Saturday, 16 October 2021 00:00

ተመድ ተቋማዊ አድሏዊነት መፈፀሙን ያጋለጡ ሁለት የድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች ከስራቸው ታገዱ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች፣ ለህወኃት ታጣቂዎች እንደሚያደሉና በሳውዲ በእስር ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ሩዋንዳ ለማስገባት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ያጋለጡ ሁለት የድርጅቱ ኃላፊዎች ከስራቸው ታግደው ወደ ኒውዮርክ መጠራታቸው ታውቋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ስር የሚገኘው የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ ማውሪንግ ኢቻንግ እና የድርጅቱ  የስነ ህዝብ ፅ/ቤት (ዩኤንኤፍፒ) የኢትዮጵያ ኃላፊ ዴኒያ ጌይል ለጄፍ ፒሪስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሳቢያ፣ በሁለት ቀናት ልዩነት ከስራቸው ታግደው ወደ ኒው ዮርክ ተጠርተዋል፡፡
 ሁለቱ የስራ ኃላፊዎች በትግራይ እየተካሄደ ባለው የህግ ማከበር ዘመቻ ተከታታይ  ዘገባዎችን እየሰራ ለሚገኘው ጄፍፕሪስ ሰሞኑን በሰጡት ሰፊ ቃለ መጠይቅ ላይ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ለህወኃት ታጣቂ ሃይሎች እንደሚያደሉ ገልፀው ፍትሃዊ የእርዳታ እንቅስቃሴ መደረግ ይገባዋል የሚሉ ሌሎች  የስራ ኃላፊዎችን እንደ የሚያገሉ  ተናግረዋል፡፡
ኃላፊዎቹ በሰጡት በዚህ ቃለ ምልልስ፤ የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ለትግራይ ሃይሎች ርህራሄ እንዳላቸው ገልጸው፤ ሚዛናዊ አቋም ሊኖረን ይገባል የምንል የስራ ኃላፊዎችን ወደ ጎን ገሸሽ አድርገውናል ብለዋል፡፡
ባፈው ማክሰኞ ከስራቸው ታግደው  ወደ ኒውዮርክ የተጠሩት የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ ማውሪን ኢቻንግ፤ የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በአማራና አፋር ክልል ጥቃት መፈፀም ከጀመሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ሲሉ ወንጅለዋል፡፡ ከፍተኛ አመራሮችቹ ለህወኃት ሃይሎች ወገንተኝነትን ማሳየታቸውንና ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የድርጅቱን ባልደረቦች ማግለላቸውን ጠቁመዋል፡፡
የህወኃት ታጣቂ ኃይሎች “ቆሻሻና ጨካኞች” ናቸው ሲሉ የኮነኑት ሃላፊዎቹ ከሳውዲ አረቢያ የተባረሩት የትግራይ ተወላጅ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማስገባትና ወታደራዊ ስልጠና እንዲያገኙ  እገዛ እንዲያደርጉ ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ፤ የተመድ የስነ ህዝብ ፅ/ቤት (ዩኤንኤፒፍ)  የኢትዮጵያ ኃላፊ ዴኒያ ጌያል፣ ኢትዮጵያ የገቡ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪዎች፤ አዲስ አበባ የሚገኙ የተመድ ሃላፊዎችን በማለፍ በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ካሉ ኃላፊዎች ጋር በቀጥታ በመገናኘት ከእኛ ከሃላፊዎቹ እውቅና ውጪ የሆኑ ተግባራትን ያከናውናሉ ብለዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እነዚህ ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ያልተገባ አስተያየት ሰጥተዋል ያላቸውን ሁለት የድርጅቱን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከስራቸው አግዶ ወደ ኒውዮርክ ጠርቷቸዋል፡፡
 የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ያላቸውን ሰባት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከግዛቱ ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን ተከትሎ፣ ድርጅቱ እርምጃውን ህገ ወጥ ነው በማለት  በጥብቅ እንደሚቃወመው  ገልጾ ነበር፡፡ መንግስት የድርጅቱን የስራ ኃላፊዎች ከአገር ማባረሩ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱን ያስተጓጉለዋል ሲልም ለፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት ለአገር ደህንነትና ለፀጥታ ስጋት ናቸው ያላቸውንና ከተፈቀደላቸው ተግባርና ተልዕኮ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ነበር ያላቸውን የመንግስታቱ ድርጅት የስራ ኃላፊዎች ከአገር እንዲወጡ የማድረግ መብት እንደሌለው በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ዋነኛ ዓላማው ሰብአዊ እርዳታን ማድረስ ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ እያከናወነ ያለው ተግባር ከዚህ በእጅጉ የተለየ መሆኑን የገለፁት የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር ተስፋዬ ጌታነህ፤ የድርጅቱ ከፍተኛ ሃላፊዎች ከሽብርተኛው ቡድን ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጋለጣቸው ምክንያት የታገዱት የስራ ኃላፊዎች፣ የሰብአዊ እርዳታ የማድረሱን ተግባር በእጅጉ እንደሚያውክ እንዴት አልተገለፀላቸውም ሲሉ ጠይቀዋል።

Read 810 times