Saturday, 09 October 2021 00:00

የእሳትና አበባ አውዳመት

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አባት ለልጁ የወፍ ወጥመድ ሰርቶ ሊያሳየው ፈልጎ እንዲህ አለው፡
“ይሄውልህ ልጄ! ወፍ ለማጥመድ ስትፈልግ ወንፊት ታዘጋጃለህ። ከዚያ እንጨት ታመጣና በገመድ ታስረዋለህ። እንጨቱን መሬት ላይ አቁመህ የወንፊቱን ጠርዝ እንዲደግፍ ታደርጋለህ። ከዚያም እንጨቱን ተደግፎ ከቆመው ወንፊት ስር እህል ትበትናለህ። ወፎች እህሉን ሊበሉ ሲመጡ ወንፊቱን ስር ይገባሉ። እህሉን እየለቀሙ ሳሉ፤ አንተ በእጅህ የያዝከውን ገመድ ስትጎትተው እንጨቱ ይወድቃል። ወንፊቱ ወፎቹ ላይ ይደፋል። ይሄኔ አንተ በቀስታ ወንፊቱን በአንድ ወገን ብቻ ከፈት ታደርግና፣ እጅህን አሾልከህ፣ ወፎቹን አንድ በአንድ ትይዛቸዋለህ” ይለዋል።
ልጁም አባቱ እንዳስተማረው በማድረግ፣ አንዲት ቆንጆ ቀለም ያላት ወፍ ይይዛል። አባት ደስ ይለዋል። አንድ አስገራሚ ነገር ግን የያል። ወፊቱ መናገር ትችላለች። እንዲህ ስትልም አወራችው-
“በህይወቴ የተማርኳቸውን ሶስት ምክሮች ልነግርህ እችላለሁ።”
ልጁም “ምን ምንድናቸው?” ሲል ጠየቃት።
ወፊቱም- “ሦስት ነገሮችን ለመፈጸም ፈቃደኛ ከሆንክ ብቻ ነው የምነግርህ”
ልጁም በጥድፊያ፤
“ሦስቱ ቅድመ ሁኔታዎች ምን ምንድናቸው?” ሲል ጠየቃት።
ወፊቱም፤ “የመጀመሪያውን ምክር እጅህ  ላይ እንዳለሁ እነግርሃለሁ።
ሁለተኛውን ምክር በአቅራቢያችን ካለው ከዚያ ዛፍ ላይ ሆኜ እነግርሃለሁ።
ሦስተኛውን ምክር አየር ላይ ስንሳፈፍ እነግርሃለሁ” አለችው።
ልጁም በወፊቱ ሀሳብ ተስማማና እጁ ላይ እያለች እንዲህ አለችው፡
“ምንም ይድረስብህ ምንም፣ ባለፈ ነገር አትጸጸት!” ልጁ በምክሯ ጠቃሚነት ተደሰተና ወፊቱን ለቀቃት። ወፊቱም ወደ አቅራቢያው ዛፍ በርራ ወጣች፤
“ሁለተኛው ምክሬ፤ የማይሆን ነገር ይሆናል ብለህ አታስብ”
ልጁ በምክሯ ተደሰተና
“ሦስተኛውስ?” ሲል ጠየቃት።
ወፊቱም፤ ወደ አየር ውስጥ ተንሳፋ፤
“ሦስተኛው ምክሬ፤ ያገኘሃቸውን ሁለት ምክሮች ምንጊዜም በሥራ ላይ አውል” አለችውና ከዐይኑ ተሰወረች።
*   *   *
የወፊቱ  ምክር ለማንኛችንም ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው። በተለይ በዚህ የአዲስ ተስፋን አበባ ባሳበብንበት ዓመት፣ አሁን የደረሰበት ወቅት ልዩ መልዕክትን የቀነበበ እንደሆነ የምናስተውልበት ነው። የምኞታችንን ችግኝ የምንቸግንበት በመሆኑም ለመላው ህዝባችን አዲስ ዕንቡጥ የምናፈካበት ነው። የመረረና የከረረም ሆነ የላላና የላሸቀ አካሄድን አስወግደን አማካይ ሂደትን የምናለመልምበት ጊዜ እየተንጸባረቀ ይመስላል። አንድም የአንድነትን፤ አንድም የብሔር ብሔረሰብን ብዝሃ- ህይወት ከሌሎችም አማራጮች ጭምር የምናመጣበት የእሳትና የአበባ ዘመን ነው። የዘንድሮውን መስከረም መጥባት ከዚህ ሂደት አኳያ የጎመን ምንቸት መውጫና የገንፎ ምንቸት መግቢያ ተስፋን እናጸኸይበታለን። “እነሆ መስከረም ጠባ!” የምንለው በዚህ መንፈስ ነው።
እነሆ መስከረም ጠባ
“የጎመን ምንቸት ውጣ
የገንፎ ምንቸት ግባ!”
በእሳትም ሆነ በአበባ
“ወልዶ መሳም
ዘርቶ መቃም”
በመስቀል ወፍ ዜማዊ እርካብ
በሳተና ጎፈሬ አጀብ
በልጃገረድ ሹሩባ፤ በኮበሌው ጸጉር ክብካብ
በከንፈር ወዳጅ፣ ዙር-ድባብ
ዐይን ካይን ጋር ሲናበብ
ቀልብ በፍቅር ሲያረብብ
እሰየው መስከረም ጠባ
“የጎመን ምንቸት ውጣ
የገንፎ ምንቸት ግባ!”
ባንድ ፊት መስቀል አበባ
የአደይ ቢጫ ውበት ፍካት፤
የእሳትና አበባ ጥምረት
ይኸው ታየ ጎኅ ቀደደ
የሳትና አበባ ድምቀት!
በራ መስቀል ደመራ
የችቦ ደቦ ደራ
እንግዲህ ዕቅድ ይፀነስ፣ የልባም ምኞት ጎመራ
ፈንዲሻው እርችት ሠራ
ዐይቤና ቅቤው ተጣራ
ቅመም ዝንጅብሉ እንጮቴው፣ ቆጭቆጫ፣ ቃሪያው አፈራ፣ ጠጅ ሳር፣ ናርዶስ መዓዛ፣ የሽቶው ሽታ፣ አውጋሩ የባህል ፈትል ድውሩ፣ ከእንቁጣጣሽ-መስቀል ክብሩ የዕምነት-ገዳው ፍካሬ፣ የአልባሳት ኅብረ-ዝማሬ፣ ሁሉም ኮራ በራ ዛሬ!
የደስ ደስ ባጨ ጎዳና
እስኪ ስላመት ያብቃና!!
መልካም በዓል


Read 10639 times