Saturday, 25 September 2021 00:00

ራሚስ ባንክ ቅዳሜ በኢሊሌ ሆቴል የምስረታ ጉባኤውን ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በ6 ወር ውስጥ ግማሽ ቢ. ብር አሰባስቧል


              ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመውና ባፋይናንስ እጥረት ከህልማቸው ያልተገናኙ ኢትዮጵያውያንን ለማገዝ ያለመው የ”ራሚስ” ባንክ ለምስረታ የሚያበቃውን ሀብት አሰባስቦ ማጠናቀቁን አስታወቀ። ባንኩ፤ በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን አዲስ መመሪያ ግማሽ ቢ. ብር በ6 ወር የማጠናቀቅ ሂደት ያሟላ መሆኑን የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አብዱል ጀዋድ መሃመድና የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ኢብሳ መሃመድ ሀሙስ ረፋድ ላይ በኢሊሌ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
ባንኩ ከሁለት ዓመት በፊት ተቋቁሞ አክሲዮን መሸጥ ጀምሮ  የነበረ ቢሆንም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ መቆየቱን ያስታወሱት የባንኩ ሃላፊዎች ያን ሁሉ ጫና በመቋቋም ለምስረታ ከሚያበቃው የገንዘብ መጠን በላይ መሰብሰቡንና እስካሁን የተከፈለው የገንዘብ መጠንም 724 ሚሊዮን 612 ሺህ ብር መድረሱን ጠቁመው አስታውቀዋል። በቀጣዩ ሳምንት ቅዳሜ በኢሊሌ ሆቴል የመስራች ጉበኤውን እንደሚያካሁድ ጨምረው ገልጸዋል። ባንኩ ከ6 ሺህ በላይ ባለ አክስዮኖች በመላው አገሪቱ እንዳሉት ያስታወሱት አቶ ኢብሳ መሃመድ ተናግረዋል።
ባንኩ ለሽያጭ ካቀረባቸው 2 ሚሊዮን አክስዮኖች መካከል አብዛኞቹ ቃል የተገባላቸው እንደሆኑ የገለጹት ሃላፊዎቹ፤ የምስረታ ጉባኤው ከተከናወነ በኋላ ባንኮችን የመክፈትና ወደ ስራ የመግባት ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ እንደሚጠይቁ አመልክተዋል።
ራሚስ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ ተጠቃሚውን ማህበረሰብ ለማገዝና በፋናንስ እጥረት እየተጉላሉ ያሉትን  ወገኖች ለማገልገል የተመሰረተ ሲሆን በግብርና፣ ሀሳብን ፋይናንስ በማድረግና በተለያዩ ፍላጎት ባለባቸው የስራ ዘርፎች ብድር በማቅረብ እንደሚሰራ ሃላፊዎቹ ተናግረዋል።
“ከነባሮቹና አሁን እየተመሰረቱ ካሉት አዳዲስ ባንኮች ጋር ያለውን ውድድር በምን መል ለማሸነፍ ዝግጅት አድርጋችኋል?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ሲመልሱ “እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ ህብረተሰቡ ያለው የፋናንስ አቅርቦት አገልግሎት 30 በመቶ ብቻ እንደሆነና ገና 70 በመቶው ያልተሳካ በመሆኑ ውድድሩ ተግዳሮት አይሆንብንም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
“ራሚስ” የሚለው ቃል የአዋሽ ወንዝ ዋና ገባር የሆነ ታዋቂ የወንዝ ስም መሆኑን የገለጹት ሃላፊዎቹ ባንካችንም በዘርፉ ያለውን የፋይናስ ክፍተት በመሙላት፣ በአገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።


Read 1638 times