Print this page
Monday, 13 September 2021 00:00

ነዋሪውን እየተፈታተነ ያለው የሸቀጦች ዋጋ ንረት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በሸቀጦች የዋጋ ንረት ክፉኛ እየተፈተነ ያለው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት፤ በተጠናቀቀው የ2013 የነሐሴ ወር በ20 ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ነው የተባለውን አጠቃላይ የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት አስመዝግቧል። ከሰኔ እስከ ነሐሴ ባሉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥም በከፍተኛ ፍጥነት የጨመረ የዋጋ ግሽበት መመዝገቡንም የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን ካቀረባቸው ሪፖርቶች መረዳት ይቻላል።
የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የነሐሴ ወር 2013 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ የዋጋ ግሽበት ጋር ሲነጻጸር የ30.4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተመልክቷል። በወሩ የነበረው አጠቃላይ የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ደግሞ 37.6 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።
በተለይ በተጠናቀቀው ነሐሴ ወር በዳቦ እህሎች፣ በሩዝ፣ በጤፍ፣በእንጀራ፣ በስንዴ፣ በማሽላ፣ በበቆሎ፣ በገብስ፣ በፓስታና መኮሮኒ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛው መሆኑ ተመልክቷል። በተጨማሪም የምግብ ዘይት፣ ስጋ፣ ወተት፣ አይብና እንቁላል፣ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመም፣ ጨው በርበሬና ቡና የዋጋ ጭማሪው ከታየባቸው ሸቀጦች ተጠቃሽ ሆነዋል።
ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ላይ ደግሞ የነሐሴ 2013  የዋጋ ጭማሪ ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2012 ጋር ሲነጻጸር የ20.8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተመልክቷል። በተለይም በአልኮል፣ ትምባሆ፣ አልባሳት፣ ጫማ፣ ጫት፣ ማገዶና ከሰል፣ የቤት ግንባታ እቃዎች (ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ውስጥ ማስዋቢያ እቃዎች፣ ህክምና፣  ጌጣጌጥ  እንዲሁም የቤት ኪራይ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር  ከፍተኛ ነው ተብሏል።
ያለፈው ሐምሌ ወር 2013 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበትን ስንመለከት፣ 22.3 በመቶ ሲሆን ይህም በነሐሴ ወር ከተመዘገበው 30.4 በመቶ ጋር ሲነፃፀር፣ የ8.1 በመቶ ልዩነት ይስተዋልበታል።
በተመሳሳይ ከሶስት ወር በፊት ማለትም በሰኔ 2013 ከነበረው የ24.5 አጠቃላይ የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት አንጻር የነሐሴ ወርን ስንመለከት ደግሞ የ5.9 በመቶ ጭማሪን እንመለከታለን። ይህም በሰኔና በነሐሴ ከነበረው የዋጋ ግሽበት አንፃር የሐምሌ ወሩ ዝቅተኛ መሆኑን ያመለክታል።
ምግብ ነክ የሆኑ ሸቀጦችን የ3 ወራት ማለትም የሰኔ፣ ሐምሌና ነሐሴ ወር የዋጋ ግሽበት ስንመለከት ደግሞ በሰኔ ወር 28.7 በመቶ፣ በሐምሌ ወር 23.7 በመቶ እንዲሁም በነሐሴ 37.6 በመቶ ሆኖ እናገኘዋለን።
በሰኔ ወር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸው የነበሩ የምግብ ሸቀጦችን ስንመለከት የበቆሎና የገብስ ዋጋ በእጥፍ የጨመረበት ሆኖ ተመዝግቧል። የስጋ፣ የምግብ ዘይት፣ የቅቤ፣ የቅመማ ቅመም፣ የበርበሬና የቡና ዋጋ ደግሞ በወቅቱ ከፍተኛ  ንረት የታየባቸው ናቸው።
በሰኔ ወር ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጋር ሲነፃፀር የ19 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የሚያመለክተው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ሪፖርት፤ በተለይ ልብስና ጫማ፣ የቤት መስሪያ እቃዎች፣ የቤት ኪራይ፣ እንዲሁም ህክምና ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶ ነበር።
የሐምሌ 2013 ወርን የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ስንመለከት ደግሞ የእህል፣ የጥራጥሬና የአትክልት ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን ምግብ ነክ ካልሆኑ ሸቀጦች መካከልም የግንባታ ግብአቶች፣ አልባሳት፣ የሃይል ምንጮች (ከሰልና ማገዶ) የዋጋ ጭማሪ ከታየባቸው ተጠቃሽ ናቸው።
ለዚህ የሸቀጦች ዋጋ በፍጥነት መናርና የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም  መፈታተን መንግስት በዋና ምክንያትነት የሚያቀርበው የገበያ ሰንሰለቱ አሻጥር የተሞላበት መሆኑን ነው።
ከዚህ ባለፈም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ ሃገሪቱ ያለችበት ጦርነት ለሸቀጦች ዋጋ ንረት ከሚቀርቡ ምክንያቶች  ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች በበኩላቸው፤ ለዋጋ ንረቱ በዋናነት የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣምን (የተፈላጊ ሸቀጦች ምርት ማነስን) የሚጠቅሱ ሲሆን በዚያው መጠን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በገበያው ውስጥ መበተንም ለንረቱ ምክንያት መሆኑን ያስገነዝባሉ።
መንግስት የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ምን እያደረገ ነው?
ለሸቀጦች የዋጋ ንረት በዋናነት የገበያ ሰንሰለቱ በአሻጥር መተብተቡ ነው የሚል ግምገማ ያለው መንግስት፤ ይሄንኑ ለማስተካከል የአሻጥር ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው ባላቸው ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። ምርት ያለ አግባብ ደብቀዋል፣ አሽሽተዋል፣ ሰውረዋል ያላቸውን ነጋዴዎች ለህግ እያቀረበ መሆኑን በየጊዜው እየገለጸ ነው።
ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል፤ የንግድ አሻጥር ፈፅመዋል ያላቸው ከ80 ሺህ 641 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እርምጃ መውሰዱንም አስታውቋል።
በዚህ እርምጃ 80ሺህ 641 የንግድ ድርጅቶች ላይ የእገዳ፣ 520 የንግድ ድርጅቶች ላይ የንግድ ፈቃድ ስረዛ፣ በ2 ሺህ 230 ተቋማት ላይ ክስ መመስረቱ ታውቋል። በሌላ በኩል፤ ከገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ ገበያውን ያረጋጋልኛል ያለውን እርምጃም እየወሰደ ነው። ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆነው ከሳምንታት በፊት ጀምሮ በባንክ በብድር አወሳሰድ ላይ የተለየ መመሪያ ማዘጋጀቱ ነው።
ቋሚ ንብረትን አስይዞ ብድር እንዳይወሰድ መገደቡ በገበያ  ሊኖር የሚችልን ከፍተኛ የገንዘብ  ዝውውር ሊገታ ይችላል የሚል ግምገማ ያለው መንግስት ይሄንኑ እርምጃ ወስዷል።
ለዚሁ የሸቀጦች ዋጋ ንረት ማረጋጊያ ይሆን ዘንድ በመንግስት ከተወሰዱ የመፍትሄ አማራጮች በተወሰኑ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የታክስ እፎይታ ተግባራዊ ማድረግ ነው።
በዚህ መሰረት ከነሐሴ 28 ቀን 2013 ጀምሮ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ዘይት ከውጭ ሃገር ያለምንም የጉምሩክ ቀረጥ እንዲገቡ አድርጓል።
ፓስታ፣ መኮረኒ፣ እንቁላል ደግሞ ያለተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲገበያዩ ውሳኔ አሳልፏል።
ይህን ውሳኔ ተከትሎም በዋናነት በዘይት ምርት ላይ ጥሩ የሚባል የዋጋ መሻሻል እየታየ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
750 ብር ድረስ ይሸጥ ነበረው አምስት ሊትር ዘይት አሁን ወደ በ560 እስከ 590 ብር ለመውረድ ችሏል። በስንዴና በሩዝ  ዋጋ ላይ ግን እስካሁን ይህ ነው የሚባል ለውጥ አለመስተዋሉን ያነጋገርናቸው ነጋዴዎችና ሸማቾች ይገልጻሉ።

Read 1403 times