Saturday, 11 September 2021 00:00

የ3007 ዓ.ም ትውልድ ትርክት

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

 (ደባኪ - ጋፋት - ጉባ)
አንድ ሰው ‹‹የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ›› ሲል፤ ለመግለፅ የፈለገው የኢትዮጵያን የቅርብ ዘመን ታሪክ መሆኑ ግልፅ ነው። ትኩረቱ ከአፄ ቴዎድሮስ ወዲህ ባለው የሐገሪቱ ታሪክ መሆኑ ይገባናል፡፡ ከዚህ ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። ግን ‹‹ዘመናዊ ታሪክ›› (Modern History) የሚል ነገር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በጣም የተሳሳተ መልዕክት የሚሰጥ ሐረግ ነው። ይሁንና ቃሉ ከአገልግሎት አልተሻረም፡፡
ለምሣሌ፤ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ የሚመጡ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪዎች፤ እንኳን በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የተፈፀመን ጉዳይ በ2007 ዓ.ም የተከሰተውን ድርጊትም በዘመናዊ ታሪክ ክፍል ሊያካትቱት አይችሉም፡፡ በ3007 ዓ.ም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ገና ታሪክ ለመሆን ያልበቁትን የ2007 ሐገራዊ ምርጫ እና የኦባማን ጉብኝት፤ ‹‹እጅግ ጥንታዊ ታሪክ›› በሚል ይጠቅሱት ይሆናል እንጂ - ለመጠቀስ የሚያበቃ ፋይዳ ይዞ ከታያቸው- ዘመናዊ ታሪክ አይሉትም፡፡ ዛሬ ገና የታሪክ ማዕረግ ያላገኙትን (ከፖለቲካ መዝገብ ያልተፋቁትን) እነዚህን የ2007 ክንውኖች፤ እንኳን በዘመናዊ ታሪክ በጥንታዊ ምዕራፍም ሊያካትቷቸው አይችሉም፡፡ ‹‹ዘመናዊ ታሪክ›› (Modern History) የሚለው ገለፃ አስቸጋሪ የሚሆነው በዚህ የተነሳ ነው፡፡
እንዲያውም በ3007 ዓ.ም፤ ምናልባት ራሱ ታሪክ የሚባል ፅንሰ ሐሳብ ሊጠፋ ይችላል፡፡ የታሪክ ፀሐፊ የሚል የሙያ ዘርፍም ሊከስም ይችላል፡፡ ዛሬ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ግስጋሴ፤ የቦታን ገዳቢነት እንዳጠፋው፤ የጥንቱን እጅግ ሰፊ ዓለም አንድ መንደር እንዳደረገው ሁሉ፤ በተመሳሳይ የጊዜን ገዳቢነት አፍርሶ፤ ዛሬ፣ ትናንት እና ነገ የሚባሉ የጊዜ አውታሮች ሊያጠፋቸው ይችላል። ስለዚህ፤ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ ‹‹ቢጫ›› ቀለም በተቀቡ የጊዜ ታክሲዎች ተሳፍረው፤ በጊዜ ጎዳና እየከነፉ ወደፊት እና ወደ ኋላ ለመሄድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሊኖራቸው ይችላል። ‹‹ደመና›› ጠቅሰው፤ ከዛሬ ወደ ነገ ወይም ወደ ትናንት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን፤ ሰባት (?) የቅዱስነት ማዕረጋት ውስጥ በአንዱ ቅዱሳን የቦታንና የጊዜን አጥር በማፍረስ፣ እንደ እግረ ፀሐይ በአንድ ጊዜ ብዙ ቦታዎች የመገኘትና ደመና ጠቅሶ የመጓዝ ብቃት የሚያገኙ ቅዱሳን እንዳሉ ይተረካል፡፡ በ3007 ዓ.ም ቴክኖሎጂ ይህን ችሎታ ሊፈጥር ይችል ይሆናል፡፡
የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ ‹‹ለጉብኝት ወደ 2007 ዓ.ም እንሂድ›› ለማለት የሚችሉ ስልጡኖች ይሆኑ ይሆናል። ምናልባት፤ ታሪክን ከዲጂታል ገፆች ወይም ከወረቀት በማንብብ ሳይሆን፤ ‹‹መሚፋይድ›› የሆኑ (በሬሳ ማድረቂያ የደረቁ) የታሪክ ክስተቶችን በዓይን ማየት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ምናልባትም ‹‹ሃሎ ሲኦል፣ ሃሎ ገነት ወይም ሃሎ ሰማይ ቤት›› እያሉ መደወል የሚችሉ ይሆናል፡፡ ይህ የስብሃትን ሀተታ- ኮምቡጡር ይመስል ይሆናል፡፡ ግን በዚህ ትውልድ ዕድሜ ስንት ነገር አየን፡፡
ሆኖም፤ የነገሮች መሠረታዊ ይዘት ብዙ ሳይቀየር በአሁኑ መልክ ከቀጠለ፤ በ3007 ዓ.ም የሚኖር አንድ ጋዜጠኛ፤ የኛን ዘመን ኢትዮጵያውያን ከቀደሙትና ከእኛ በኋላ ከሚመጡት በርካታ ትውልዶች ለይቶ መጥቀስ ከፈለገ፤ በእነሱ ዓይን ወይም ሚዛን እርባና ያለው ሥራ ካለን፣ የኛን ዘመን ታሪክ ሲጠቅስ - ‹‹በጥንታዊ ታሪክ›› እያለ ነው፡፡
የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ፤ ‹‹በምርጫ 97 ቅንጅትና ኢህአዴግ ባካሄዱት ክርክር የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበው ማነው? ምርጫው ተጭበርብሯል አልተጭበረበረም?›› የሚል ነገር በፍፁም አጀንዳ አድርጎ አያነሳም፡፡ ሌላው ቀርቶ፤ ደርግን ከስልጣን ያባረረው ኢህአዴግ ይሁን ቅንጅት ለመለየት ይቸገራል። ዛሬ ሰይፍ የሚያማዝዙ የፖለቲካ ጉዳዮች በመጭው ዘመን እይታ የጅሎች ንትርክ መስለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን (ኢትዮጵያዊ፣ አሜሪካዊ ወዘተ የሚባል ነገር ትርጉም የሚሰጥ ከሆነ) ውሎ አድሮ ታሪክ የሚሆነውን የዛሬውን ዘመን ድርጊት በዝርዝር ሊያስታውሱት አይችሉም። እኛ የአንደኛውን ሺ ዓመት (ሚሊኒየም) ‹‹ከታላቅነት ማማ ወርድን በድህነትና ኋላቀርነት መርመጠመጥ የጀመርንበት ዘመን›› ብለን በጥቅል እንደ ጠቀስነው፤ በጥቅል ይጠቅሱን ይሆናል፡፡
እናም፤ በእነሱ ዓይን ወይም ሚዛን፣የእኛ ትውልድ እርባና ያለው ሥራ ሊጠቀስ የሚችለው #ከረጅም ዘመናት ውድቀት በኋላ የተስፋ ዘር መዝራት የቻለ ትውልድ” በሚል ይመስለኛል፡፡ ነገሩ ይመስለኛል ነው። በእርግጠኝነት ለመናገር የማይቻል ጉዳይ መሆኑ ሳይዘነጋ፤ ጋዜጠኛው ‹‹ለረጅም ዘመናት ቁልቁል ስንወርድ ከቆየን በኋላ፤ እንደገና መነሳት የጀመርነው፤ በሦስተኛው ሚሊኒየም መጀመሪያ በነበረው ትውልድ ነው›› በሚል ያስታውሰን ይሆናል። መቼም፤ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን የእኛን ትውልድ በዚህ ዓይነት ጥቅል ነገር ካስታወሱን ዕድለኞች ነን፡፡ በተረፈ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወይም በኃይለማርያም ደሳለኝና በመንግስቱ ኃይለማርያም መካከል ልዩነት አይመለከቱም ብቻ ሣይሆን ልዩነት የማየት ፍላጎትም ጨርሶ አይኖራቸውም ማለት ይቻላል፡፡
በ3007 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ታሪክ ፀሐፊ የሚኖር ከሆነ፤ ይህ ታሪክ ፀሐፊ፤ ‹‹ለበርካታ ዓመታት የአባይን ወንዝ ለማልማት የሚያስችሉ የተለያዩ ጥናቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም፤ ብዙዎቹ ከሸልፍ ላይ ተጥለው አቧራ ሲጠጡ ከርመዋል፡፡ የአባይን ወንዝ የማልማት ዕቅድ ሁሌም ከውጭ ዕርዳታ ጋር ተያይዞ የሚታሰብ በመሆኑ፤ ዕርዳታ ፍለጋ ስንወጣ፤ ዘወትር ሐሳባችንን በእንጭጩ የሚጨፈለቅና የሚቀጭ ምላሽ እየገጠመን፤ ከኛው ሐገር መንጭቶ በበራችን ከሚፈሰው የአባይ ወንዝ አንዲት ጠብታ ውሃ መንካት ሳንችል ቆይተናል፡፡ ግብፅ፤ ‹ከአባይ ውሃ አንዲት ጠብታ ውሃ መንካት አትችሉም› በሚል እያስፈራራችን፤ እንዲህ ዓይነት መራራ በደል ተሸክመን በመኖራችን ከፍተኛ የመንፈስ ስብራት ደርሶብን ነበር። ሰፊ ለም መሬትና የውሃ ሐብት ይዘን፤ በተደጋጋሚ በረሃብ ማለቃችንና በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች እየተራቡ በዓለም ህዝብ ፊት ለልመና መቆማችን ከፍተኛ የመንፈስ ስብራት ፈጥሮብን ነበር፡፡ ስለዚህ የ‹መቻል› ሳይሆን ‹ያለመቻል› መንፈስ ነግሶብን ቆየን፤ ድህነት እንደ በሬ ቀንበር ጭኖ፣ እንደ ባሪያ ቋንጃችንን ሰብሮ ሲገዛን ኖሯል›› ብሎ ሊጽፍ ይችላል፡፡
ጠፈርተኞች፤ በህዋ ሆነው ምድርን ሲመለከቱ፤ ረጅሙ የቻይና ግንብ ይታያቸዋል ይላሉ፡፡ እናም፤ በ3007 ዓ.ም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ኋላ ሲመለከቱ ጎልቶ ሊታያቸው ከሚችሉ ነገሮች አንዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ ቆሜ ስመለከተው፤ እንደኛ ያለ ታሪክ ላለው ህዝብ፤ እንደ ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት በራስ አቅም ለመስራት መነሳት ትልቅ ሥራ ነው፡፡
እኛ ታላቁ የህዳሴን ግድብ ለመገንባት መነሳታችን፤ የበራ ሻማን እፍ ብሎ ማጥፋት ይሳነው የነበረ ሰው፤ ተራራን ገፍቶ ለመጣል ሲነሳ ከማየት ጋር ሊነፃፀር የሚችል የለውጥ ኃይል ያጀበው ድርጊት ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት እንደ በሬው በዝማም ሸብቦ ከያዘን ‹‹የአይቻልም መንፈስ›› መፈታት ነው። ስለዚህ፤ የህዳሴውን ግድብ ያለ ውጭ ዕርዳታ ሰርቶ ማጠናቀቅ ሳይሆን ‹‹ግድቡን ራሳችን እንገነባዋለን›› ብሎ ከመነሳት የሚልቅ ተዓምራዊ ተግባር ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሞት መነሳት እንጂ፤ከተነሱ በኋላ መራመድ ተአምር ሊሆን አይችልም፡፡
 የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ የህዳሴው ግድብ የፈጠረው የመንፈስ ብርሃን ጎልቶ ይታያቸው ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንዲያውም፤ ከኢትዮጵያ ድንበርና ከዚህ ዘመን አጥር ተሻግሮ፤ በተከታታይ ብዙ ትውልዶች ልብ ውስጥ ደምቆ ሊያበራ የሚችል ብርሃን ነው፡፡ የአፍሪካ ህዳሴ ፋና ለመሆን የሚችል አህጉራዊ ክስተት ነው፡፡ 
የህዳሴው ግድብ፤ አፍሪካን በበታችነት መንፈስ ቀይዶ ለማኖር፣ ቀፍድዶ ለመያዝ ሲባል በመሰሪ ጥበብ ከተሸረበው ሰንሰለት በማውጣት እግረ-መንፈሳችንን፤ ከቅኝ ግዛት እግረ ሙቅ የሚያላቅቅና ካቴናን አውልቆ የሚጥል የአርነት መንፈስ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ለአፍሪካውያን የሚሰጣቸው ትርጉም ምን እንደሆነ ለመረዳት፤ ጉባ በመሄድ ግድቡን የጎብኙ አፍሪካውያንን ቃል ልብ ብሎ ማድመጥ ብቻ በቂ ነው፡፡
ሰምታችኋቸው ከሆነ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት ለጉብኝት ወደ ጉባ የሄዱ የአፍሪካ ሐገራት ወታደራዊ መኮንኖች፤ እንደ ማንኛውም ጎብኚ ያለውን ሁኔታ ከተመለከቱ በኋላ፤ ‹‹በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ጥሩ ሥራ ሠርታችኋል። ከገመትኩት በላይ ነው›› በማለት ነገር አዳንቆ ከመመለስ አለፍ ብለው፤ ለፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ለኢንጅነር ስመኘው ሽልማት ሲያበረክቱ አይተናል፡፡ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ወታደራዊ መኮንኖች መካከል፤ የዛምቢያው መኮንን፤ ‹‹ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ፤አፍሪካ ያለ ውጭ ዕርዳታ በራሳቸው አቅም ምን መስራት እንደሚችሉ አሳይቶናል›› ሲሉ የተናገሩት ቃል፤ግድቡ ለአፍሪካውያን የሚሰጣቸውን ትርጉም በትክክል የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡
አፍሪካውያን ከምዕራብ የዕርዳታ አንቀልባ ወርደው በራሳቸው እግር ለመቆም ሲሞክሩ የታየበት፤ የቅኝ ግዛት ኮተትና ግሳንግስ ተሽቀንጥሮ ሲጣል ያየንበት፣ኢ-ፍትሃዊ ሰንኮፍ በይቻላል መንፈስ የተነቀለበት፣ክፍለ - አህጉራዊ የትብብር ማዕከል ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ግድብ መሆኑን እያየን ነው፡፡ የሱዳኑ አምባሳደር ግድቡን ከጎበኙ በኋላ፤ ‹‹ይህ ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤የአፍሪካ አህጉር ግድብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ፤ ለዓለም ጭምር የሚጠቅም ሥራ እየሰራች ነው›› ሲሉ መናገራቸው ለዚህ አብነት ነው፡፡ ስለዚህ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ይህን ትውልድ በዚህ ያስታውሱት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡
ጉዞ ጀምረናል
‹‹ጀምረናል ጉዞ ጀምረናል፤ወደ ኋላ ማን ይመልሰናል›› የሚለው ህብረ - ዝማሬ፤ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውንን ልብ ላያሞቅ ይችላል። ሆኖም፤ የሕዳሴው ግድብ በአባይ ተፋሰስ ሊገነቡ ከሚችሉት ግድቦች ውስጥ ትልቁ ግድብ በመሆኑ፤መጭው ትውልድ ከታላቁ ህዳሴ የሚበልጥ ግድብ በዚህ ተፋሰስ ሊሰራ እንደማይችል እናውቃለን። ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ የህዳሴው ግድብ ለመጪዎቹ 400 ዓመታት ሊያገለግል የሚችል ግድብ ነው። ስለዚህ ይህ የኛ ትውልድ፤ ወደፊት የሚመጡ ተከታታይ ትውልዶች በልዩ አድናቆት የሚመለከቱት ሥራ እየሰራ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ይህ ትውልድ፤ ሐገሪቱን ከአንድ ሺህ ለሚበልጥ ዓመታት ቁልቁል እያወረዳት፤ እንደ ሲዖል አዘቅት ያለ ማቋረጥ እየዋጣት፣ ከተስፋ መቁረጥ ጠርዝ ከጣላትና በተሸናፊነት መንፈስ ከከፈናት የውርደት ጉዞ እንድትወጣ የሚያግዝ ሥራ እየሰራ ያለ ጀግና ትውልድ ይመስለኛል። የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ ‹‹ለራስ ሲቆርሱ…›› ብለው ሊቀልዱብኝ ይችላሉ። ግን እንደዚህ ማሰቤን መደበቅ አልሻም፡፡  
ስለዚህ፤ ጉባ የምትገኘው የግድቡን ግንባታ ያበሰረችው የመሠረት ድንጋይ ብዙ ትውልዶች በአድናቆት የሚመለከቷት ድንጋይ ትሆናለች። በእርግጥ፤ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፤ ‹‹ለእኔ ይህች ድንጋይ የውርደት ካባን ማራገፍ የጀመርንባት ድንጋይ ነች›› ሲሉ መናገራቸውን የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ላያስታውሱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም፤ ዛሬ ላይ ቆሞ ለሚያይ ሰው፤ ጉባ በክብር የተቀመጠችው ያቺ ድንጋይ፤ ተራ የፕሮቶኮል ጌጥ ወይም የተለመደ የማስታወሻ ድንጋይ መስላ አትታየኝም። ለአንድ የታሪክ ምዕራፍ፤ እልባት ሆና የተቀመጠች ልዩና ክቡር ድንጋይ ነች፡፡ ከዚያች ድንጋይ በይፋ መቀመጥ በፊትና በኋላ ነገሮች በእጅጉ ተቀያይረዋል። እኛ ስለ ራሳችን ያለን ግምት ብቻ ሣይሆን ዓለም ስለኛ ያለው ግምትም ተለውጧል፡፡   
በዚህ በእኔ ስሌት፤ ትልቅ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ታሪክ ሊሆን የሚችለው ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየተሰራ ያለው፤ የውርደትን መራራ ጽዋ ሲጨልጥ በቆየ፤ ረሃብን፣ ድህነትን፣ ስደትን እስኪበቃው በተጋተ፤ በመጥፎ የታሪክ ሸክም ጎብጦ፤ ቅስሙ ክፉኛ በተሰበረ የኛ ትውልድ ነው፡፡ ከመከራ አዘቅት ወጥቶ ይህን ገድል የሰራው፤ ኑሮ በሞላለት ወይም በልቶ በተረፈው ትውልድ ሳይሆን፤ ገና በልቶ መጥገብ ባልጀመረ ትውልድ በመሆኑ፤ ለ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም ይሰጣቸው ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ትውልድ፤ ከፊተኛው ትውልድ ድህነትን ተቀብሎ፤ ከእርሱ በኋላ ለሚመጡ ትውልዶች ብልፅግናን አውርሶ የሚያልፍ  ከሆነ፤ በእርግጥ በመጭው ትውልድ በክብር ይታወሳል፡፡
ያለፉ አራት መቶ ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክን በወፍ በረር ቃኝተህ፤ ከቅኝትህ የተገነዘብከውን የታሪክ ሐቅ አስፍር ብባል፤ ኢትዮጵያን እጅ ከወርች አስረው ያሰቃይዋት፣ የግሪንግሪት ጥለው የረጋገጧት ሁለት ዋነኛ ችግሮችን ተናገር ቢሉኝ፤ ‹‹የሀገራችን ሁለት ሠይጣን ችግሮች፤ ሐይማኖትንና ‹ጠቅላይ ግዛትን› ሰበብ አድርገው የሚለኮሱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ወይም ግጭቶች፤ እና የውጭ ወራሪ ኃይሎች ቀጥተኛ ጥቃትና ዘወርዋራ ሸፍጥ ናቸው›› እላለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት ቀያይ ሰይጣኖች ወይም ችግሮች፤ ለድህነትና ለኋላ ቀርነት አሳልፈው ሰጡን፤ ድህነትና ኋላ ቀርነት መልሰው ለሌሎች በርካታ ችግሮች አቀባበሉን፡፡ ቅብብሎሹ ያለ ማቋረጥ ቀጥሎ እዚህ ደርሰናል፡፡ በዚህ ትውልድ ይገታል ወይስ….? የሚለው ለትንቢት የማይመች ጉዳይ ነው፡፡ ግን ተስፋ እንዳለን አምናለሁ፡፡
እርግጥ፤ያለፉ ተከታታይ ትውልዶች፤ ደምና አጥንታቸውን ገብረው፤ ውድ የሐገር ነፃነት ቅርስ አስረክበውናል፡፡ ድሃና ኋላ ቀር ብንሆንም፤ ነፃነቷ የተከበረ ሐገር አውርሰውን አልፈዋል፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ፋና፣ የፀረ - ቅኝ አገዛዝ ትግል ቀንዲል የሆነች፤ ለጥቁር ህዝቦች ትግል የመንፈስ ኃይል በመሆን ታላቅ ከበሬታ የሚሰጣት ሐገር ሰጥተውናል፡፡
ኢትዮጵያ፤ ኋላ ቀርነት የተጫናት፣ድህነት ያደቀቃት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ያደከማት፣ የተረጋጋ የመንግስት አስተዳደር መመስረት የተሳናት ሐገር ሆና፤ የቅኝ አገዛዝ ኃይሎች እንደ ተራበ አውሬ በዙሪያዋ ሲያንዣብቡ፤ እንደ ተኩላ መንጋ ዘለው ሊሰፍሩባት ሲያደቡ ቢቆዩም ነፃነቷን አስከብራ ኖራለች፡፡ ግን ኋላቀርነትና ድህነት ረግጠው ገዝተውናል። በእኔ አስተያየት፤ ሐገሪቱን ለጠላት ተጋላጭ የሚያደርጋት፤ ኋላ ቀርነት መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘቡ ኢትዮጵያዊ መሪ አፄ ቴዎድሮስ ናቸው። አፄ ቴዎድሮስ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ጉዳይ አደጋ እንደተጋረጠበት ገብቷቸዋል፡፡ በየአካባቢው ሥልጣን በያዙና እርስ በእርስ በሚቀናቀኑ መሳፍንት የተከፋፈለችውን ሐገር በጦርነት አንድ ለማድረግ ሲሞክሩ፤ አደጋው ታይቷቸው ነበር፡፡
ቋራ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ ትምህርቱን ሲከታተል የነበረው ትንሹ ቴዎድሮስ (ካሣ ኃይሉ)፤ጥቂት ተከታዮችን ይዞ፤ የጎበዝ አለቃ ሆኖ የታሪክ ጉዞውን ጀመረ፡፡ ከሌሎች አቻ የአካባቢ መሳፍንት በተለየ አስተሳሰብ እየተመራ፤ ለተጠቁ አለኝታ የመሆንና ለፍትህ የመቆም ዝንባሌን እያሳየ፤ እያደርም ተከታዮቹን እያበዛ  የመጣው ካሣ ኃይሉ፤ የኢትዮጵያን ድንበር ገፍቶ፤ ሱዳንን በኃይል በመያዝ በሐገሪቱ አገዛዙን ከመሠረተው የግብፁ ገዢ መሐመድ ዓሊ ጋር ‹‹ደባኪ›› በተባለች ሥፍራ ጦርነት ገጠመ፡፡ ‹‹ደባኪ›› ላይ አስቦትና ገምቶት የማያውቅ ሽንፈት ደረሰበት፡፡ አንዳንድ የታሪክ ፀሐፊዎች፤ ‹‹በአፄ ቴዎድሮስ ህሊና ለሥልጣኔ የመጓጓት ልዩ ስሜት እንዲፈጠር ያደረገው፤ የደባኪ ጦርነት ነው›› ይላሉ፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ልዩ የመሪነት ሰብዕና እና ብቃት የተገለጠው በዚሁ ጦርነት መሆኑንም ይመሰክራሉ። ካሣ ኃይሉ፤ ‹‹ደባኪ››  ላይ ከግብፁ መሐመድ ዓሊ ጋር ጦርነት ገጥሞ  ክፉ ሽንፈት ሲገጥመው፤ ሽንፈቱን ሳያቅማማ ተቀብሎ፤ የሽንፈቱ ምንጭ ምን እንደሆነ ለመረዳት መቻሉን በማድነቅ፤ የመሪነት ብቃቱ የተገለጠበት የመጀመሪያው አጋጣሚም ይኸው መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የታላቅ መሪነት መገለጫ ጠባዩ፤ ሽንፈቱን መቀበሉና የሽንፈቱን ምንጭ ለይቶ ችግሩን ለማስወገድ ጥረት ማድረጉ ነው፡፡
የታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት፤ ካሣ ኃይሉ በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ያየው፤ ደባኪ ላይ በተካሄደው ጦርነት ነበር፡፡ የቋራው ካሳ እንደ አንበሳ የሚያስፈሩ ጋሜዎቹን አሳልፎ፤ ከመሐመድ ዓሊ ጋር ደባኪ ጦርነት በገጠመ ጊዜ፤ ከዚያ ቀደም አይቶት የማያውቀው የመድፍ ቅምቡላ እያስገመገመና እየተምዘገዘገ መጥቶ መሬት - ሰማዩን ሲደበላልቀው ተመለከተ። ጦርነቱን፤ በልበ ሙሉ ወታደሮቹ ጀግንነት የሚዘልቀው መሆኑ ገባው። ደባኪ ላይ ጦርነት የገጠሙት፤ ጥበብና ድንቁርና ነበሩ፡፡
ሻምላቸውን አገንድረው፤ በጀግንነት ገድሎ መሞትን እንጂ፤ ንግድ የሚባል ነገር የማያውቁት እኒያ የጃፓን የጦር አበጋዞች፤ ይህን ወግ አፍርሶ፤ ከጀርመኖች ጥበቡን ቀስሞ ቢራ ሲነግድ ያገኙትን አንድ ዘመዳቸውን ሲወቅሱ፤ ‹‹ልጄ የአባቶችህን ወግ ትተህ፤ ሻምላ አገንድሮ በጀግንነት መሰለፉን እንደ ከንቱ ነገር ወዲያ ጥለህ፤ ቢራ ጠማቂ ትሆን?›› በሚል ሲወቅሱት፤ ‹‹አጎቴ ተሳስተሃል፡፡ የዘንድሮ ሻምላ እንደ ድሮው፤ አየሩን ሲቀዝፍ ጆሮ የሚበጥሰውን የጃፓኖችን ዘመን ሻምላ ይዞ መገኘት አይደለም፡፡ የዚህ ዘመን ጀግንነት፤ ዶላር ይዞ መገኘት ነው›› እንዳለው፤ ካሣ ኃይሉ በደባኪ (Dabaki) አውድ ግንባር፤  ዋናው ነገር ጥበብ እንጂ ባዶ ጀግንነት እንዳልሆነ ተረዳ፡፡ የደባኪ ትምህርት ዕድሜ ዘመኑን ሁሉ  እረፍት ነስታ ጥበብን ፍለጋ እንዲባዝን አደረገችው። በመጨረሻ፤ ለሞት የሚያበቃ ስህተት አሰራችው፡፡
ያቺ ‹‹የአባቶቼ ሀገር›› እያለ ይጠራት የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ዘመናዊ ዕውቀትን ወይም የጦር መሣሪያን ካልታጠቀች፤ በዙሪያዋ ከሚያገሱት የተራቡ አውሬዎች አንዱ መጥቶ እንደሚሰለቅጣት፤ የጦር መሣሪያ ‹‹ሀሁ›› የተማረባት ደባኪ ነግራዋለች፡፡ ስለዚህ የጦር ኃይሉን ለማዘመን፣ የመንግስትን አስተዳደር ለማፅናት፣ ወሳኝ አድርጎ የሚመለከተውን ጥበብ ለመቅሰም ተጋ፡፡
በዚሁ ሰበብ ከታላቋ ብሪታንያ ጋር ለመቀያየም በቃ፡፡ ‹‹የእጅ ሙያ የሚያሰለጥን ሰው ላኩልኝ›› እያለ በወዳጅነት ሲጠይቅ ቆይቶ፤ አልሆን ሲለው፤ በግሉ ሙያተኞች አውሮፓውያን እንዲያመጡላት በወዳጆቹ በኩል (በግል) ሙከራ አድርጎ አልሳካ ሲለው፤ ለስብከት ከመጡት  አውሮፓውያን መካከል መርጦ፤ ጋፋት ላይ ጥበብን በኢትዮጵያ ሊያላምድ ሞከረ፡፡ በመንገድና  በብረታ ብረት ወዘተ ሥራ የሚያግዙትን እያከበረ፤ ሰባኪ ነኝ ባዮቹን ሰሜን ‹‹ያና›› እንዲቀመጡ አድርጎ የቻለውን አደረገ፡፡ በመጨረሻም፤ እየወሻከቱ፤ እንዳሰበው አልሆን ሲሉት እና እንግሊዝ ለላከው ደብዳቤ ምላሽ ስትነፍገው፤ ሰባኪ ነን ባዮቹን እና ቆንስላዎቹን ጠራርጎ እስር ቤት አስገባቸው፡፡
በዚህ ዘመን፤ ለእኛ ምሣሌ መሆን የሚችሉ ቦታዎችን እናገኛለን፡፡ ‹‹የና›› እና ‹‹ጋፋት››። ‹‹የና›› እና ‹‹ጋፋት›› የቴዎድሮስን ሁለት ፈተናዎች መወከል የሚችሉትን ያህል፤ ለዛሬው ዘመን ትውልድ ኑሮ ምሣሌ የመሆን ልዩ ትርጉም አላቸው፡፡ ‹‹ጋፋት›› የጥበብ መንደር ነች። ‹‹የና›› ደግሞ የሐይማኖት፡፡ ‹‹የና›› በአፄ ቴዎድሮስ ፈቃድ ያገኙ ሚሲዮናውያን፤ ለቤተ እስራኤሉ ሐይማኖት የሚሰበክባት (ክርስትና) ምድር ናት፡፡ ‹‹የና›› እና ‹‹ጋፋት›› በተምሳሌትነት፤ የዚህ የኛን ትውልድ ፈተናም ሊገልጡ ይችላሉ፡፡ ትንታኔ የሚያስፈልገው አልመሰለኝም፡፡ ሆኖም፤ የኛ ትውልድም በ‹‹የና›› እና ‹‹ጋፋት›› ሊጠቀስ የሚችል ፈተና እንደተጋረጠበት አምናለሁ፡፡
ሐገሪቱ ሳይወራረድ የዘለቀ የታሪክ ዕዳ ተሸክማ፣ የዜጎችን ነፃነት የሚያከብር አስተዳደር አጥታ፤ ከቴዎድሮስ ዘመን እየተጎተተ የመጣ ያልተመለሰ ጥያቄ እንደሰቀዘ ይዞ ከ1983 ዓ.ም አደረሳት፡፡ በ1983 እንደ ቴዎድሮስ ዘመን የመበታተን አደጋ ላይ ነበረች። ህገ መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በመዘርጋት የእርስ በእርስ ጦርነት መነሻዎችን ማስታገስ ብትችልም፤ ኋላ ቀርነትና ድህነት አጉብጦ ሊገድላት አንድ ሐሙስ የቀራትን ሐገር የተረከበው ይህ ትውልድ፤ባለተስፋ ሐገር መፍጠር መቻሉን የሚያውቀው የ3007 ዓ.ም ትውልድ ብቻ ይሆናል። በመጨረሻ፤ የጀመርነው ጉዞ ከተሳካልን የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ ድንቅ የዕድገት ጉዟቸውን ሲተርኩ፤ ከደባኪ ተነስተው፤ በጋፋት በኩል አድርገው፤ ጉባን በማጣቀስ፤ አፍሪካን የሚጨምር ትርክት ሊሰሩ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ከቀደምት የአዲስ አድማስ ጽሁፎች መሃል ለትውስታ አምድ ተመርጦ በድጋሚ ለንባብ የበቃ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡


Read 554 times