Wednesday, 13 October 2021 06:14

"ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፦

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ በሙዚቃ ውስጥ የህብረተሰቡን ድርሻ ሲገልጽ ምን ብሏል መሰለዎ ?
“ሕብረተሰቡማ ምን ያድርግ ? ሙሾውንም ሰጠ፤ የሰርግ ዘፈኑንም ሰጠ፤ ዓለማዊ ዘፈኑንም ሰጠ፤ ሲድር ደግሞ ‘ ጉሮ ወሸባ ‘ የሚባልበትንም ሰጠ። ሁሉንም ሰጠ። ከዚህ በላይ ምን አለውና ምኑን ይስጥ?
(“ፈርጥ” መጽሔት ሐምሌ /1992 በተፈራ መኮንን )
ይኸውልዎት እንግዲህ ሕብረተሰቡ ለእርስዎ ያለውን ሁሉ ሰጥቷል። አንድ ሕዝብ ለመሪው መስጠት የሚችለውን ሁሉ ሰጥቷል። ድጋፉን ሰጥቷል፤ ሕይወቱን ሰጥቷል፤ ድምጹን ሰጥቶ መርጧል፤ “ጦር ሜዳ ገብቶ ፈረስ አይለወጥም “ ብሎ መመረጥ ያለባቸውን የተፎካካሪዎችዎን እጩዎች ትቶ መመረጥ ያልነበረባቸውን የእርስዎን እጩዎች መርጧል። ሙሾውንም፣ የሰርግ ዘፈኑንም ሰጥቶዎታል። ሕዝቡ ያልሰጠዎት የለም። ከሕዝቡ የቀረ የለም። አሁን ያለው ከእርስዎ የሚጠበቀው ነው።
መስከረም 24 ቀን 2014 ከተመሰረተው አዲሱ መንግሥት ሕዝቡ ብዙ ይጠብቃል። ሕዝብ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ረሀቡንም ጥሙንም ችሎ ዝም ያለው፣ ሀገሪቷ እሷት ላይ መሆኗንና እርስዎም እሳት ማጥፋት ላይ መሆንዎን በማሰብ ነው። ሕዝብ በራሱ መሪዎች ሲበደልም ሲገደልም ዝም ያለው ይህን በመረዳት ነው። ስለዚህ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መስከረም 24 ቀን 2014 ለእርስዎ የደስታ ሳይሆን የፈተና መጀመሪያ ቀን ነው። ከዚያ በኋላ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ የተመረጠ የመጀመሪያው መንግሥት ምስረታ ቀን ይሆናል። ይህ መንግሥት ከሌሎቹ የበለጠ እዳ የተሸከመ መንግሥት ነው። ይህን ጦርነት በድል ይወጡታል። ኢትዮጵያ ስለምታሸንፍ። ማሸነፍ ስላለባት። ከዚያ ግን ፈተናዎ ይብሳል። የረጋ ሀገርን መምራት ይከብዳል። ሙሾውንም የሰርግ ዘፈኑንም የሰጠዎት ሕዝብ ከእርስዎ የሚጠብቀው እስካሁን የሰጡትን ያህል ብቻ አይደለም። እጅግ ብዙ ነው። ሕዝቡን እንዲያክሉ ፈጣሪ ይርዳዎ። አሜን።



Read 1706 times