Print this page
Monday, 20 September 2021 16:38

የሶቅራጥስ ጅኒ (daemon) ምክር

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የአቴናው ሶቅራጥስ በፍልስፍና የታሪክ ሂደት ውስጥ ከዘመን ቅደም ተከተል አኳያ ከእርሱ ቀድመው (Pre-socratic) ከነበሩት ፍልሱፋን በተለየ ሁኔታ ያነሳቸው በነበሩት ጥልቅ የፍልስፍና እሳቤዎች፣  እንዲሁም ደግሞ ይኼንን ገቢራዊ ለማድረግ ይጠቀምበት በነበረውና የሶቅራጥስ መንገድ (Socratic Method) ተብሎ በሚታወቀው የመጠይቅ ስልቱም እጅግ ይታወቅ እንደነበር ይነገራል። ይኽ የሶቅራጥስ መንገድ ተብሎ የሚታወቀው በሌላ መጠርያው የማዋለድ ዘዴ (midwifery method) በመባልም ይታወቃል፤ ልክ አንዲት አዋላጅ የምትወልደውን እንስት ፅንሱን በሠላም እንድትገላገል ከመርዳት ውጭ ሌላ ነገር እንደማትፈይድላት ኹሉ፣ ሶቅራጥስም ልክ እንደ አዋላጅ እያንዳንዱን ሊቅ ነኝ ባይ ጥያቄ በመጠየቅ በልቡና ማኅፀን ውስጥ የተፀነሰውን ዕውቀት ከማዋለድ ውጭ ሌላ ሚና እንዳልነበረው ለማሳየት ይጥር ነበር። ቅድመ ታሪኩም እንደዚህ ነበር ይባላል፡- በአንድ ወቅት አንድ ኬይሪፎን (Chaerephon) የተባለ የሶቅራጠስ ባልንጀራ ደልፊ ወደተባለና በጊዜው ስመጥር ንግርት (Oracle)  የማወቂያ ሥፍራ  አንድ ነገር ለመጠየቅ  አቅንቶ እንደነበር ይነገራል፤ ጥያቄውም በዓለም ላይ ካሉት ሰዎች መካከል ጠቢብ ማነው? የሚል ነው። መልሱ ታድያ ሶቅራጥስ የሚል ነው የነበረው። ይኼን እንደተባለ የሰማው ሶቅራጥስ ግን ጠቢብ መባሉ እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥና ጥያቄዎችንም ከመጠየቅ አላገደውም፤ እንደውም ይኼ የተነገረለት ንግርት እውነት አለመኾኑን  ለማሳየት በሚመሥል መልኩ  አሉ የተባሉትን የአቴና “ጠበብት” የተለያዩ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎችን መጠየቅ መቀጠሉን እስከ ሕይወቱ ኅልፈት ድረስ አላቆመም ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ በእርግጠኝነት የሚያውቀው አንድ ነገር አለማወቁን ብቻ ነበርና። አፖሎጂ (Apology) በተባለውና የሶቅራጥስ ዋና ተማሪ እንደነበር በሚነገርለት አፍላጦን (Plato) እንደተጻፈ በሚታወቀው መጽሐፍ ላይ እንደተከተበው፤ ሶቅራጥስ ከእርሱ የሚልቁ ጠበብትን ፍለጋና አንድም ስለ እርሱ ጠቢብነት በደልፊ የተነገረው ንግርት እንደው የመላ የነሲብ አነጋገር እንደኾነ ለማረጋገጥ ከጠየቃቸው የዘመኑ “ጠበብት” መካከል የፖለቲካ ልሂቃን፣ ባለቅኔዎችና አደጓሪዎች (craftsmen)  ይገኙበት ነበር። በመጨረሻ ላይ ሶቅራጥስ የደረሰበት ድምዳሜ ግን  እነዚህ ኹሉ ምንም እንደማያውቁና ነገር ግን ራሳቸውን ልክ እንደ ዐዋቂ ይቆጥሩ እንደነበር ነው፤ በእነርሱና በእርሱ መካከል የነበረው ልዩነት ደግሞ ከላይ እንደተጠቀሰው እርሱ ከእነርሱ በተቃራኒ አለማወቁን በጥልቀት ማወቁ ብቻ ነበር።
በዚህ  አጭር ጽሑፍ ውስጥ የሃሳባችን የስኅበት ማዕከል እንዲኾን የፈለግነው ሶቅራጥስ፤ የዘመኑ የፖለቲካ ክበብ ላይ እንዳይሳተፍ ለመወሰን ምክንያት የኾነውን ነገር እንደ መንደርደርያ አስከትለን ጥቂት  እይታን ለማጋረት አልመን ነው።
ሶቅራጥስ በአፖሎጂ ላይ እንደሚከተለው ብሎ ነበር፡- ምናልባትም  አንዳንዶቻችሁ ለምንድነው ወደ አደባባይ በመምጣት ሃገረ መንግሥቱን ከማማከር ይልቅ ሰዎችን በግል በማማከርና ስለ እነርሱ በማሰብ ራሱን ፋታ የሚያሳጣው ብላችሁ ልትጠይቁ ትችሉ ይኾናል። የዚህን ምክንያት ልንገራችሁ።  ወደ እኔ ዘንድ ስለመጣው ንግርትና  ትእምርት (sign) ስናገር በተደጋጋሚ ሳትሰሙኝ አትቀሩም፤ ይኼንንም መለኮታዊነት ሜሊተስ (Meletus) በክሱ ሂደት ያጥላላው ጉዳይ ነበር። ይኽ ትእምርት ከልጅነቴ ጀምሮ ይከተለኝ የነበረ ነገር ነው፤ ይኽ ምልክት  ወደ እኔ የሚመጣ ድምፅ ሲኾን  ሁልጊዜ ላደርገው የምፈልገውን ነገር እንዳላደርግ የሚከለክለኝ ነበር፤ ነገር ግን የኾነ ነገር አደርግ ዘንድ ግን ትዕዛዝን አይሰጠኝም ነበር። እንግዲህ ይኽ ነበር ፖለቲከኛ እንዳልኾን አግዶኝ የነበረው።  የአቴና ሰዎች ሆይ! እኔም በእርግጥ እንደማስበው ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ቢኖረኝ ኖሮ፣ ከብዙ ጊዜ በፊት ደብዛዬ ይጠፋ ነበርና፤ በዚህም የተነሳ ለናንተም ኾነ ለራሴ አንዳች ፋይዳ ያለው ነገርን መሥራት አይቻለኝም ነበር።
Plato: APOLOGY OF SOCRATES
ሶቅራጥስን ከልጅነቱ ጀምሮ ምልክትን በመስጠት ይከለክለው እንደነበር የነገረንን አካል ዓቃቤ መልአክ አልያም ደግሞ በዓረቢ ልሳን ‘ጅኒ’ ብለን ልንጠራው እንችላለን። ጅኒ የሚለውና ሴማዊ ጥንት (origin) እንዳለው የሚታመነው የዓረብኛ ሥም የሚያመለክተው  አንድ ከህዋሳተ አፍኣ (senses) የተደበቀን ህላዌ (being)  ለመግለጽ ነው። ለማንኛውም ይኼ የሶቅራጥስ አማካሪ ምልክትን በመስጠት ጭምር ከልጅነቱ ጀምሮ እንዳያደርገው ይከለክለው ከነበሩት ነገሮች መካከል በፖለቲካ ውስጥ እንዳይሳተፍ የመምከሩ ጉዳይ ነው። በዚያ ላይ ይኼ አማካሪ ጅኒ ስልጡን ባሕርይ ቢጤ ያለው ሳይኾን አይቀርም፤ ምክንያቱ ደግሞ መከልከል እንጂ ማዘዝ ባለመፈለጉ ነው። ቢያንስ አለማድረግን እንጂ ማድረግን ካላስተማርኩህ ብሎ ችክ የማይል ዓይነት ነው።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፤ የሶቅራጥስን ልቡና ብሩህ እንዲኾን አድርጐት የነበረው ከፍተኛ የማሰብ አቅም (Personal faculty) በዘመኑ በነበሩት አቴናውያን ዘንድ ምናልባትም ራሱን የቻለ ጅኒ ወይም ከጅኒ ጋር እንደተያያዘ ተደርጎ ይታይ የነበረ ሳይኾን አይቀርም። በእርግጥ አሁን ሳይንስና ቁሳዊነት በተንሰራፋበት ሁኔታ ውስጥ ለምንኖር ሰዎች ስለ ዲበአካላዊ ህልዋን (metaphysical beings) አንስቶ መወያየቱ ብዙም ቀልብ የማይሰጠውና ተአማኒነት የሌለው ተደርጐም ሊወሰድ ይችላል፤ በፍልስፍና ግን አሁንም ድረስ ቁልፍ የምርምር ዘርፍ እንደኾነ የቀጠለ ጉዳይ ነው። በእርግጥ ከሶቅራጥስ ቀድሞ የነበረውና ሄራክሊተስ በመባል የሚታወቀው ፈላስፋ የሰው ጠባይዕ መንፈሱ ነው (“ethos anthropos daimon”) ማለቱን ስናስተውል፣ በቀድሞ የጽርዕ ፍልስፍና ውስጥ ለዲበኣከላዊ ህልዋን ይሰጥ የነበረው  ሥፍራ ራሱን የቻለና ትልቅ  እንደነበረ እንገነዘባለን።  በሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብዙዎች ፖለቲካን እንደ ትልቅ ሙያ ቆጥረውትና ከዚያ ውጭ ሙያ የሌለ እስኪመስል ድረስ  መድረኩን አጨናንቀውት ስንመለከት፣ ያ ሶቅራጥስን ፖለቲካ ላይ እንዳይገባ ይከለክለው የነበረው ስልጡን ጅኒ ምናልባትም በብዙ ምዕራፍ ርቋቸዋል  ለማለት የሚቻል ይመስላል፤ ስለዚህ ድምፁ እየተሰማቸው አይደለም፤ በመኾኑም አማካሪ አልባ ናቸው ማለት ይቻላል። በእርግጥ በዓለማችን አሠራር  በፖለቲካ እንዳትሳተፍ ለመከልከል የግድ እንደ ሶቅራጥስ የማይታይ ጅኒን ምክር መቀበል ላይጠበቅብህ ይችላል፤አምባገነን መንግሥታትም ለመንበራቸው ልታሰጋቸው ትችላለህና ራሳቸው በአካል ተገልጸው ይመክሩሃል ይዘክሩሃል፤ እምቢ ካልክ ደግሞ ወደ ወኅኒ ይወረውሩሃል። ልዩነቱ የሶቅራጥስ በፖለቲካ ውስጥ እንዳይሳተፍ መከልከሉ  አንድም ፖለቲካ፣ ያው የአላዋቂዎች ስብስብ በመኾኑ ቁምነገር አይገኝበትም ብሎ እና ሌላው ደግሞ ቀሪ  ጊዜውን ለፍልስፍናና ለጥበብ በማዋል ያለማወቅ ክፍተቱን ለመሙላት ፈልጐም ነው። በዚህ ተቋማዊ አስተሳሰብ በበዛበትና ሰዎች እንደ ግለሰብ ሳይኾን እንደ ቡድን በሚያስቡበት ጊዜ ላይ የሶቅራጥስን ዘመን አይሽሬ የትምህርት መንገድ መቅሰም አስፈላጊ ነገር ሳይኾን አይቀርም፤ ምክንያቱም ሶቅራጥስ ከፖለቲካ ሹመኝነት ይልቅ ራሱን ለፍልስፍና ጥያቄዎች አሳልፎ በመስጠቱ ማንም የማይቀማውን በጎ ዕድልን መርጧልና። እርሱ እዚህ ውሳኔ ላይ በመድረስ መፈላሰፉን ቀጥሎ የነበረ ቢኾንም ታድያ የአቴና ፖለቲከኞች ግን በተለያየ ሰበብ ችሎት ፊት አቀረቡት፤ በፍልስፍና መስታወት አለማወቃቸውን በማሳየቱ እንደ ወንጀለኛ ለመቆጠር በቃ።
ከቢር (Kabir) በመባል የሚታወቀው የአስራአምስተኛው ክፍለዘመን ታዋቂ የህንድ ባለቅኔ እንደዚህ ብሎ ነበር፡- በዕውር ከተማ ውስጥ መስታውትን እሸጣለሁ (“I sell mirrors in the city of the blind”).
በመጨረሻም የሶቅራጥስ ኅልፈት  ጉዳይ በአቴናውያን ሸንጎ እጅ ለመውደቅ በቃ። ሶቅራጥስ በጊዜው  ተከስሶባቸው ከነበሩት ኹለት ነገሮች መካከል አንደኛው ወጣቶችን በፍልስፍናዊ የመጠይቅ መንገዱ (maieutics) እየተጠቀመ  ከስነምግባር እንዲያፈነግጡ ያደርጋል የሚል ሲኾን፤ ሌላኛው ደግሞ  በእኛ አማልክት አያምንም፤ እንደውም አዳዲስ አማልክትን አስተዋውቋል በሚል ነው። ሶቅራጥስ በእነርሱ የፍርድ ሚዛን ጥፋተኛ እንደኾነ ሲወሰንበት ኹለት አማራጮችን ሰጥተውት ነበር፤ ወይ ሃገራቸውን ለቅቆ እንዲሰደድ አልያም ደግሞ ሄምሎክ የተባለውን መርዝ ጠጥቶ እንዲሞት፤ ሶቅራጥስም መርዝ ጠጥቶ መሞትን መረጠ።
በቀላሉ ለመረዳት እንደሚቻለው የሶቅራጥስ ሞት መንስኤ ሌላ ነገር ሳይኾን ጥያቄ መጠየቁና መፈላሰፉ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ላይም ብዙ ጠያቂና አሳቢ ምሁራንን እንጂ ፖለቲከኞች ብቻ የምንፈልግበት ጊዜ ላይ ያለን አይመስለኝም፤ በገሃድ የምናየው ሃቅ ግን በተቃራኒው ነው፡፡




Read 1351 times
Administrator

Latest from Administrator