Sunday, 03 October 2021 18:19

የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በ2 ወራት 39 ሚ. ዶላር ዘረፉ መባላቸውን አስተባበሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት በ2 ወራት ውስጥ ብቻ የዘረፉትን 39 ሚሊዮን ዶላር ጨምሮ ባለፉት 3 አመታት በድምሩ ከ73 ሚሊዮን ዶላር በላይ የህዝብ ሃብት መዝብረዋል በሚል ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የቀረበባቸውን ውንጀላ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው በማለት እንዳጣጣሉት ተዘግቧል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር፣ ባለፈው ሳምንት ባወጡት መረጃ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የህዝብን ገንዘብ እየዘረፉ ለግል ጥቅማቸው እንደሚያውሉ መናገራቸውን ያስታወሰው አልጀዚራ፤ የአገሪቱ መንግስት ግን ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ ውንጀላቸው በአለማቀፍ ደረጃ የተከፈተብኝ የስም ማጥፋት ዘመቻ አካል ነው ሲል እንዳጣጣለው ዘግቧል፡፡
የደቡብ ሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ማርቲን አሊያ ሎሙሮ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ውንጀላው የደቡብ ሱዳንን መረጋጋት የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች ሴራ አካል ነው፤ ዘረፋው ቢፈጸም እንኳን ህዝቡ ይጠይቀናል እንጂ ተመድ ምን ጥልቅ አደረገው ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም ፕሬዚዳንት ሳል ኬር ግን፣ እ.ኤ.አ በ2012 ባደረጉት ንግግር፣ የአገሪቱ ባለስልጣናት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የህዝብ ሃብት ወደ ውጭ አገራት ማሸሻቸውን በአደባባይ ማመናቸውን ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

Read 1419 times