Sunday, 03 October 2021 18:01

ቁስለቶች ወደ ካንሰርነት ሳይለወጡ ማስቆም ይቻላል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

pre-cancer ወደ ካንሰርነት ለመለወጥ ከ10-15 አመት ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡
precancerous lesion የሚለው አባባል የካንሰር ሴል መሳይ ግን የካንሰር ያልሆኑ ሴሎች በሰውነት ውስጥ ሲታዩና ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የመሰራጨት እድሉ የሌላቸው ናቸው፡፡
precancerous ጊዜ ቢፈጁም ወደ ካንሰርነት የመለወጥ እድል ያላቸው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡
የካንሰር ሴሎች ከጤነኝነት ወደ ካንሰርነት በመጀመሪያው ቀን አይለወጡም፡፡ በሁለተኛው ህመሙ እድገት ይኖረዋል። በሶስተኛው ወደካንሰርነት ይለወጣል እንደማለት ነው፡፡
  Precancerous cells በሰውነት ውስጥ ከካንሰር በፊት የሚፈጠሩ ሴሎች በፍጥነት ወደ ካንሰርነት ስለማይለወጡ በነበሩበት ሁኔታ ሕመም ሆነው ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ ሕክምና ከተደረገላቸውም ይድናሉ።   
የማህጸን ጫፍ እና ተያያዥ የሆኑ አካላት ላይ የካንሰር ሕመም ከመከሰቱ በፊት የሚደረገውን ጥንቃቄ እና በበሽታው ላለመያዝ በሴቶች የሚደረገውን ጥረት ወይንም ፍላጎት በኦሮሚያ በተለይም ሱዴ በምትባል ወረዳ የተደረገ ሲሆን መረጃውን ያኘነው ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጆርናል (Ethiopian Journal of Reproductive Health (EJRH) July, 2021 Volume 14, No. 2) ነው፡፡ ሱዴ የምትገኘው በኦሮሚያ አርሲ ዞን ሲሆን በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ 217 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡
ጥናቱ እንደሚያመለክተው በሴቶች የመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱት የካንሰር ህመሞች የሴቶች የመራቢያ አካላት የካንሰር ሕመሞች በሚል ይለያሉ። እነዚህ ሕመሞች የማህጸን ጫፍ፤ የጡት፤ የማህጸን፤  የብልት፤ የማህጸን ፍሬዎች ላይ የሚከሰቱ ናቸው። የማህጸን ጫፍ እና የጡት ካንሰር ከየትኞቹም የካንሰር ሕመሞች በከፋ ሁኔታ የሚከሰቱ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ለሚኖሩ ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ የጤና ጠንቆች ናቸው፡፡ በተለያዩ ጥናቶች እንደሚታየው 80% ያህል የካንሰር ሕመም እና 95% ያህል የማህጸን በር ካንሰር ሕመም የሚከሰተው ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ነው፡፡ ለዚህም እንደምክ ንያት ከሚቆጠሩት መካከል የመረጃ እጥረት፤ ችግሩ መኖሩን አስቀድሞ አለማወቅ፤ አገልግሎት ወደሚሰጥባቸው አካላት መድረስ አለመቻል የመሳሰሉት ናቸው፡፡ አገልግሎት ወደሚሰጥባቸው አካላት አለመድረስ ሲባል በገንዘብ ወይንም በመገናኛ እጥረት አለበለዚያም በርቀት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም ውጪም ሴቶች አስቀድሞውኑ ችግሩ መከሰቱን ልብ ብለው ሳይከ ታተሉ መቅረትና የሚረዳቸው ሰው በአጠገባቸው ማጣትንም የሚጨምር ሊሆን ይችላል፡፡
በመልማት ላይ ባሉ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ በማህጸን ጫፍ ካንሰር የሚያዙ ሴቶች የሚኖሩት በገጠር ነው፡፡ ምንም እንኩዋን እስከአሁን ባለው ዳሰሳ ትክክለኛው መረጃ ባይገኝም ወደ 99% የሚሆነው የማህጸን ጫፍ ካንሰር የሚከሰተው በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ከሚተላለፈው ኢንፌክሽን ነው፡፡  ለኢንፌክሽኑ መተላለፍ ምክንያት የሚባለው HPV (Human papilloma virus) በሴቶችላይ ከታዳጊነት እድሜ ትንሽ ከፍ ባሉት እና ወደሀያዎቹ መጀመሪያ ላይ ሰውነታቸው ለወሲብ ዝግጁ በሚሆንበት ወቅት ጀምሮ ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን የማህጸን ጫፍ ካንሰር ወደ ካንሰር ከመለወጡ አስቀድሞ የሚከሰተው ሕመም ልጅ በመውለድ እድሜ ባሉት ላይም ይታያል፡፡ ጋብቻ የፈጸሙ ወይንም ለማግባት የደረሱ፤ ከአንድ ሰው በላይ ወሲብ የሚፈጽሙ፤ በትምህርታቸው ዝቅ ያሉ በማህጸን ጫፍ ካንሰር ሊታመሙ ይችላሉ፡፡ በባህል ከሚፈጸሙ የጋብቻ አይነቶች በውርስ የሚፈጸመው የጋብቻ አይነት በሞት ባልዋ የሞተባት ሴት የባልዋን ወንድም እንድታገባ የሚደረግበት ልማድ በማህጸን ጫፍ ሕመም ለመያዝ እንደ አንድ ምክንያት ይሆናል።
የማህጸን ጫፍ ካንሰር ቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ ወደ ካንሰር ሕመምነት ሳይቀየር ህመሙ ሙሉ በሙሉ ሊድን የሚችል ሲሆን ይህም ሊፈጠር የሚችለውን ከባድ ሕመምና ሞት ሊቀንስ እንደሚችል እሙን ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ለሴቶች የማህጸን በር የቅድመ ካንሰር ምርመራን ፕሮግራም በእድ ሜያቸው ከ30 እስከ 49 አመት ያሉት ቀላል በሆነ መንገድ እና ውጤታማ እንዲሁም በተመጣጠነ ወጪ በተለይም አቅም በሌላቸው አገራት እንዲተገበር ያደረገ ሲሆን ይህም የማህጸን በር ካንሰር ሕመም እንዲቀንስ እና በዚህም የሚከሰተው ሞት እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አድርጎአል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው አለም አቀፍ ግንዛቤ በመነሳትም ኢትዮጵያ በካንሰር ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የካንሰር ሕመሞችን እና ሞትን ለመቀነስ የሚያስችል አሰራርን በመዘርጋት እ.ኤ.አ በ2020- 15% ያህል ዝቅ እንዲል አስችሎአል፡፡ ይህ አላማም በአገልግሎቱ መላ ህብረተሰቡን በ50% ያህል ለማዳረስ ያቀደ ሲሆን አገልግሎቱም የካንሰር ሕመም ምልክት የሌለባቸውን ሴቶች ጭምር እና እድሜአቸው ከ30-49 አመት የሆናቸውን ወደ 80% ያህል እንዲያድግ ይመኛል፡፡  
በኢትዮጵያ የተዘረጋው ንድፍ ከላይ እንደተጠቀሰው ቢሆንም በተግባር ግን በተለይም በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶችን መድረስ ያልተቻለ ሲሆን በማህጸን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ሕመም ዙሪያ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶችም መነሻቸው በከተሞች ውስጥ የሚገኙ የጤና ተቋማት ናቸው ይህንን ጽሁፍ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጆርናል ላይ ያወጡት ባለሙያዎች ምስክርነት፡፡ የዚህ ጥናት መነሻም ከላይ የተጠቀሰውን ምክንያት መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ በገጠራማ ቦታ መኖሪያቸውን ያደረጉ እድሜአቸው ከ30-49 አመት የሆኑ ሴቶች የማህጸን ጫፍ ካንሰር ከመከሰቱ በፊት የሚወስዱትን እርምጃ መመልከት ነው እንደ ጥናት አቅራቢዎቹ እማኝነት፡፡
ይህ ጥናት በተደረገበት ወቅት የተገኘው መረጃ እንደሚያስረገዳው እ.ኤ.አ በ2019 በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ 217 ኪ.ሜ በአርሲ ዞን ኦሮሚያ በምትገኘው ሱዴ ወረዳ የህዝቡ ብዛት 192,797 ያህል ሲሆን ከዚህ ውስጥ 42,665 ያህሉ ሴቶች ነበሩ፡፡ መረጃው እንደሚጠቁመው ወደ 20,973 የሚሆኑት ሴቶች እድሜአቸው በ30 እና 49 መካከል ነበር፡፡ በወረዳዋ የልጅነት ጋብቻ፤ በልጅነት ወሲብ መፈጸም፤ ከአንድ በላይ ግንኙነት ማድረግ፤ የውርስ ጋብቻ፤ እና ከአንድ በላይ ጋብቻ የመሳሰሉት በከፍተኛ ሁኔታ ይፈጸማሉ፡፡  የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው ለናሙና የተወሰዱት 633 ሴቶች የቀረበላቸውን ጥያቄ መቶ በመቶ መልሰዋል፡፡ ለጥናቱ የተወሰዱት ሰዎች አማካይ እድሜ 36,2 አመት ሲሆን ጥያቄ ከቀረ በላቸው አብዛኞቹ ማለትም 564 (89.1) ከመቶው በቅርብ ጋብቻ የፈጸሙ ነበሩ፡፡ ወደ 4646 (73.3) የሚሆኑት በጭራሽ ትምህርት ያልተማሩ ሲሆን 553 (87.4) የሚሆኑት የቤት እመቤቶች ነበሩ፡፡
በዚህ ጥናት እንደተረጋገጠው በማህጸን በር ላይ ካንሰር ከመከሰቱ አስቀድሞ የሚደረ ገውን ጥንቃቄ ወደ 4.7% ያህል መሆኑንና ይህም በገጠሩ ክፍል በመውለድ እድሜ ላይ ላሉ ሴቶች እና ለህብረተሰቡ ትልቅ የጤና ችግር መሆኑን ነው፡፡ ስሌቱም ሲገመት ማህጸን ህመሙ ወደካንሰር ከማደጉ ወይንም ካንሰር ሴሉ ወደሌላ አካል ከመሰራጨቱ በፊት ጥንቃቄ ማድረግ ወይንም ከመሰራጨቱ አስቀድሞ የመከላከሉ ትኩረት ማጣት በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ህዝብ ወደ 13.4% ያህል ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ እድሜአቸው ከ40-49 አመት የሆኑት ሴቶች ሕመም ከሁለት እስከ አራት ጊዜ ያህል በእድሜአቸው ከ40 አመት በታች የሆኑትን ይበልጣል፡፡ ይህም ምናልባት ለብዙ አመታት ከዘለቀው የወሲብ ግንኙነት አፈጻጸም ከሚኖረው ልዩነት እና በልጅነት ልጅን ከመ ውለድ ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል፡፡ ትዳራቸውን የፈቱ ሴቶችም በሚኖራቸው የተለያዩ ግንኙነቶች የተነሳ ከካንሰር አስቀድሞ የማህጸን በር ሕመም ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ በአዲስ አበባ የተደረገ ጥናትና በደብረ ማርቆስ የተደረገ ሪፖርት ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ የዚህ ምክን ያት ተብሎ የሚጠረጠረውም ከአንድ በላይ የወሲብ ግንኙነት መፈጸም በሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ለሚተላለፈው ኢንፌክሽን ስለሚያጋልጥ ነው እንደ ጥናት አቅራቢዎቹ እምነት፡፡ ስለዚህ ለችግሩ መስፋት ከሚባሉት ውስጥ፡-
ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ፤
ከአንድ በላይ ጋብቻ የሚፈጽሙ ፤
በውርስ ጋብቻ የሚፈጽሙ፤
በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ሕመም ገጥሞአቸው የነበሩ፤
ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ HPV የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ስለሆነ ለህመሙ የመጋለጣቸው ሁኔታ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ የማህጸን ጫፍ ካንሰር ከመከሰቱ አስቀድሞ የሚኖረውን ሕመም እንዳይከሰት ለማድረግ እና የካንሰር ሕመሙን ለመከላከል የሚረዳው ፡-
የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ከፍ ማድረግ፤
ቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ፤ ጠቃሚ መሆኑን ማስተማር ይገባል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሚመለከታቸው አካላት ፤መንግስታዊ ያልሆኑና መንግስትን ጨምሮ እንዲሁም ሌሎች ተባባሪ አካላት ከማህጸን ካንሰር ጋር ተያይዘው ነገር ግን ካንሰር ከመከሰቱ አስቀድሞውኑ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል፡፡   


Read 12534 times