Sunday, 19 September 2021 00:00

በጦርነት ክፉኛ የተጎዳችው ወሎ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለወሎ አካባቢ በፌደራሉም ሆነ በክልሉ መንግስት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ፡፡ እናንተ ወደ አካባቢው ከተንቀሳቀሳችሁ በኋላ ሁኔታውን እንዴት ገመገማችሁት? ወሎ በአሁኑ ወቅት በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው?
አሁን ባለው ሁኔታ የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ሶስት አካባቢዎች ላይ ገብተው ይገኛሉ፤ በዋግህምራና ሰሜን ወሎ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲሁም ደቡብ ወሎ ደላንታ አካባቢ ፀሃይ መውጫ የምትባል ቦታ ገብተው ነው ያሉት። በእርጥ ይሄ ከፌደራል መንግስትም ሆነ ከአማራ ክልል ትኩረት አልተሰጠውም የሚባለው ብዙ ነገሮችን በዝርዝር ማየት የሚጠይቅ ይመስለኛል። ቅሬታ ያለው ጉዳዩ በሚዲያ ተገቢው ሽፋን አልተሰጠውም ከሚለው ጋር የተያያዘ እንጂ ሁኔታውን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ተገቢው ነገር እየተደረገ እንደሆነ እንገነዘባለን። ሰራዊቱ ከደቡብ ጎንደር ቦታዎችን አስለቅቆ ወሎ አካባቢዎችን ነፃ ለማውጣት ያልተቋረጠ ጥረት እያደረገ ነው። በተለይ የጠላት ሃይል ቀድሞ ወሯቸው በነበሩ አካባቢዎች ላይ ብቻ እንዲገታ እንዲሁም ባሰበው ልክ እንዳይስፋፋ ተደርጓል። ጠላት ወደፊት እንዳይገፋ የአማራ ልዩ ሃይልና የአካባቢው ገበሬዎች ተጋድሎ እያደረጉ ነው። ጠላት ወዴትም እንዳይስፋፋ በማድረጉ በኩል ወሳኝ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ታዝበናል። ጦርነት ተዋግተህ የምታገኘው ውጤት እንደመሆኑ ጠንካራ ውጊያ እየተደረገ ነው። በዚህ ረገድ መንግስት ችላ ያለው ነገር እንደሌለ ተረድተናል።
የአካባቢው ህዝብስ ራሱን ለመከላከል ዝግጅቱ ምን ይመስላል? ስለ ጦርነቱስ ግንዛቤው ምን ያህል ነው?
እኛ ተዘዋውረን ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደተረዳነው፣ ህዝቡ የጦርነቱን አሳሳቢነት በማያወላዳ መልኩ ተገንዝቧል። በተለይ ገበሬው በሚገባ ተደራጅቶ ራሱን ለመከላከል ጥረት እያደረገ ነው። እኔ ባለሁበት ተንታ አካባቢ ከህዝቡ ጋር ስብሰባ ለማድረግ ሞክረን ነበር። በዚህም የተረዳነው የአካባቢው ህዝብ ራሱን በሚገባ ማደራጀቱን ነው። በተለይ ተንታ  ወሳኝ ቦታ ነው። በ1982 ህወኃት ደርግን ለማሸነፍ እንደ ትልቅ ስትራቴጅያዊ ቦታ የተጠቀመበት ነው። ከዚህ አንጻር፣ የአካባቢው ሚሊሻና ወጣት በየኬላዎቹ ጠንካራ ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑን ተረድተናል። በሌላ በኩል፣ ህዝባዊ ተጋድሎው በአንድ የተሰባሰበ ማዕከል ስር እንዲሆን የአካባቢው ወጣቶችና ሚሊሻ መከላከያውን ለመቀላቀል ተመዝግበዋል። በአጠቃላይ አካባቢው ላይ ጥሩ ግንዛቤና ንቃት እንዳለ መገንዘብ ችለናል። ቀደም ብሎ አሸባሪው ቡድን ወረባቦ ለሁለት ቀን ቆይቶ በነበረበት ወቅት የገበሬውን ሃብት ሁሉ ሲዘርፍና ማህበረሰቡን ሲያጎሳቁል እንደነበር መረዳት ችለናል። በተለይ እኔ ያነጋገርኳቸው አንድ አባት፤ የአሸባሪው ቡድን አባላት  ከገበሬው የሚዘርፉት ሲያጡ ጣራ ላይ ወጥተው ከጣሪያ ጋር የተጣበቀን ሶላር ፓኔል ሲዘርፉ እንደነበር፣ ከጣራው አልላቀቅ ያላቸውን እዚያው በድንጋይ አድቅቀው አውድመውት እንደሄዱ አስረድተውኛል። በሰሜን ጎንደር አካባቢ የደረሰውን ጭፍጨፋም ህዝቡ እንዲያውቀው አድርገናል። በዚህም ከመሰል ጭፍጨፋ ለመዳን ለህልውናው እንዲፋለም መነቃቃትን ፈጥረናል።
ታጣቂው ቡድን በተለይ ደሴን ለመያዝ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል። ከዚህ አንፃር የደሴ ህዝብ ስሜቱ ምን ይመስላል?
ደሴ ከተማ ታሪካዊና በርካታ ሃብት ያለባት ከተማ ስትሆን፤ ኮምቦልቻም ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ማዕከሎች ያሉባት መሆኗ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር፣ ደሴንና ኮምቦልቻን ለመያዝ ያልተደረገ ጥረት የለም። እነዚህን ሁለት ከተሞች ደግሞ መያዝ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። የደሴ ህዝብ ብዛት እንግዲህ እስከ መቶ ሺህ ይገመታል፤ ኮምቦልቻም ከ100 ሺህ በላይ ህዝብ የሚኖርበት ነው። ስለዚህ ጁንታው ወደ እነዚህ ከተሞች ቢገባ የደሴ ህዝብ ሃብቱን እንደሚዘረፍና ህልውናውን እንደሚያጣ በሚገባ ተረድቷል። ስለዚህም ከአካባቢው የትም ንቅንቅ ሳይል ራሱን ለፍልሚያ ማዘጋጀትን ነው የመረጠው። የደሴ ከተማ በሌላ አንጻር አሁን ከፍተኛ ተፈናቃዮችን የያዘ ከተማ ነው። ተፈናቃዮቹና  የደሴ ህዝብ የጁንታውን ወሬ ሰምቶ ቢፈናቀል፣ ሊፈጠር የሚችለውን መገመት አይከብድም። የትኛው ከተማ ነው ይህን ተፈናቃይ ሊሸከም የሚችለው? ምናልባት አዲስ አበባ ነው። ስለዚህ የደሴም ሆነ የኮምቦልቻ ህዝብ አካባቢውን ጥሎ የትም እንደማይሸሽ አረጋግጧል። ነዋሪው በሚገባ ተደራጅቶ የሚቃጣበትን ጥቃት ለመመከት ነው ተዘጋጅቶ ያለው። ህዝቡ ጠላት ምናልባት አልፎ ቢመጣ እዚሁ ከተማችን ላይ እንዋጋለን ብሎ ነው ራሱን አዘጋጅቶ የሚጠብቀው፡፡ ስነ-ልቦናውም በዚሁ የተቃኘ ሆኖ ነው ያገኘነው። ወጣቱ እንደውም ጦርነት ወዳለባቸው አካባቢዎች ሄዶ መከላከያንና የአማራ ክልል ልዩ ሃይልን ተቀላቅሎ ነው እየተፋለመ ያለው። ጠላት በተለያዩ አካባቢዎች ነው ደሴን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ያለው። ነገር ግን መከላከያ፣ የአማራ ልዩ ሃይልና የአካባቢው ወጣትና ገበሬ ጠንካራ መከላከል አድርጎ ወዴትም እንዳይስፋፋ አድርጎታል። የአካባቢው አመራሮች ከህዝብና ከመከላከያው ጋር ተቀላቅለው ነው እየተዋጉ የሚገኙት፡፡ ውሎ  አዳራቸው በግንባር ሆኗል ማለት ይቻላል።
ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ የህወኃት ሃይል በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ረሃብ እንደተከሰተ እየተነገረ ነው። እስኪ እናንተ በቅርበት የታዘባችሁትን ይንገሩን?
እኛ እንደ ሲቪል ማህበር የረሀቡን ሁኔታ ለማጣራት ጥረት እያደረግን ነው። በእርግጥ ወትሮም በሴፍቲኔት ፕሮግራም ስር በነበረው የዋግህምራ ዞን ችግሩ እንዳለ ተረድተናል። ዋግህምራ መሬቱ ምርታማነት የሚያንሰው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አብዛኛው ዞኑ በእርዳታ ስር ያለ ነበር፡፡ የሰቆጣ ቃል ኪዳን የሚባል ስምምነትም እንዳለ ይታወሳል፡፡ ይሄ ቃል ኪዳን በአካባቢው ያለ እድሜ በምግብ እጥረት መቀንጨርን መቆጣጣር ላይ ያለመ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አካባቢው ባለፉት 3 ወራት ገደማ ተደራሽ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ረሀብ የመከሰቱ ነገር ብዙም አጠራጣሪ አይሆንም። በሌላ በኩል፤ ከጁንታው ነፃ በወጡ አካባቢዎች እርዳታ እየቀረበ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። ህዝቡን በዋናነት ለችግር ያጋለጠው ግን የጁንታው ዘረፋና ውድመት መሆኑን ለማወቅ አይከብድም፡፡ ነገር ግን አሁንም ይሄ አካባቢ በጠላት ስር ሆኖ ከቆየ የከፋ ረሀብና እርዛት መፈጠሩ አይቀሬ  ነው። በሌላ በኩል፤ ጠላትን መክተው በመያዝ የሚታወቁት የሶዳማና ድሬ አርሶ አደሮች ጠላትን ከመግጠማቸው በፊት አቅመ ደካማ ቤተሰቦቻቸውን  አፋር አካባቢ ወደ አንድ ሰወር ያለ ስፍራ አስቀምጠዋቸው ነው እነሱ ጠላትን ገጥመው እየተዋጉ  ያሉት። ስለዚህም ለእኒህ ለተፈናቀሉ የጀግና ቤተሰቦችም መድረስ ይገባል፡፡ ያሉበት አካባቢ ሞቃት ከመሆኑና ተሰባስበው ከመገኘታቸው ጋር ተያይዞ ለከፋ ወረርሽኝ እንዳይጋለጡ ስጋት አለን፡፡ ለዚህ ሁሉም አካል ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ በኛ የወሎ ህብረት በኩል ለጊዜው ለመስከረም ወር የሚሆን መጠነኛ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ነገር ግን ህፃናት ላይ ወረርሽኝ መሰል በሽታዎች መታየታቸው አሳሳቢ ነው፡፡ እኛም በህብረታችን በኩል የጤና ባለሙያዎች አሰማርተን ምርመራዎች እያደረጉ ነው፡፡ በዚያ አካባቢ ወደ 32 በመቶ የሚሆኑት ተፈናቃዮች ህጻናት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ህፃናት ውስጥ ብዙዎቹ ላልታወቀ ወረርሽኝ ተጋልጠዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎች ምርመራ እያደረጉ እኛ የተወሰኑ መድሃኒቶችን ለመግዛት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በአብዛኛው ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በብዙ ችግሮች ውስጥ እያለፉ ነው። ምናልባት ደሴ እና ኮምቦልቻ ላይ ያሉ ተፈናቃዮች በቂ ድጋፍ እያገኙ ነው፡፡ በሌላው አካባቢ ግን እንደዚህ አይነት ድጋፍ የለም፡፡ ብዙዎች ተቸግረው ነው ያሉት። ከሁሉም የሚያሰጋው ግን የዋግህምራ ዞን ሁኔታ ነው፡፡ ረሃብ የተከሰተው በዚሁ አካባቢ ነው። በሌሎቹም ቢሆን ወደ ረሃብ ሊያድግ የሚችል ሁኔታ ነው እየተመለከትን ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ሳልጠቅስ የማላልፈው ነገር እኛ እንደ ወሎ ህብረት የቻልነውን እያደረግን ነው፤ ነገር ግን ብቻችንን የምንወጣው ጉዳይ አይደለም፡፡ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው የገጠመን። ይሔ አሸባሪ ቡድን እያደረሰ ያለውን ውድመት ወሎ ህብረትም ሆነ የአካባቢው አስተዳደር ብቻውን የሚወጡት አይደለም። ለምሳሌ  ወልዲያ ላይ እኛ ባለን መረጃ፣ 23 ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማትን ሙሉ በሙሉ አውድሟቸዋል፡፡ የጤና ኬላ የሚባሉት ሁሉ ወድመዋል፤ ት/ቤቶች የሉም፤ መድሃኒት ቤቶች ተዘርፈዋል፤ የስኳር በሽተኞች ሳይቀሩ መድሃኒት በማጣት እየተቸገሩ ነው፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤት ንብረት የሚባል ነገር ሁሉም ተዘርፏል፤ የግለሰብ ተሽከርካሪዎች በሙሉ ተዘርፈዋል። አርሶ አደሮች ሰብላቸውን፣ እህላቸውን ተዘርፈዋል፤ ወድሞባቸዋል። ስለዚህ ጉዳዩ መጠነ ሰፊ ችግር ነው። ይሄን ችግር ለመወጣት አሁን እኛ ማድረግ የምንችለው የደረሰውን ውድመት አጥንተን ለመንግስትና ለአለማቀፉ ለጋሾች ሪፖርት ማድረግ ነው። ይሄን ለማድረግ አንድ በባለሙያዎች የተደራጀ ገለልተኛ የጥናት ቡድን አቋቁመናል፡፡ ስራውንም እየጀመርነው ነው። ጥናቱን ለማድረግ በራሱ ከፍተኛ ጉልበት ጊዜና ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የህብረተሰቡን ስነ ልቦና ለመጠገን ሌላ ቡድን አዘጋጅተን ህዝቡን ለማበረታታት እቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይሄን ለማድረግ እንግዲህ የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ትብብር እንፈልጋለን። የኢትዮጵያ ህዝብም ትብብሩን እንደማይነፍገን እርግጠኞች ነን፡፡

Read 1369 times