መልሱ አልተሰጠም
አንተነህ ግዛው
ምን ይረባታል፣ መልሱ ቢጠፋኝ
እያዟዟረች፣ የምታለፋኝ
አጉል ጠያቂ - ልክ የለው ሲጠም
ያደናግራል - እያማረጠም
ልማድ ሆኖበት - ዙሪያ መጠምጠም
መልስ ነው ይላል - መልስ አልተሰጠም
መላም የለው፣ መልስም የለው፣ መላም የለው፣ የሷስ ነገር
ሆነ ብሎ ማወናበድ፣ ሆነ ብሎ ማደናገር
የአንዳንዱ ጠያቂ፣ ንፍገትስ ይደንቃል
መርጠህ መልስ ብሎ፣ መልሱን ይደብቃል
ትክክል የመሆን - ዕድልን ነፍገሽኝ
ምረጥ ትይኛለሽ - መልሱን ሸሽገሽኝ
መላም መልስም የለው - መላም የለው የሷስ ነገር
ሆነ ብሎ ለማሳሳት - በጥያቄ ማደናገር
አስመርጣ መጣል ሲያምራት - ታዞራለች ዙሪያ ጥምጥም
መልስ ብላ ስታስጨንቅ - ልከኛውን መልስ አትሰጥም
ያንቺ ቢጤ ፈታኝ፣ አውቆ ሲያሰናክል
መልስ አልተሰጠምን፣ ያደርጋል ትክክል
ፈትነሺኝ ላላልፍ፣ አልወጣም አልወርድም
ጠማማ ጥያቄሽ፣ ቀና መልስ አይወልድም።
Published in
የግጥም ጥግ