Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 13:11

ዶ/ር እሌኒ፤ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ይሸለማሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሽልማቱን፣ የገጠር ሴት ተማሪዎችን ለመደገፍ አውለዋለሁ ብለዋል

የኢትዮጵያ እህል ገበያ ድርጅትን በማቋቋምና በመምራት አድናቆትና ዝና ያተረፉት ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን፤ በኖርዌይ ያራ ፋውንዴሽን የአመቱ ተሸላሚ ሆነው ተመረጡ። ከሶስት ሳምንት በኋላ በታንዛኒያ በሚካሄድ ስነስርአት የ30ሺ ዶላር (የግማሽ ሚሊዮን ብር) ሽልማት የሚቀበሉ ሲሆን፤ ገንዘቡን በገጠር ሴት ተማሪዎችን ለመደገፍ እንደሚያውሉት ዶ/ር እሌኒ ተናግረዋል።በኖርዌይ ትልቁ የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ መስራችነትና በተለያዩ የአገሪቱ መንግስታዊ ተቋማትና ደጋፊ ድርጅቶች የትብብር የሚንቀሳቀሰው ያራ ፋውንዴሽን፤ የመጀመሪያውን ሽልማት በ1998 ዓ.ም ለጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መስጠቱ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ የእርሻ ልማትን ለማሻሻልና ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል በማለት ጠ/ሚ መለስን ከሸለመ በኋላ፤ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በእርሻና በገጠር ልማት መስኮች ከፍተኛ ስኬት አስመዝግበዋል ተብለው የተመረጡ 7 የቢዝነስ መሪዎችንና የተቋም መስራቾችን ሸልሟል።ዶ/ር እሌኒ፤ በኢትዮጵያ የእርሻ ገበያ ውስጥ በአዲስ አቅጣጫ መሰረታዊና ውጤታማ ለውጥ የሚያመጣ ስራ አከናውነዋል የሚለው ያራ ፋውንዴሽን፤ በዶ/ር እሌኒ መሪነት የተመሰረተው የኢትዮጵያ የእህል ገበያ ድርጅት በተለይ የቡና አምራች ገበሬዎች ያለ ብዙ ወጪ እንዲገበያዩ አስችሏል ብሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስና ዘመናዊ የገበያ አሰራርን መፍጠር ፈታኝና ውስብስብ እንደነበረ ፋውንዴሽኑ ጠቅሶ፤ ዶ/ር እሌኒ ውጤታማ አሰራሮችን በመፍጠርና አዳዲስ መንገዶችን በማሳየት ስኬት አስመዝግበዋል ያለው ፋውንዴሽኑ፤ ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም አነቃቂ አርአያ ሆነዋል በማለት ለሽልማት እንደመረጣቸው ገልጿል።በሽልማቱ እንደተደሰቱ የተናገሩት ዶ/ር እሌኒ፤ የኢትዮጵያ እህል ገበያ ድርጅት በአጭር ጊዜ ውስጥ እውቅና ማግኘቱንና ኢትዮጵያ በጥቂት አመታት ውስጥ ለሽልማት መመረጧን ጠቅሰው ጠ/ሚ መለስ ይሄን ሳያዩ ማለፋቸው ግን ይቆጫል ብለዋል። ጠ/ሚ መለስ ከያራ ፋውንዴሽን ያገኙትን ሽልማት የገጠር ሴት ተማሪዎችን ለመደገፍ እንዳበረከቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ዶ/ር እሌኒም ሽልማታቸውን ለተመሳሳይ አላማ እንደሚያውሉት ገልፀዋል።

 

 

 

Read 39382 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 13:33