Print this page
Saturday, 16 October 2021 00:00

መንግስት ዘር ተኮር ጥቃቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ= እንዲያስቆም ፓርቲዎችና የሠብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥሪ አቀረቡ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በወለጋ የተገደሉት አስክሬን ማንሳት አልተቻለም
                               
      በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ፣ሀሮ፣ባጊጭ እና ከረሙ ቀበሌዎች ከመስከረም 2014 ጀምሮ ባሉ ተከታታይ ቀናት በሸኔ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት እየተፈፀመ መሆኑን፣ በዚህም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸውንና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በከፋ ሁኔታ መባባሳቸውን ኢሠመጉ ያስታወቀ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የአቋም መግለጫ ያወጡት ኢዜማና አብን በበኩላቸው፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የክልሉ መንግስት በበኩሉ 15 ሰዎች በዚህ ጥቃት መገደላቸውን አስታውቋል።
መስከረም 26 ቀን 2014 በከረሙ አካባቢ የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ሃይል በግዳጅ ምንክንያት በአካባቢው በመሄዱ ከመስከረም 30 ቀን 2014 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት የሸኔ ታጣቂዎች በሃሮ  ቀበሌ ተኩስ በመክፈት የአማራ ብሔር ተወላጆችን እንደገደሉ፣የአካል ጉዳት እንዳደረሱና ንብረት እንዳወደሙ ከጥቃቱ ሠለባዎች መረጃ ማሰባሰቡን የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አመልክቷል፡፡
እስከ ሃሙስ ጥቅምት 4 ቀን 2014 ድረስ ታጣቂዎች በአካባቢው በመኖራቸው የሟቾችን አስክሬን ማንሳት እንዳልተቻለ፤ ጥቃቱን የሸሹ ሴቶችና አቅመ ደካሞች እንዲሁም ህጻናት በየጫካው ተሸሽገው እንደሚገኙና ለጥቃት ተጋልጠው እንዳሉ እንዲሁም በምግብ እጦት እየተሰቃዩ መሆኑን ኢሠመጉ በመግለጫው አስገንዝቧል፡፡
የሸኔ ታጣቂዎች በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ አጠቃላይ  ነዋሪዎች የደህንነት ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን፣በአካባቢው የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ ኢሠመጉ አመልክቷል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ይህ ጥቃት ከመፈፀሙ አስቀድሞ፣ “የደህንነት ስጋት አለብን፤ በአስቸኳይ ለሚመለከተው አካል አሳውቁልን” የሚል ጥቆማ ለኢሰመጉ አድርሠው እንደነበረ ተቋሙም መልዕክታቸውን ተቀብሎ የሚመለከታቸው አካላት እርምጃ እንዲወስዱ የመወትወት ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቋል፡፡
በዚህም ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣በሠላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ክፍል እና ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሁኔታውን አሳውቆ ጉዳዩን እንደሚከታተሉት ገልጸውለት እንደነበር ያወሳው ኢሰመጉ፤  በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደርም የችግሩን አሳሳቢነት በመግለፅ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ መረጃዎችን ማጋራቱን አመልክቷል;፡፡
መንግስት አሁንም አፋጣኝ እርምጃ ወስዶ በስጋት ውስጥ ያሉ ዜጎችን ከጥቃት እንዲታደግና የአካባቢውን ደህንነት አስተማማኝነት እንዲያረጋግጥ፣ የደህንነት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ አስቀድሞ የደህንነት ተግባራትን ማከናወን ላይ መንግስት እንዲያተኩር እንዲሁም አጥፊዎችን አጣርቶ ለህግ እንዲያቀርብ ኢሠመጉ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡
በከረሙ የተፈፀመውን ብሔር ተኮር ጥቃት በፅኑ ያወገዙት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ብቅናቄ (አብን)፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት በማንኛውም መልኩ የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት በተደጋጋሚ የሚፈፀሙ መሰል ጥቃቶችን ከመሰረቱ በማድረቅ ለዜጎች ደህነነት ዘላቂ ዋስትና ሊሰጥ እንደሚገባው ፓርቲዎቹ አሳስበዋል- በመግለጫቸው፡፡
በምስራቅ ወለጋ ከረሙ ወረዳ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ መግለጫ የሰጠው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፤ በዘር ተኮር ጥቃቱ 15 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
በአሸባሪነት የተፈረጀው የሸኔ ታጣቂዎች ቡድን በአካባቢው ነዋሪ በሆኑ አራት የአማራ ብሄር ተወላጆችን ሲገድሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን “የአማራ ፅንፈኛ  ሽፍቶች” ያላቸው ቡድኖች 11 የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን መግደላቸውን አመልክቷል።
በግድያው ላይ ተሳታፊ የሆኑ 3 የሸኔ አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱ ቀሪዎቹን አጥፊዎች ላይ በቁጥጥር ስር በዋማል የተጠናከረ አሰሳ መቀጠሉን የክልሉ ኮሚሽን በመግለጫው አመልክቷል። አካባቢው የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንም ኮሚሽኑ ጠቁመዋል።


Read 924 times
Administrator

Latest from Administrator