Saturday, 18 September 2021 16:43

ኢትዮጵያውያን አመጋገባቸውን ሊቀይሩ ይገባል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 70 በመቶ ኢትዮጵያውያን ካርቦ ሃይድሬት ያላቸውን ምግቦች ብቻ እንደሚያዘወትሩ ያመለከተው በኢትዮጵያውያን የአመጋገብ ስርዓት ላይ የተካሄደው ጥናት፤ በዚህም ሃገሪቱ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ በሚከሰቱ በሽታዎች ለዜጎቿ የምታወጣው ወጭ ከፍተኛ ነው ብሏል።
መቀመጫውን ኬንያ ናይሮቢ ያደረገውና በሥነ-ምግብ ምርምሮች የሚታወቀው “Global Alliance for Improved Nutrition (GAIN)” የተሰኘው ተቋም፣ በኢትዮጵያውያን አመጋገብ ላይ ያካሄደውን ጥናት ከትናንት በስቲያ ይፋ ያደረገ ሲሆን ሃገሪቱ በዜጎቿ የአመጋገብ ጉድለት የተነሳ ለህክምና የምታወጣው ወጪ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሟል።
በሃገሪቱ የሚወለዱ ህፃናት የተሟላ አካላዊና አዕምሯዊ እድገትና ጤንነት እንዲኖራቸው፣አገሪቱ ወደ ተመጣጠነ የምግብ ስርዓት የሚወስድ ስልቶችን ልትተገብር እንደሚገባ  በትናቱ ጠቁሟል።
እያንዳንዱን ምግብ በ1 ዶላር ወጪ ብቻ በማዕድናትና ቫይታሚኖች የበለጸገ በማድረግ 13 ዶላር ያህል በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰት  በሽታን መከላከል ይቻላል  ብሏል- የተቋሙ የጥናት ውጤት።
በሃገሪቱ የምግብ ስርዓት ውስጥ ለፋብሪካ የሚዘጋጁ እንደ ዱቄት ያሉ ምግቦችን በትንሽ ወጪ በተለያዩ ለጤና ጠቃሚ በሆኑ ማዕድናትና ቫይታሚኖች የበለፀጉ በማድረግና ለተጠቃሚው በማሰራጨት የማህበረሰቡን የአመጋገብ ስርዓት ስልታዊ በሆነ መልኩ በመቀየር ጤናማ ህብረተሰብ  ማፍራት እንደሚቻል በጥናቱ ተመልክቷል።
በተለይ በፎሊክ አሲድና ቫይታሚን ኤ የበለፀጉ ምግቦችን በማምረት የህፃናት ሞትን መቀነስና የሰዎችን አካላዊ ጥንካሬና ጤንነት መጠበቅ ላይ ሊሰራ ይገባል ተብሏል።
በዋናነት የጨቅላ ህፃናትን ሞትና ያለጊዜው መወለድን ለመከላከል በእጅጉ ጠቃሚ የሆነውን ፎሊክ አሲድ የተሰኘውን ንጥረ ነገር፣ አንድ ሰው በቀን 4 መቶ ግራም ያህል ማግኘት ያለበት ቢሆንም ኢትዮጵያውያን በአማካይ በቀን ግማሽ ያህሉን ወይም 2 መቶ ግራም ብቻ ነው የሚያገኙት ተብሏል።
በዚህም ምክንያት እድሜያቸው ለወሊድ ከደረሱ ኢትዮጵያዊያን እናቶች መካከል 84 በመቶ  ያህሉ  ጤንነቱ ያልተሟላ ህፃን ለመውለድ የተጋለጡ ናቸው ብሏል-ጥናቱ።
በርካታ የጤና ጠቀሜታ ያለውን ቫይታሚን ኤ በተመለከተ ደግሞ ቫይታሚኑን ማግኘት ካለባቸው ኢትዮጵያውያን ህፃናት ውስጥ 80 በመቶዎቹ ማግኘት እንደማይችሉ ተጠቁሟል። እንደ መፍትሄም፤ የነቁና በአእምሯቸው የበለጸጉ እንዲሁም በአካላዊ ጥንካሬ የዳበሩ ህፃናትን ለማፍራት፣ ኢትዮጵያውያን የአመጋገብ ባህል ላይ በቀላል ወጪ ለውጥ የሚያመጣ ስልቶችን መጠቀም እንደሚገባቸው ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።


Read 13447 times