎች መኪናዎችን ወደ ሰቆጣ በመላክ ቤተሰቦቻቸውን እያስመጡና በምቾት እንዲኖሩ እያደረጓቸው ነው-ይላሉ
ለእኛ በመንግስትና በበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚደርሰንን የእርዳታ ቁሳቁስ እንኳን በአግባቡ እንዲደርሰን እያደረጉ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ። ይህንን የተፈናቃዮቹን ወቀሳ ከንቲባው አቶ አሸብር፤ ከእውነት የራቀና የተሳሳተ ወቀሳ ነው ሲሉ ይቃወሙታል።
በእርዳታ ስርጭቱ ወቅት አንዳንድ ያልተገቡ ድርጊቶች ተፈጽመዋል። እነዚህን ድርጊቶች  እያረምንና እያስተካከልን የመጣልንን የእርዳታ ምግብና ቁሳቁስ ያለአንዳች አድልዎ ለተፈናቃዮቹ እያከፋፈልን ነው፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቅሬታቸውን በተጨባጭ ማስረጃ ቢያስደግፉልን በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ያመቸናል ብለዋል።
በቀጣይነት በእርዳታ አሰጣጡም ሆነ በተፈናቃዮቹ መጠለያ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ቀን ከሌት እየሰራን ነው ብለዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ህውሃት ታጣቂ ሃይሎች አካባቢውን ተቆጣጥረው በፈፀሙት ጥቃት በርካቶች ለሞትና ለስደት መዳረጋቸውና አካባቢው አሁንም በህውሃት ሃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ይታወቃል።Read 8847 times